ደቡብ አፍሪካ መጤ ጠል ጥቃቶችን ያሳያሉ የተባሉ 'ሐሰተኛ ቪዲዮዎችን' አወገዘች

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በውጭ ዜጎች ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶችን ያሳያሉ ተብለው የተለቀቁ "የሐሰተኛ ቪዲዮዎች እና ምስሎች" አውግዟል።
ይህ የተባለው በአገሪቱ ውስጥ መጤ ጠል ጥቃቶች እየተባባሱ ነው በሚል በደቡብ አፍሪካ እና በሌሎች የአፍሪካ አገሮች መካከል ያለው የዲፕሎማሲ ውጥረት እየጨመረ በመጣበት ወቅት ነው።
በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ አፍሪካውያን ደኅንነት "ከባድ አደጋ" ላይ ወድቋል ያለው የጋና መንግሥት የአፍሪካ ህብረት በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት እንዲያካሂድ ጠይቋል።
ናይጄሪያም ጥቃት እንዳይፈጸምባቸው የሰጉ ዜጎቿን ወደ አገራቸው ለመመለስ ቃል ገብታለች።
ኬንያ፣ ማላዊ፣ ሌሶቶ እና ዚምባብዌ በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ዜጎቻቸው ጥቃቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ በመግለጽ አስጠንቅቀዋል።
ደቡብ አፍሪካ "የምትደብቀው ነገር እንደሌለ" በመግለጽ ለጋና መልዕክት ምላሽ ሰጥታለች።
ይህ የጫና የተቀሰቀሰው ከሁለት ሳምንት በፊት በደቡብ አፍሪካ ህገወጥ በሆነ መንገድ እንደገቡ በሚታመኑ ሰዎችንላይ በቡድን የተደራጁ ሰዎች ጥቃት ሲፈጽሙ የሚያሳይ ነው የተባለ ቪዲዮ በበይነ መረብ ከተጋራ በኋላ ነው።
በአንደኛው ቪዲዮ ላይ አንድ ጋናዊ የመኖሪያ ፈቃዱን ከተጠየቀ በኋላ ተመልሶ "አገሩን እንዲያቀና" ሲነገረው ያሳያል።
ሐሙስ ዕለት ከተካሄደ የካቢኔ ስብሰባ በኋላ ለመገናኛ ብዙኃን ሃሳባቸውን የገለጹት የፕሬዚዳንቱ ሚኒስትር ኩምቡድዞ ንሻቭሄኒ ስለየትኛው ቪዲዮ እየተናገሩ እንደሆነ በትክክል ሳይገልጹ "የሐሰት ቪዲዮዎች እና ምስሎች የውሸት ብቻ ሳይሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ የደቡብ አፍሪካን መልካም ስም ለማጥፋት እና አገሪቱ የተሻለ የአፍሪካ አጀንዳ ለማግኘት ያላትን ፍላጎት ለማዳከም የታሰቡ ናቸው" ብለዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ደቡብ አፍሪካውያን ከቅርብ ቀናት ወዲህ በዋና ዋና ከተሞች ሕገ-ወጥ ስደትን በመቃወም ድምጻቸውን እያሰሙ ሲሆን ህገ ወጥ ስደተኞች ከአገር እንዲባረሩም ጠይቀዋል።
ህገ ወጥ ስደቱ በሥራ፣ በመኖሪያ ቤት እና በወንጀል ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ተቃዋሚዎች ተናግረዋል።
ንሻቭሄኒ ሰልፎቹን በተመለከተ ባደረጉት ንግግር ደቡብ አፍሪካውያን "እየተባባሰ የመጣውን የሕገ ወጥ ስደትን ተግዳሮት" መቃወም መብታቸው እንደሆነ ቢናገሩም፤ ከዚህ በፊት ከተደረጉ ተቃውሞዎች ጋር የተያያዘው ዓመፅ ተቀባይነት እንደሌለው አክለዋል።
መጤ ጠልነት (ዜኖፎቢያ) በደቡብ አፍሪካ ለረጅም ጊዜ ችግር ሆኖ የቆየ ሲሆን አልፎ አልፎም እስከ ሞት የሚደርሱ ጥቃቶች ይፈጠራሉ። የአሁኖቹ ተቃውሞዎች በአብዛኛው ሰላማዊ የነበሩ ሲሆን የውጭ አገር ዜጎች ሱቆች መዝረፍ ወይም በሰነድ አልባ ስደተኞች ላይ የሚፈጸም ጥቃትን በተመለከተ ይፋዊ ሪፖርቶች የሉም።
የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ እየጨመረ የመጣውን የፀረ-ስደት ስሜት ተከትሎ በአህጉሪቱ እየጨመረ የመጣውን ስጋት ለማርገብ የዲፕሎማሲ ጥረቶችን ሲያጠናክር ቆይቷል።
ጋና ለአፍሪካ ህብረት በጻፈችው ደብዳቤ ላይ በደቡብ አፍሪካ ያለው ዜኖፎቢያ "ለአፍሪካ አንድነት፣ ወንድማማችነት እና ለአህጉራዊ አንድነት የጋራ መርሆዎች ፈተና ነው" ብላለች። የእውነታ አጣሪ ቡድን ወደ አገሪቱ እንዲላክም ትፈልጋለች።
ረቡዕ ዕለት የፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ቃል አቀባይ "ደቡብ አፍሪካ እንግዳ ተቀባይ ሀገር መሆኗን አፅንኦት ሰጥተዋል። ደቡብ አፍሪካውያን እንግዳ ተቀባይ፣ ወዳጅ እና ተግባቢ ሕዝቦች ናቸው። እናም ይህችን አገር ወይም ህዝቦቿን እንደመጤ ጠል አድርጎ ለመሳል የሚፈልግ ማንኛውንም ሃሳብ ውድቅ እናደርጋለን።"
ንሻቭሄኒ ሐሙስ ዕለት የጋናን ደብዳቤ በመጥቀስ ፕሬዚዳንቱን ሃሳብ በማስተጋባት "በደቡብ አፍሪካ ምንም አይነት የውጭ ዜጎች ጥቃት አልደረሰም" ብለዋል።
የውጭ ዜጎች በአጠቃላይ የወንጀል ድርጊት ሰለባዎች እንደሆኑ ቢያሙንም ግን ይህን ፖሊስ መቋቋም ያለበት መሆኑን ጠቅሰዋል።














