ሜላኒያ ትራምፕ በዩክሬን ቀውስ በተባባሰባት ከተማ የተኩስ አቁም እንዲደረግ አሸማገሉ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካ ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ በሩሲያ በተያዘችው ኦልሽኪ ከተማ በሩሲያ እና ዩክሬን መሀል የተኩስ አቁም እንዲደረስ ማድረጋቸውን ዋይት ሐውስ አስታወቀ።

ያለ መድኃኒት፣ ምግብ እና ንጹህ ውሃ በአደጋ አፋፍ ላይ መሆኗ የተነገረላት ከተማዋ በጦርነት ግንባር ላይ የምትገኝ ሲሆን የተኩስ አቁሙ ከአምስት ቀናት በኋላ ይጀምራል ተብሏል።

ዩክሬን እና ሩሲያ ነዋሪዎችን ለማስወጣት እና የሰብዓዊ እርዳታ እንዲገባ መወሰኑን ጠቅሰው የተኩስ አቁም ስምምነቱን አረጋግጠዋል። ሁለቱ አገራት ጦራቸው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከጥቅምት 27 ጀምሮ ተኩስ ያቆማል ብለዋል።

ኦልሽኪ እአአ የካቲት 22 በተጀመረው ወረራ የመጀመሪያ ቀናት በሩሲያ ቁጥጥር ስር ውላለች። በሁለቱ ኃይሎች መሀል ቅርቃር ውስጥ የገባችው ከተማ ነዋሪዎች በሕይወት ለመቆየት አረም መመገብ መጀመራቸው ተነግሯል።

ዋይት ሐውስ ባወጣው መግለጫ ሜላኒያ ትራምፕ እና አንድ ወኪላቸው በቀጥታ ከሩሲያ እና ዩክሬን መሪዎች ጋር በመምከር የተኩስ አቁም ላይ እንዲደረስ ሰርተዋል ብሏል።

"ከሁለቱም አገራት ወታደራዊ ያልሆኑ፣ ሲቪሊያን መሪዎች የኦልሽኪን ነዋሪዎች በቤታቸው ለመጎብኘት እና ምን እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ለመወሰን በጋራ ይሠራሉ" ሲሉ ሜላኒያ ትራምፕ ተናግረዋል።

"ለቅቀው መውጣት ለሚፈልጉ ነዋሪዎች እርዳታ እና ወደሚፈልጉት መዳረሻ ትራንስፖርት ይዘጋጅላቸዋል። አንዳንዶች ወደ ሩሲያ፤ እና ሌሎች ደግሞ ወደ ዩክሬን መጓዝ ይፈልጋሉ ብዬ እገምታለሁ።"

ሜላኒያ ትራምፕ አክለውም የኦልሽኪ ነዋሪዎች "የተገደበ የኃይል አቅርቦት፣ ፈንጂ በተቀበረባቸው መንገዶች የሚኖሩ እና በየቀኑ ወታደራዊ ጥቃቶችን ችለው ቆይተዋል" ያሉ ሲሆን፤ "ያለ እኔ ጣልቃ ገብነት በከተማዋ ሰብዓዊ እርዳታ የማስገባት እድል እና አረጋዊያንን ማስወጣት የማይቻል ነው" ብለዋል።

የዋይት ሐውስ መግለጫ የተኩስ አቁሙ ለምን ያህል ጊዜ የፀና እንደሚሆን አልጠቀሰም።

የዩክሬን የምክር ቤት አባል እና የፕሬዝዳንት ዜሌንስሊ ፓርቲ የምክር ቤት ወኪል በኦልሽኪ እና በአካባቢው ታቅቦ የነበረውን ሰፈራን እንደገና በቅርቡ ይጀመራል ብለዋል።

ለዚህም በቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ የታወጀው የተኩስ አቁም ግቡን ለማሳካት ይረዳል ሲሉ አክለዋል።

የፕሬዝዳንት ፑቲን ቃል አቀባይ "ሰፈራውን ለቅቀው መውጣት የሚፈልጉ መውጣት ይችላሉ" ሲሉ ስምምነቱን አረጋግጠዋል።

ባለፈው ወር በኦልሽኪ የቀሩ አንዳንድ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ያለማቋረጥ በከባድ መሣሪያ በሚደበደብ እና ምግብ እና ውሃ በተቋረጠበት ከተማ በሕይወት ለመቆየት ሲሉ ምን እንደሚያደርጉ አሳዛኝ ታሪኮችን አጋርተዋል።

ሕፃናት በምግብ እጥረት፣ በሕክምና አገልግሎት አለመኖር እና በትምህርት እጦት "ውድቀት" ውስጥ መሆናቸን ተናግረዋል።

ሁሉም የከተማዋ ሕዝቦች በሩሲያ ኃይሎች "ሙሉ እግድ" እንደሚኖሩ የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሪ ሲቢሃ ገልፀዋል።

ዩክሬን በአካባቢው እርዳታ ለማድረስ እንደሞከረች ነገር ግን ባለፉት ወራት እንዳልተሳካላትም ተናግራለች።

ባለፈው መስከረም ክሬምሊን ኦልሽኪ "አስጊ ሁኔታ" ውስጥ እንደምትገኝ እና "ምግብ እና መድኃኒት ለማቅረብ ችግር" እንደገጠመው ተናግሮ፤ ለዚህም ኪዬቭን ወቅሷል።

ከሩሲያ ወረራ በፊት ኦልሽኪ 24 ሺ ነዋሪዎች ነበሯት። ዩክሬን አሁን በከተማዋ እና በዙሪያዋ ባሉ አካባቢዎች 200 ሕፃናትን ጨምሮ ስድስት ሺ ነዋሪዎች ብቻ እንደቀሩ አስታውቃለች።