ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ ኤለን መስክ ለዩክሬን የሚያቀርበው የኢንተርኔት አገልግሎት ዳግም መጀመሩን አስታወቁ
የኤለን መስክ ንብረት የሆነው ስታርሊንክ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ የኪዬቭ ጦር ኃይሎችን እንቅስቃሴ ካስተጓጎለ በኋላ ዶናልድ ትራምፕ አገልግሎቱ በዩክሬን ተመልሷል አሉ።
ትራምፕ ይህን ያሉት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ወታደራዊ ክፍሎችን የሚያገናኘው የኤለን መስክ ስታርሊንክ አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ አልተመለሰም ካሉ በኋላ ነው።
መስክ ዩክሬን የድሮን ጥቃቶችን ለመፈፀም እና ከሩሲያ ጥቃቶች ራሷን ለመከላከል የሚያስችላት አገልግሎት ከመቋረጡ ጀርባ እንደሌሉበት ተናግረዋል።
ትራምፕ መስክ አገልግሎቱን እንዲያስጀምሩ ስልክ መደወላቸውን በሚመለከት በወጣው ዘገባ ላይ መመለስ ባይፈልጉም፤ "የመጨረሻው ነገር ዳግም አስጀምሮታል" ሲሉ በተዘዋዋሪ ተናግረዋል።
የትራምፕ አስተዳደር የመስክ ኩባንያ አገልግሎቱን እንዲያቋርጥ መመሪያ መስጠቱን ቀደም ብሎ አስተባብሏል።
የኢንተርኔት አገልግሎት እቀባው የመጣው ትራምፕ ዜሌንስኪ በሩሲያ የነዳጅ ማጣሪያዎች ላይ የሚፈፅሙትን ጥቃት እንዲያቆሙ ጫና እያደረጉ በነበረበት ወቅት ነው።
ትራምፕ ኪዬቭ በሩሲያ የነዳጅ ማጣሪያዎች ላይ የምትፈፅመው ጥቃት የነዳጅ ዋጋ እንዲያሻቅብ አድርጓል በሚል ይሞግታሉ።
በሚቀጥለው ወር የአጋማሽ ዘመን ምርጫ የሚጠብቃቸው ትራምፕ ሩሲያ ላይ ተጥለው የነበሩ ማዕቀበችን ያላሉ ሲሆን፤ ከሩሲያ ነዳጅ ለመግዛትም ተስማምተዋል። ይህ እርምጃቸው በዩክሬን እና በአውሮፓውያን አጋሮቻቸው ዘንድ ትችት ገጥሞታል።
ዩክሬን ለሲቪሊያን አገልግሎት የሚውል ስታርሊንክ እና ለወታደራዊ ግንኙነት ደግሞ ደኅንነቱ የተጠበቀው 'ስታርሽልድ' የተባለ የኢንተርኔት አገልግሎት አቅርቦትን ትጠቀማለች።
አገልግሎቱ 10 ሺህ ሳተላይቶችን በመጠቀም በተለይም ከመደበኛ አገልግሎት ራቅ ባሉ አካባቢዎች እና ለጦርነት ግንባሮች ግንኙነትን የሚያቀርብ ነው።
ሐሙስ ዕለት ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ የዩክሬን ወታደራዊ ኃይል ስርዓት ላይ የአገልግሎቱ ፍጥነቱ ሙሉ ለሙሉ እንዳልተመለሰ ተናግረው ነበር።
"የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን [ማርኮ ሩቢዮ] እየጠበቅኩ ነው። በ48 ሰዓታት ገደማ መረጃ ሊሰጡኝ ቃል ገብተዋል" ብለዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ይህን አስተያየት ከሰጡ በኋላ ዎል ስትሪት ጆርናል ወዲያው ትራምፕ ወደ መስክ ስልክ ደውለው ለዩክሬን የሚያቀርበው ኢንተርኔት ላይ የተጣለውን እቀባ እንዲያነሱ መጠየቃቸውን ዘግቧል።
ከዚህ የስልክ ልውውጥ በኋላ ሐሙስ ዕለት የኢንተርኔት ግንኙነቱ በመደበኛነት እየሰራ መሆኑንም መገናኛ ብዙኃኑ አክሏል።
ቢቢሲ የዎል ስትሪት ጆርናልን ዘገባ አላረጋገጠም። ማብራሪያ በመፈለግም ዋይት ሐውስ እና ስፔስኤክስን ጠይቋል።
ዩክሬን አሜሪካ የምታጋራትን የደኅንነት መረጃዎች ማቋረጧን በመጀመሪያ ይፋ ያደረገችው ጥቅምት መጀመሪያ ላይ ነበር።
ባለፈው ሳምንት መስክ ለወታደራዊ ተልዕኮዎች የሚውለው የስታርሊንክ አካል የሆነው የስታርሽልድን አገልግሎት በበላይነት አሜሪካ መንግሥት እንደሚቆጣጠረው ተናግረዋል። ዩክሬን የስታርሽልድን አገልግሎት ለአንዳንድ ወታደራዊ ተልዕኮዎቿ ትጠቀማለች።
መስክ ስርዓቱ ለአሜሪካ ጦር መስሪያ ቤት ፔንታጎን የተሰራ መሆኑን ጠቅሰው ከእቀባው ጀርባ የጦር መስሪያ ቤቱ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።
ዋይት ሐውስ በተደጋጋሚ የአገልግሎት እገዳውን ትዕዛዝ እንዳልሰጠ ተናግሯል።