በቬንዙዌላ መሬት መንቀጥቀጥ ልጇን ለማዳን ሕይወቷን ያጣችው እናት

እናት የልጇ ሕይወት ለማዳን እንደሞተች ተገልጿል

የፎቶው ባለመብት, Instagram

የምስሉ መግለጫ, እናት የልጇ ሕይወት ለማዳን እንደሞተች ተገልጿል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በቬንዙዌላ በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ወቅት አንዲት እናት ልጇን ለማዳን ስትል ሕይወቷ ማለፉን እግር ኳስ ተጫዋቹ ባለቤቷ ሄክተር ቤሎ እና የአገሪቱ ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ገለጹ።

የቬንዙዌላ የዜና ምንጮች ዘገባ እንደሚያሳየው ሕወቷን ያጣችው እናት አንድሪያ ትባላለች። ባለቤቷ ቤሎ በኢንስታግራም ገጹ ባሰፈረው ጽሑፍ "ውድ ፍቅሩ" በአገሪቱ በተከሰቱት ሁለት ኃይለኛ የመሬት መንቀጥቀጦች ወቅት የትንሽ ልጃቸውን ሕይወት ማዳኗን አስታውቋል።

"ፍቅሬ፤ እንዴት እንዳዳንሻት፣ ልጃችንን ለማዳን ስትይ እንዴት ሕይወትሽን እንደሰጠሽ፣ የመጨረሻ ትንፋሽሽን በምትተነፍሽበት ጊዜ እንኳ ያልተውሻት ደፋር ሴት እንደነበርሽ ታሪኩን እነግራታለሁ" ሲል ጽፏል።

በቬንዙዌላ ዋና ከተማ ካራካስ አቅራቢያ በተከሰተው መንታ የመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት 920 ሰዎች ሲሞቱ ከ3,000 በላይ ደግሞ ተጎድተዋል። የነፍስ አድን ሠራተኞች በፍርስራሾች ውስጥ ተቀብረው በሕይወት ያሉ ሰዎችን ለማዳን የሚያካሂዱትን ፍለጋ ቀጥለዋል።

ቤሎ ኢንስታግራም ላይ ባጋራቸው ተከታታይ ልጥፎቹ ሆስፒታል ውስጥ ያለችውን ልጁን ለመመልከት ወደ ካራካስ መጓዙን ገልጿል።

"ልጄ እና አክስቷ በጥሩ ሁኔታ ላይ ናቸው። ዛሬ አይወጡም፤ ሆስፒታሉ ውስጥ ይቆያሉ። በዚህ ከባድ ህመም ውስጥ ስለደገፋችሁኝ እጅግ አመሰግናለሁ" ብሏል።

በሌላ ልጥፉ ደግሞ "እንዴት አድርጌ ነው የእርሷን ሕይወት ለማትረፍ የአንቺን ማጣትሽን እና ምንም ነገር ለማድረግ እዚያ እንዳልነበርኩ ለልጅሽ የምነግራት? እንዴት እገልጸዋለሁ? [ፈጣሪ] ጥንካሬውን ስጠኝ" በማለት ጽፏል።

ኩማና ዴ ካምፔኦነስ የተሰኘው የቬንዙዌላ የእግር ኳስ ቡድን ተጫዋቾች የፕሬስ እና የማስታወቂያ ድርጅትም ስለኳስ ተጨዋቹ ባለቤት ሞት ጽፏል።

"የእግር ኳስ ተጫዋቹ ሄክተር ቤሎ 'ኪኬ' የትዳር አጋር አገሪቱን የመታውን የመሬት መንቀጥቀጥ ተከትሎ ፍርስራሽ ውስጥ ሕይወቷ አልፎ መገኘቱን ስንገልጽ በሐዘን ነው" ብሏል።

"ልጃቸው ግን ሙሉ ቤተሰቡ የሚኖርበት ሕንጻ ላይ ከደረሰው መደርመስ ተርፋለች" ሲል የሕጻኗን መትረፍ አስታውቋል።

ሄክቶር ቤሎ ከልጁ ጋር "ብቻውን" መቅረቱን በመጥቀስ ሐዘኑን ገልጿል

የፎቶው ባለመብት, Instagram

የምስሉ መግለጫ, ሄክቶር ቤሎ ከልጁ ጋር "ብቻውን" መቅረቱን በመጥቀስ ሐዘኑን ገልጿል

በመሬት መንቀጥቀጡ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ እንዲሁም የሟቾች ማንነት የመለየቱ ሥራ አሁንም ቀጥሏል። በርካታ ሰዎችም ረቡዕ ዕለት ባጋጠመው መንቀጥቀጥ ጠፍተዋል።

ከሞቾቹ መከካል ሁለት ተጫዋቾች እንደሚገኙበት ክለቦቻቸው እና የቬንዙዌላ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ገልጸዋል።

ካራካስ እግር ኳስ ክለብ እንደገለጸው ከ18 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ የሚጫወተው ረዛን ሲጃ፤ ላ ጉዋኢራ በተባለው ስፍራ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ከቤተሰቦቹ ጋር አብሮ ሕይወቱ አልፏል።

'በክለብ ስፖርት ሳን አጉስቲን' የተባለው ቡድን ደግሞ ተጫዋቹ ቪክቶር ፓላሲዮስ በክለቡ አካዳሚ ውስጥ "የማይጠፋ አሻራ" ጥሎ ማለፉን በኢንስታግራም ገጹ አስታውቋል። "በኅልፈቱ የተሰማንን ህመም ለመግለጽ የሚያስችሉ በቂ ቃላት የሉንም" ሲል ሐዘኑን ገልጿል።

የቀድሞ 'ሚስ ቬንዙዌላ' አሸናፊ የነበረችው ጂሴል ሬየስ ደግሞ በመሬት መንቀጥቀጡ እናቷን ማጣቷን በኢንስታግራም ገጿ አስታውቃለች። የእናቷ ሞት የተሰማው ትንከባከባቸው ከነበረች እና በሕይወት ከተረፈችው ነርስ ነው።