መከሰስ አለባቸው የተባሉት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሥልጣን እንደማይለቅቁ አስታወቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በፍርድ ቤት እንዲከሰሱ ጫና የበረታባቸው የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ሥልጣን እንደማይለቅቁ አስታወቁ።
ከሰሞኑ ይፋ የተደረገውን እና የአገሪቱ ምክር ቤት ፕሬዝዳንቱ እንዲከሰሱ የሚያደርግበትን ውሳኔ በፍርድ ቤት እንደሚታገሉም ገልጸዋል።
ራማፎሳ "እዚሁ ነው የምቆየው፤ ሥልጣን አልለቅም" ብለዋል።
በአውሮፓውያኑ 2022 የደቡብ አፍሪካ ምክር ቤት ራማፎሳ እንዳይከሰሱ የጣለው ዕገዳ የአገሪቱን ሕገ መንግሥት የጣሰ እንደሆነ በፍርድ ቤት መወሰኑን ተከትሎ ፕሬዝዳንቱ ከሥልጣን እንዲወርዱ ተጠይቋል። የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ራማፎሳ እንዲከሰሱ የሚያስችል ነው።
በደቡብ አፍሪካ ገጠራማ አካባቢ ከሚገኝ የራማፎሳ መኖሪያ ቤት ሶፋ ሥር የተደበቀ 580,000 ዶላር መሰረቁ የተገጸው በ2022 ነበር። ዝርፊያውን ተከትሎም ፕሬዝዳንቱ ጥያቄዎች ሊቀርቡላቸው እንደሚገባ ገለልተኛ ቡድን አስታውቋል።
ፕሬዝዳንቱ ከቤታቸው የተዘረፈው ገንዘብ ከየት እንደተገኘ አለማሳወቃቸው ውዝግብ አስነስቷል። ራማፎሳ ግን ያልተገባ ድርጊት አለመፈጸማቸውን ገልጸዋል። ገንዘቡ የተገኘው ሕጋዊ ከሆነ የቀንድ ከብት ንግድ መሆኑንም ተናግረዋል።
በወቅቱ ራማፎሳ ላይ ክስ ለመመሥረት የቀረበውን ሐሳብ የአገሪቱ ምክር ቤት በሰጠው ድምጽ ውድቅ አድርጎታል።
ራማፎሳ የሚመሩት 'አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ' (ኤኤንሲ) የተባለው ፓርቲ በወቅቱ በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ አግኝቶ ነበር።
የደቡብ አፍሪካ የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት በበኩሉ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንቱ እንዲከሰሱ በማድረግ ጉዳዩ በጥልቅ መመርመር እንዳለበት ባለፈው ሳምንት ውሳኔውን አሳልፏል።
ራማፎሳ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን በድጋሚ እንዲያጤን እና ውሳኔውን እንዲቀለብስ እንደሚጠይቁ ገልጸዋል። ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያሳለፈው "በስሚ ስሚ መረጃ ላይ ተመሥርቶ ነው" ብለዋል።
ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት የወሰዱት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ጁሊየስ ማሌማ ፓርቲ የሆነው 'ኢኮኖሚክ ፍሪደም ፋይተርስ' (ኢኤፍኤፍ) እንዲሁም ሌሎች አካላት ናቸው።
የፖለቲካ ተንታኝ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ካላንድ እንደሚናገሩት፤ ፕሬዝዳንቱ እንዲከሰሱ በምክር ቤት ድምጽ ሊሰጥባቸው የሚችልበት ዕድል ጠባብ ቢሆንም፤ ክስ የሚመሠርትባቸው ከሆነ የሥልጣን ዘመናቸው እና ክብራቸውን የሚያጠለሽ ይሆናል።














