ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ ሩሲያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች የተነሱት የሰላም ድርድሩ እንዲቀጥል ለማድረግ ነው አሉ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በርካታ የሩሲያ ማዕቀቦችን እንዲነሱ ያሳለፉት ውሳኔ፣ ሞስኮ በድርድር ጠረጴዛው ዙሪያ እንድትቆይ ለማድረግ የተደረገ ጥረት መሆኑን ተናገሩ።
ፕሬዝዳንቱ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት "በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ለሚደረገው ጦርነት ሰላም ለማምጣት የድርድር ሂደት ውስጥ ነኝ" ብለዋል። አክለውም "ሩሲያን በሞኝነት ከድርድር ጠረጴዛው እንድትርቅ የሚያደርግ ማንኛውም ነገር ማከናወን" እንደማይፈልጉ ጠቅሰዋል።
ትራምፕ ሩሲያ ላይ ተጥለው የነበሩ ማዕቀቦችን አርብ ምሽት ላይ ያነሱት የቅጣት ሕጉ ተግባራዊ ሊሆን ሁለት ቀናት ሲቀረው ነው። ይህ እርምጃ የተወሰደውም ከዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ ጋር የገቡበት ውዝግብ እየተባባሰ ባለበት ወቅት ነው።
ዜሌንስኪ እሁድ ዕለት ኤንቢሲ ኒውስ ከተባለው የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጎን መሰለፍ "ታሪካዊ ስህተት" እንደሚሆን ተናግረዋል።
የሩሲያ መልዕክተኛ የሆኑት ኪሪል ዲሚትሪየቭ በበኩላቸው የትራምፕን ማዕቀብ የማንሳት ውሳኔ "አስፈላጊ እና እውነተኛ ታሪካዊ ቅጽበት" ሲሉ ጠርተውታል። በአሜሪካ ኮንግረስ ጸድቀው፣ መስከረም ላይ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በፊርማቸው ሕግ ያደረጓቸው ማዕቀቦች፣ በዋሽንግተን እና በዓለም አቀፉ ገበያ ላይ "ከባድ ጉዳት" ሊፈጥሩ ይችሉ እንደነበርም መልዕክተኛው አክለዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የማዕቀቦቹን መነሳት የገለጹት የ60 ቀናት እገዳ በሚል ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ ማዕቀቦቹ በአሜሪካ እና በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ላይ ሊያደርሱ የሚችሉት ተፅዕኖ እንደሚገመገም አስረድተዋል።
ትራምፕ በበኩላቸው የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት "ጦርነቱ እንዲቋጭ አይፈልግም፣ ምናልባትም ፈልጎ አያውቅም" ሲሉ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ለጥፈዋል። "ከሁለት ዓመት በፊት አሁን ሊደርስበት ከሚችለው የተሻለ ስምምነት መፈጸም ይችል ነበር" በማለትም አክለዋል።
ዜሌንስኪ፣ ሩሲያ በየካቲት 2014 ዓ.ም. ሙሉ ወረራ ከከፈተችበት ጊዜ አንስቶ ጦርነቱ እንዲቋጭ ጥረት ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን በአንጻሩ ፕሬዝዳንት ፑቲን ሰላምን እንደማይፈልጉ በመግለጽ በተደጋጋሚ ከስሰዋል።
ባለፈው ሳምንት አሜሪካ ከሩሲያ ለመግዛት የሚያስችላትን አወዛጋቢ ስምምነት ከፈጸመች በኋላ የዋሽንግተን እና ኪዬቭ ግንኙነት መቃቃር ውስጥ ገብቷል።
ሩሲያ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ማዕቀቦች ቢጣሉባትም፣ አሁንም ነዳጇን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ችላለች። አብዛኛውን የምትሸጠው ለቻይና እና ለህንድ ሲሆን ነዳጁ ለገበያ የሚቀርበውም በቅናሽ ዋጋ ነው።
'ሴንተር ፎር ሪሰርች ኦን ኤነርጂ ኤንድ ክሊን ኤር' የተሰኘው ቲንክ ታንክ መረጃ እንደሚያሳየው ሩሲያ ከምታመርተው ድፍድፍ ነዳጅ ውስጥ ግማሽ ያህሉ የሚቀርበው ለቻይና ነው፤ የሕንድ ድርሻ ደግሞ 37% ገደማ ይደርሳል።
ትራምፕ ከሩሲያ ነዳጅ ለመግዛት የተደረሰውን ስምምነት ይፋ ካደረጉ እና ከፑቲን ይልቅ ከዜሌንስኪ ጋር "መስራት ይበልጥ ከባድ ነው" ካሉ በኋላ በአውሮፓ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት የዩክሬኑ መሪ ዜሌንስኪ፣ "እውነተኛ መሪዎች" መካከል መሆን መልካም ነገር እንደሆነ ተናግረዋል።
ዜሌንስኪ ሩሲያ ጦርነትን የምትመራበትን የገንዘብ አቅም ለመገደብ የሚያስችሉ ጥብቅ ማዕቀቦች እንዲጣሉ በተደጋጋሚ ሲጎተጉቱ ቆይተዋል። ከሰሞነኛው የአሜሪካ እርምጃ በኋላ ግን የትራምፕ አስተዳደር ሩሲያ ላይ የተጣሉ ተጨማሪ ማዕቀቦችን ያነሳል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።
ዩክሬን አጋር የሆኑ የአውሮፓ አገራትም በተመሳሳይ በኢራን ጦርነት ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረውን የአሜሪካ የኤነርጂ ዋጋ ለመቀነስ ሲባል ከሩሲያ ነዳጅ ለማስገባት ያለመውን የትራምፕ ዕቅድ ተችተዋል።