በኤአይ የተዘጋጁ ምሥሎችን በማየት መለየት ይችላሉ? እንዴት መለየት እንደሚቻል እንጠቁምዎ

የሥነ ልቦና ባለሙያዋ ዶ/ር ክሌር ሰዘርላንድ ሁለት ትላልቅ ፎቶዎችን ይዘዋል። በአንዱ ምሥል ላይ ዓለም አቀፍ የምርምር ጥናት እየመሩ ያሉ የአውስትራሊያዊ ምሁር ፊትን ያሳያል፤ ሌላኛው ደግሞ በሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) የተዘጋጀ የ'ዲፕፌክ' ምሥል ነው።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት እውነተኛ የሚመስሉ ምሥሎችን መፍጠር ላይ የተካነ እየሆነ ነው። ከጊዜ ወደ ጊዜም የትኛው እውነት፤ የትኛው ፈጠራ ነው የሚለውን መለየት አስቸጋሪ እየሆኑ መጥቷል።
ታዲያ ሰዎች በማሽን የተሠራ የሰው ምሥልን መለየት እንዲችሉ ማሠልጠን ይቻላል?
በአበርዲን ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩት ሰዘርላንድ እና አውስትራሊያዊት ባልደረባቸው ለመመለስ ሲጥሩ የነበረው ይህንን ጥያቄ ነው።
ትክክለኛውን ከመንገራችን በፊት ይህንን ፈተና መውሰድ ይጠበቅቦታል። ምን ያህል እንዳገኙ መመዝገብ እንዳይዘነጉ።
ይህን ፈተና አስቸጋሪ ከሆነብዎት፤ አይጨነቁ። ብቻዎች አይደሉም።
ከዚህ ቀደም ብዙውን ጊዜ አጭበርባሪዎች የሚጠቀሙባቸውን በኮምፒውተር የተፈጠሩ ምሥሎች መለየት እጅግ የቀለለ ነበር። ምክንያቱም ኤአይ ስድስተኛ ጣት ወይም ሌላ ግልጽ የሆነ እንግዳ ነገር ምሥሉ ላይ በማካተት ስህተቶችን ይሠራ ነበር።
ነገር ግን ኤአይ ከስህተቶቹ ይማራል።
ፕሮፌሰር ኤሚ ዳዌል፤ ምሥሎቹ ላይ "እንደ ስድስተኛ ጣት ወይም ግራ አጋቢ የጆሮ ጌጦችን ያሉ ነገሮችን መፈለግ የሚያስገኘው ስኬት ውስን ነው። አንዱ ምክንያት ኤአይ በጣም ጥሩ እየሆነ ነው፤ አጭበርባሪዎችም ግልጽ የሆነ ስህተት የሚታይባቸው ምሥሎችን ከመጠቀም ይቆጠባሉ" በማለት ያብራራሉ።
ፕሮፌሰር ዳዌል ማለት የሁለት ሰዎች ምሥል በተያዘበት የመጀመሪያው ፎቶ ላይ የሚታዩት ሴት ናቸው። የተያዘው ሌላኛው የወንድ ምሥል ሐሰተኛ ነው።
ፕሮፌሰሯ የአውስትራሊያ ናሽናል ዩኒቨርሲቲ የስሜቶች እና የፊቶች ላብራቶሪ ዳይሬክተር ናቸው። ትክክለኛ የሚመስሉ ኤይ ምሥሎችን መለየት ይቻል እንደሆን ለማወቅ የሚሠራውን እና በአውስትራሊያ፣ በካናዳ እና በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙ ተመራማሪዎችን የያዘውን ቡድን ሲመሩ ቆይተዋል።
ቢያንስ አሁን ላይ ባለው ሁኔታ መልሱ "አዎ፤ ሰዎችን ማሠልጠን ይቻላል" የሚል ሆኗል። ሰዎች በኤአይ የተሠሩ ሐሰተኛ ምሥሎችን እንዲለዩ ማሠልጠን ግን ከተለመደው ወጣ ያለ አካሄድን ይጠይቃል።
ሐሰተኛ ምሥሎችን በቀልብ መለየት
ዶ/ር ሰዘርላንድ መቀመጫውን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረገውን የአበርዲን ዩኒቨርሲቲ ምርምር ይመራሉ።
በጊዜ ሂደት ምሥሎችን በመመልከት ብቻ የትኛው እውነተኛ፤ የትኛው በኤአይ የተሠራ እንደሆነ ቀልባቸው ይነግራቸው እንደጀመር ያስረዳሉ።
"ስለዚህ ምን አሰብን? እሺ፤ ይህንን ነገር ለሌሎች ሰዎች ማስተማር ከቻልን በጣም ጥሩ ነገር ይሆናል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ይህንን ሙከራ ለማድረግ የተጠቀሙት እጅግ እውነተኛ የሚመስሉ ፊቶችን ለመፍጠር ተመራጭ ከሆኑት የኤአይ መገልገያዎች አንዱ የሆነውን 'ስታይልጋን3' ነው። በዚህ መሣሪያ አማካኝነት በሺህዎች የሚቆጠሩ ማሽን ሠራሽ የፊት ምሥሎችን አዘጋጁ።
ከዚያም የጥናቱ ተሳታፊዎች ሥልጠና ሳይሰጣቸው በፊት እና ከተሰጣቸው በኋላ ምሥሎቹን ለመለየት እንዲሞክሩ ተደረገ።
ምን እንዲመለከቱ ነበር የሰለጠኑት?
ተመራማሪዎቹ የጥናት ተሳታፊዎቹን ያሠለጠኗቸው ትኩረታቸው በስድስት የመገንዘብ ብቃቶች ላይ እንዲሆን በማድረግ ነበር።
የቅርፅ ልክነት (Symmetry) - ብዙውን ጊዜ ኤአይ ሰው የሚያደርጉን ትናንሽ መዛነፎች መፍጠር አይችልም። በትንሹ ዝቅ ያለ የዐይን ሽፋሽፍት ወይም ወደ አንድ ወገን ያጋደለ ፈገግታ በምሳሌነት መጠቀስ ይችላሉ። "ነገሩ እውነት ለመሆን እጅግ የራቀ ከሆነ፤ ምናልባት እውነት አይደለም"
- ተመጣጣኝነት - ይህም ተመሳሳይ ሀሳብ ነው። ትልቅ አፍንጫ ወይም ወጣ ብለው የሚታዩ ጆሮዎች ብዙውን ጊዜ ዲፕፌክ ምሥሎች ላይ አይታዩም።
- ማራኪነት - ዶ/ር ሰዘርላንድ "የኤአይ ፊቶች በጣም ማራኪ ናቸው" ይላሉ። "የውበት መመዘኛ በአብዛኛው ግላዊ ጉዳይ ቢሆንም፤ ብዙውን ጊዜ ኤአይ የሚፈጥራቸው ፊቶች የሚስብ ገጽታ ያላቸው ናቸው" በማለት ያብራራሉ።
- መለያ ገጽታ - "ይህ ማለት 'አንድን ፊት ከብዙ ሰዎች መካከል የተለየ የሚያደርገው ምንድነው?' ኤአይ የሚሠራቸው ፊቶች ወደ ተለመዱ የፊት ገጽታዎች የማዘንበል ባህሪ አላቸው። ስለዚህ የተለመደ ገጽታ ያላቸው ይመስላሉ" ሲሉ ባለሙያዋ ያስረዳሉ።
- ስሜት ገላጭነት - ዶ/ር ሰዘርላንድ "የኤአይ ፊቶች ብዙም ስሜት የማይታይባቸው ይመስላሉ። ብዙ ስሜት ያለማሳየት ዝንባሌ አላቸው" ይላሉ።
- ትውስታ ውስጥ መቅረት - "ብዙውን ጊዜ አእምሮ ውስጥ የሚቀሩ አይደሉም፤ ለማስታወስ አስቸጋሪ ናቸው።"
በተጨማሪም ኤአይ የቆዳ ቀለማቸው ነጭ ያልሆኑ፣ የአዛውንት ወይም የታዳጊዎች ፊቶችን መሥራት ላይ እጅግ የተካነ አይደለም። ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ማሽኖች የሚሰለጥኑት ነጭ ወጣቶች ነው።
እነዚህ የኤአይ ምሥልን ለመለየት የተሰጡ ምክሮች የተለመዱ እና ግልፅ ያልሆኑ ሊመስሉ ይችላሉ፤ ዋናው ጉዳይም ግን እንዲህ መሆናቸው ነው።

የፎቶው ባለመብት, Nightingale
አንድ የኤአይ ሐሰተኛ ምሥልን በእርግጠኝነት ለመለየት የሚያስችሉ ምልክቶች እምብዛም አይገኙም። ይልቁንም መፍትሔው ስለ ኤአይ ምስሎች ባህሪያት መረዳት እና ቀልብን ማሰልጠን ነው።
ተመራማሪዎቹ እንደሚናገሩት፤ ሰዎች በኤአይ የተሠሩ እና እውነተኛ ምሥሎችን በተደጋጋሚ እንዲመለከቱ ማድረግ፤ እንዲሁም የትኛው ትክክል፣ የትኛው ሐሰት እንደሆነ ማስረዳት፤ የሐሰት ምሥሎችን የመለየት ችሎታቸው በከፍተኛ መጠን እንዲያድግ ያስችላል።
ተሳታፊዎች በአንድ ሰዓት ገደማ ጊዜ ውስጥ የተሻሻሉባቸው አጋጣሚዎች እንዳሉም ተመራማሪዎቹ ገልጸዋል።
ይህንን በማድረግ የጥናቱ ተሳታፊዎች በትክክል የመለየት ብቃታቸው ከ40 እስከ 80 በመቶ እንደሚያድግ ተመራማሪዎቹ ደርሰውበታል።
ጥቂት ሰዎች እንዲያውም ለ100 ፐርሰንት የተጠጋ ትክክለኛነት ላይ ደርሰዋል።
በሚያስገርም ሁኔታ፤ የሰው ልጅ አእምእሮ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚከተለው ዘዴ፤ የተለያዩ ነገሮችን የሚፈጥሩ ኤአይ ሞዴሎች ከሚሠሩበት መንገድ ጋር ተመሳሳይ ነው።
የኤአይ ሞዴሎች የሚሠለጥኑበት በቂ መረጃ ሲሰጣቸው፤ ምንም እንኳ እንዴት እያደረጉት እንደሆነ ሙሉ በሙሉ ባንረዳውም በጊዜ ሂደት ትክክለኛነታቸው ይጨምራል።
በተጨማሪም ተመራማሪዎቹ፤ ተሳታፊዎች የኤአይ ምሥሎችን መለየት ላይ ምን ያህል በራስ መተማመን እንደሚታይባቸው አጥንተዋል።
ከዚህ ቀደም የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሰዎች በኤአይ የተሠሩ ፊቶችን የመለየት አቅማቸው ላይ ያላቸመው መተመማን ከመጠን በላይ ነበር። እጅግ በራሳቸው የሚተማመኑት ሰዎች ብዙ ስህተት ሲሠሩም ተገኝተዋል።
ከሥልጠናው በኋላም ተሳታፊዎቹ ሐሰተኛ ምሥሎችን መለየት ላይ ያላቸው በራስ መተማመን ጨምሮ ታይቷል።
ይህ ጥሩ ነገር እንደሆነ ዶ/ር ሰዘርላንድ ይናገራሉ። "ምክንያቱም ትክክል ስትሆንም ስትሳሳትም የማታውቅ ከሆነ ያንን መረጃ ምንም ልታደርገው አትችልም" ይላሉ።
ታዲያ አሁን ሌላ ፈተና ለመውሰድ ዝግጁ ነዎት?
ውጤትዎ እንዴት ሆነ? በራስ መተማመን ተሰምቶዎታል?
ምላሹ 'አልተሰማኝም' ከሆነ ራስዎን ማስጨነቅ አይገባም። በሰዎች እና በኤአይ ዓለም ውስጥ ወደ ፍጹምነት የሚያስጠጋው ተደጋጋሚ ልምምድ ነው።
ኤአይ ምሥሎችን የመለየት ብቃትዎን ማሳደግ የሚሹ ከሆነ የሚለማመዱባቸው በርካታ ድረ ገጾች አሉ። ከፈለጉም የዚህ ጥናት አካል መሆን ይችላሉ።
ለምን የኤአይ ሐሰተኛ ምሥሎችን መለየትን መማር ያስፈልጋል?
ግልጹ እና ቀላሉ መልስ፤ የመጭበርበር አደጋ ስላለ ነው።
ዓለም አቀፉ አማካሪ ኩባንያ 'ዲሎይት' እንደተነበየው ከሆነ በሚቀጥለው ዓመት ውስጥ በኤአይ ዲፕፌክ ማጭበርበሮች አሜሪካ ውስጥ ብቻ የሚደርሰው የገንዘብ ኪሳራ 2023 ከነበረበት 12 ቢሊዮን ፓውንድ ወደ 40 ቢሊዮን ፓውንድ ሊያድግ ይችላል።
በሆንግ ኮንግ በሚገኝ አንድ ኩባንያ የሚሠራ አንድ ሠራተኛ አለቃውን ከሚመስል ዲፕፌክ ምሥል ጋር የቪዲዮ ጥሪ ውይይት ካደረገ በኋላ 25 ሚሊዮን ፓውንድ ለአጭበርባሪዎች እንደላከ የዲሎይት ሪፖርት ላይ ተጠቅሷል።
የዲፕፌክ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችልበት ሌላኛው አስከፊ መንገድ ፖለቲካዊ ስለላ ነው።
የዜና ወኪሉ አሶሺዬትድ ፕሬስ ከሰባት ዓመት በፊት በአውሮፓውያኑ 2019 ራሷን ከታዋቂ የዋሽንግተን የጥናት ተቋማት እና የፖሊሲ ክበቦች ጋር ግንኙነት እንዳላት እንዲሁም የሩሲያ ጉዳዮች ባለሙያ እንደሆነች በገለጸች ኬቲ ጆንስ የተባለች ሴት የሊንክድኢን ገጽ ላይ ምርመራ አድርጎ ነበር።
የኬቲ ጆንስ ፎቶ እና የሊንክድኢን አካውንት በሙሉ ሐሰተኛ ሆኖ ተገኝቷል።
የኤፒ ምርመራ እንደሚያሳየው፤ ይህቺ በሩሲያ የስለላ ድርጅት የተፈጠረች ዲፕፌክ ከአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ረዳቶች እና ከብሔራዊ ደኅንነት ባለሥልጣናት ጋር በተሳካ ሁኔታ ግንኙነት መፍጠር ችላለች።

የፎቶው ባለመብት, Linkedin
አኤይ ግን መጥፎ ነገር ብቻ ይዞ አልመጣም። የቴክኖሎጂው የሚያስገኛቸው አዎንታዊ ጥቅሞችምን የሚያነሱት ዶ/ር ሰዘርላንድ፤ ኤአይን በመጠቀም ከረጅም ጊዜ በፊት የጠፋ ልጅ በተለያዩ ዕድሜ ክልሎች ውስጥ ምን ሊመስለ እንደሚችል በፍጥነት እና በአነስተኛ ዋጋ መሥራት እንደሚቻል ይጠቅሳሉ።
ሰዎች "በቅን ልቦና የሚጠቀሙበት ከሆነ ለፈጠራ ሥራዎች እጅግ በጣም ጠቃሚ" ሊሆን እንደሚችል ያክላሉ።
ጥሩው ዜና፤ ቢያንስ አሁን ባለው ሁኔታ እውነታውን እና በኮምፒውተር የተፈጠረውን መለየት የማንችልበት ዓለም ውስጥ አለመሆናችን ነው።
መጥፎው ዜና ደግሞ፤ የኤአይ ሞዴሎች እንዴት ሐሰተኛ ምሥሎችን መለየት እንደሚቻል የሚያሳዩትን ጨምሮ ተያያዥ የጥናት ውጤቶችን "አንብበው" ሊሆን ይችላል። እናም ራሳቸውን ለማሻሻል እየተማሩ ነው።















