'ቤተሰቦቼ ከሞትኩ በኋላ መርዶ ቢነገራቸው ይሻላል' - በሳዑዲ እስር ቤቶች የሞት ቅጣት የሚጠባበቁት ኢትዮጵያውያን

የፎቶው ባለመብት, family
- ፀሐፊ, አክሊሉ ጸጋይ
- የሥራ ድርሻ, ቢቢሲ ትግርኛ
- ታትሟል
- የንባብ ጊዜ: 9 ደቂቃ
ክብሮም ወደ ስደት ሲሄድ ገና የ16 ዓመት ታዳጊና የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነበር።
ከሃገሩ ለመሰደድ የተገደደውም በህወሓት እና በፌዴራል መንግሥት መካከል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ሸሽቶ ነው።
"በ2013 ከትግራይ ምሥራቃዊ ዞን እገላ ከምትባለው ወረዳ ትምህርቱን አቋርጦ ወደ ስደት አቀና" ይላል በትግራይ የሚኖረው የአጎቱ ልጅ መብራህቶም አለማ።
የመን ውስጥ ጥቂት ወራትን አሳልፎ ወደ ሳኡዲ አረቢያ ሲደርስ ብዙም ሳይቆይ ተያዘ። በወቅቱ ቤተሰቡ ከየመን ወደ ሳዑዲ አረቢያ እየተሻገረ እንደሆነ የሚገልጹ መልዕክቶች ይደርሳቸው ነበር። በሳዑዲ አረቢያ በሚገኙ ዘመዶች አማካኝነት ነበር ስላለበት ሁኔታ መረጃ የሚደርሳቸው።
የመን ውስጥ እያለ "ወደ ሳዑዲ አረቢያ ስደርስ እደውላለሁ" ብሎ የነበረ ቢሆንም ከዛ በኋላ ግን ድምጹ ጠፋ። ረዥም ግዜ ከጠበቁ በኋላ እንደታሰረ ሰሙ። ከታሰረ ከ3 ዓመታት በላይ አልፎት ነበር።
"እስር ቤት ሆኖ በተለይ ስለ ቤተሰቡ ደኅንነት ይጠይቀኝ ነበር። በተለይ ታላቅ ወንድሙ እርሱን ተከትሎ ወደ ስደት አምርቶ የመን ከገባ በኋላ እስር ቤት ሆኖ ስለሱ ይጨነቅ ነበር" ሲል የአክስቱ ልጅ ተስፋይ ከሳዑዲ አረቢያ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ወንድሙ ወደ የመን ሲገባ ክብሮም በእስር ቤት ሁለት ዓመታት አሳልፎ ነበር። ስደተኞች ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመሻገር በሚሰባሰቡበት ቦታ ወንድሙ በየመን ታጣቂዎች ተገድሏል። ክብሮም የወንድሙን ሞት በእስር ቤት ሲሰማ ጭንቀቱ በመራራ ሀዘንና ቁጭት ተተካ።
ከባዱ መርዶ
ክብሮም በሳዑዲ አረቢያ ከሚገኘውን የአጎቱን ልጅ ጋር ሲደዋወል "አሁን እዚያ ለሦስት ዓመታት ስለቆየን ሊፈቱን ይችላሉ። ቢያቆዩንም ራሱ ለአንድ ዓመት ነው" በማለት በተስፋ ይናገር ነበር።
የሞት ፍርድ እንደተፈረደበት የነገራቸው በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ለነበሩት አንዳንድ ጓደኞቹ እና እስር ቤት ውስጥ ላሉ ብቻ ነበር። ለቤተሰቦቹ ግን እንዳይጨናነቁ በማሰብ የእስር ግዜውን ጨርሶ እንደሚፈታ ነበር የሚነግራቸው።
"ተይዞ ሲታሰር እዚህ አገር ውስጥ ወላጆቹን እና ዘመዶቹ አናገኘውም። ነገር ግን በሳዑዲ አረቢያ ካሉ ሌሎች ዘመዶቻችን ጋር ይገናኝ ነበር። ስንጠይቃቸው 'እያገኘነው ነው፤ ይለቀቃል' ይሉን ነበር" ይላል የአጎቱ ልጅ መብራህቶም።
የሞት ፍርዱ ከመፈጸሙ ከሁለት ሳምንታት በፊት ሳዑዲ አረቢያ ወደሚገኘው የአክስቱ ልጅ ተስፋይ ደውሎ ለመጨረሻ ጊዜ ተነጋገሩ።
ሁልጊዜ እንደሚለው በአጭሩ "ደህና ነኝ" ካለ በኋላ እሱን ተከትለው ወደ ሳዑዲ አረቢያ ስለገቡት ሌሎች ታናናሽ ወንድሞቹ ሁኔታ መጠየቅ ጀመረ።
ያኔ በስልክ 'አደራ ተባበራቸው፤ ተከታተላቸው። ሥራ እንዲያገኙ አግዛቸው' እንዳለው ተስፋይ ይገልጻል።
"በተገደለበት ቀን ዋዜማ እዚህ ሳዑዲ አረቢያ ወደ ሚገኝው ሌላ የአጎቴ ልጅ ጋር ደውሎ ነበር። እየተጣደፈ ስለ ደኅንነታችን ብቻ ነበር የጠየቀው" የሚለው ተስፋይ ብዙም ሳያወሩ ስልኩን እንደዘጋው ለቢቢሲ ተናግሯል።
በማግስቱ ከሰዓት በኋላ በእስር ቤቱ ውስጥ የነበሩ ሌሎች እስረኞች ወደ ተስፋይ ደወሉ። አሳዛኙን መርዶም ነገሯቸው።
"ፍርዱ ስለተፈጸመ ለቤተሰቡ መርዶውን ንገሯቸው" የሚል ለማመን የሚከብድ ነገር አረዷቸው።
የሳዑዲ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በአሲር ዞን ውስጥ ሦስት ኢትዮጵያውያን በሞት ስለመቀጣታቸው ባወጣው መግለጫ ላይ የሃይማኖት መልዕክቶችን እና የሸሪዓ ሕግን በመጥቀስ የሟቾችን ስም ይዘረዝራል።
"ኪዳኔ አንገሶም ወልዳይ፣ ፊልሞን ሐጎስ ገብረመስቀል እና ክብሮም ገብረማርያም ገብረእግዚአብሔር ወደ ሳዑዲ አረቢያ አደንዛዥ ዕፅ በማዘዋወር ተሳትፈዋል" የሚለው መግለጫው፣ በምርመራ ውጤት መሠረት ወንጀሉን ፈጽመው እንደተከሰሱ ያመለክታል።
በእነርሱ ላይ የቀረበው ክስ ከተረጋገጠ በኋላ ሞት እንደተፈረደባቸው እና በሸሪዓ ሕግ መሠረት ፍርዱ ተፈጻሚ እንዲሆን መወሰኑን በመጥቀስ "የሞት ቅጣቱ ሚያዝያ 13/2018 ዓ.ም. በአሲር ዞን ተፈጻሚ ሆኗል" ይላል።
ክብሮም ወላጆቹን የሚታዘዝ ቅን ልጅ እንደነበር መብራህቶም ይመሰክራል።
በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ሁለት ታናናሾቹ እና በየመን የተገደለው የበኩር ልጅ ጨምሮ አራቱም ወንድማማቾች ወደ ስደት አቅንተው ሁለቱም በወጡበት የጠበቃቸው ሞት ነበር።

የፎቶው ባለመብት, family
በሐዘንና በድንጋጤ የተዋጠችው እገላ
ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት ወላጆችና ዘመዶች አንዳቸውም ልጆቻቸው ከመታሰራቸው በስተቀር የሞት ፍርድ እንደተፈረደባቸው አያውቁም።
በሳዑዲ አረቢያ የሚገኘው ተስፋይ ወደ ክብሮም ወላጆች እየደወለ "ፍርዱ ቀላል ይሆናል፤ የረመዳን ጾም ሲገባ ምህረት ይደረግላቸዋል" ይላቸው ነበር።
ነገር ግን ፍርዳቸው ሲፈጸም የሦስቱም መርዶ በትግራይ ወደምትገኘው እገላ ወረዳ ደረሰ። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ሦስቱም ከዚያች ወረዳ የመጡ ናቸው። ወደ ሳዑዲ አረቢያ የተሰደዱበት ጊዜ ግን የተለያየ ነው።
"መርዶው በተሰማ ጊዜ በእገላ ከፍተኛ ድንጋጤና ሐዘን ተፈጠረ። ምክንያቱም ከአካባቢው ወደ ሳዑዲ አረቢያ የተሰደዱ ብዙ ወጣቶች አሉ።
"በተነገረን መሠረት 'ወደ ፍርድ ቤት ልንወስዳችሁ ነው' በሚል ነው ከእስር ቤት አውጥተው የገደሏቸው" ይላል መብራህቶም።
ሂዩማን ራይትስ ዎች ሚያዝያ 20 ቀን ባወጣው መግለጫ በካሚስ ሙሻይት ስለተያዙና ስለተፈረደባቸው ሦስት ሰዎች መረጃ ያላቸውን ምንጮችን ቃለ መጠይቅ እንዳደረገ አመልክቷል።
ምንጮቹ እንደገለጹት ሚያዝያ 13/2018 ዓ.ም. የሳዑዲ እስር ቤት ጠባቂዎች ሦስት እስረኞችን ጠርተው ወሰዷቸው።
ያኔ ለይተው ሲወስዷቸው ወደ ፍርድ ቤት እንደሚሄዱ ነበር የተነገራቸው። በኋላ ግን የእስር ቤቱ ጠባቂዎች ለሌሎቹ ኢትዮጵያውያን እስረኞች ሦስቱ እንደተገደሉ ገልጸው "ለቤተሰቦቻቸው ንገሩ" ማለታቸውን ዘገባው ያብራራል።
ልጆቻቸው በሳውዲ አረቢያ የታሰሩ ወላጆች ዜናው ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ በከባድ ጭንቀት ውስጥ ይገኛሉ።
"እንዳንጨነቅ አውቀው ደበቁን እንጂ ይገደላሉ" በማለት በከባድ ጭንቀት ውስጥ እንዳሉ መብራህቶም ለቢቢሲ ይገልጻል።

ስደት በሞት መስመር ያገናኛቸው. . .
ሂዩማን ራይትስ ዎች ምንጮችን ጠቅሶ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ እስር ቤቶች ውስጥ እንዳሉ ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።
"ከ200 በላይ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ኢትዮጵያውያን በካሚስ ሙሻይት ታስረው ይገኛሉ" ሲልም ጠቅሷል።
ሞት ከተፈረደባቸው መካከል ከትግራይ ምሥራቅ ዞን የተሰደደው የ31 ዓመቱ ደስታ ይገኝበታል።
በኅዳር 2013 ዓ.ም. የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሲጀመር ሁለት ወንድሞቹና ዘመዶቹ የትግራይ ኃይሎችን ተቀላቀሉ። እሱ ግን ቤት ለመቆየት አሳማኝ ምክንያት ነበረው።
ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነው። በተጨማሪም ወላጆቹንና ሌሎች የቤተሰቡ አባላት የሚያስተዳድር ሌላ ሰው አልነበረም።
ይሁን እንጂ ብሎኬትና ሌሎች የግንባታ ቁሳቁሶችን በማምረት የሚያገኘው ገቢ በቂ አልነበረም። ለእርሱ እና ለልጆቹ እንኳን መሠረታዊ ፍላጎቶች ለማሟላት የሚበቃ ነገር አያገኝም።
በወቅቱ ትግራይ ውስጥ በሚካሄደው ጦርነት ደስታና መላው ቤተሰቡ ከባድ ችግር ውስጥ ተዘፈቁ።
የኤርትራ ወታደሮች ወደ አካባቢው ገብተው "ሰዎችን ሲያሰቃዩና ሲገድሉ" ይመለከት እንደነበር ይናገራል። ይህ ከሌሎች ችግሮቻቸው በተጨማሪ ለደስታ እንቅልፍ የሚያሳጣና የሚያስጨንቅ ነበር።
ሕይወቱን ላለማጣትና ቤተሰቡም ያለ አስተዳዳሪ ከሚቀሩ አንድ ነገር መወሰን ነበረበት።
በ2013 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ ከሌሎች ወጣት ወንዶችና ሴቶች ከሚገኙበት ቡድን ጋር ወደ ሳዑዲ አረቢያ አቀና።
ለ40 ቀናት ጥም፣ ረሃብ፣ ድካም፣ ሕመም እና በሕይወታቸው ውስጥ እጅግ የከፋው ስቃይን ከተጋፈጡ በኋላ የመን ደረሱ።
የ24 ዓመቱ ሃብቶም ሁኔታም ተመሳሳይ ነው።
በ2012 ዓ.ም. የ11ኛ ክፍል ተማሪ ነበር። በወቅቱ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተከስቶ ነበር፤ ብዙም ሳይቆይ የትግራይ ጦርነት ተከተለ። ይህም የሕይወቱን ዓላማ እንዲሰናከል አደረገ።
"ዓላማዬ በመሰናከሉ ተበሳጭቼ ለመሰደድ ወሰንኩ። መጋቢት 9/2013 ከቤት ከወጣሁ ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥም ባሕሩን አቋርጬ ወደ የመን ገባሁ።
"በሐምሌ 2013 በሰንዓ ከተማ ምግብ እየለመንኩ ሳለ አንድ ያልበደልኩት የመናዊ ተኩሶ እጄን አቆሰለኝ። ቁስሌ እስከ ጥር 2014 ድረስ አልዳነም፤ ለምኜ ነው የታከምኩት" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

ወደ ሳዑዲ አረቢያ በሚሻገርበት ወቅት ከሱ ጋር የነበሩ ብዙ ስደተኞች በአገሪቱ ድንበር ጠባቂዎች እንደተገደሉ የሚያስታውሰው ሃብቶም "ለመቀበር ያልታደሉ ሞተው የቀሩ ብዙ ናቸው" ሲል ይጨምራል።
"ከ40 እስከ 50 የምንጠጋ ሰዎች አብረን እየተሻገርን ነበር። ነገር ግን ሲተኮስብን ሕይወታችንን ለማዳን ተበታትነን ሸሽተናል። ማን እንደተረፈ እና ማን እንደሞተ ማወቅ ከባድ ነው። ለቤተሰቦቻቸው መርዶ ያልተነገረ እዛ ተገድለው የቀሩ ሰዎች ብዙ ናቸው።" ብሏል።
በሳዑዲ አረቢያ ለሦስት ወራት ያህል በፍየል እረኝነት ከሠራ በኋላ እሱንና ሌሎችን ቀጥረው ያሰሯቸው ከነበሩት የአካባቢው ነዋሪዎች አንድ ሀሳብ ቀረበላቸው።
'ብዙ ብር የሚያስገኝ ስራ እናሰራችሁ' የሚል ጥያቄ ያቀረቡላቸው ሳዑዲዎቹ፤ ገንዘቡ የሚከፈላቸው ግን የሚሰጣቸውን እቃ አንድ ቦታ ካደረሱ በኋላ እንደሆነ ነገሯቸው። ከዚያም ሃሳቡን ተቀብለው የተሰጣቸውን ዕቃ ተሸክመው እየሄዱ ሳለ በፖሊስ ተያዙ።
"ሳዑዲዎቹ ጥለውን ሸሹ። ምን እንዳሸከሙን እንኳን አናውቅም ነበር። ግን ከዚያ በኋላ ጫት መሆኑን አወቅን። ከዚህ በፊት ጫት የሚባል ነገር አላውቅም ነበር" ይላል።
ሌላው ለቢቢሲ ታሪኩን ያካፈለው ከአማራ ክልል ከራያ ቆቦ ወረዳ የመጣ 37 ዓመቱ ዘውዱ ነው።
"እኔ ገበሬ ነኝ፤ አልተማርኩም" የሚለው ዘውዱ በመጋቢት 12/2011 ዓ.ም. ከገጠር ወደ ስደት እንዳቀና ይገልጻል። ከዚያ በፊት በሳዑዲ አረቢያ የነበረ ሲሆን በሥራ ላይ እያለ ተይዞ ከታሰረ በኋላ ወደ አገር ተባርሯል።
እሱም በተመሳሳይ "'ገንዘብ እንሰጥሃለን፤ ዕቃ ተሸከምልን' አሉኝ" ይላል፤ በፖሊስ እንደተያዘም ይጠቅሳል።
በአሁኑ ጊዜ በአሲር ክልል የሞት ፍርድ ተፈረዶባቸው ታስረው ከሚገኙት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ነው። ስልሳ ስምንት ኢትዮጵያውያን ከሌሎች በከባድ ወንጀሎች የሞት ፍርድ ከተፈረደባቸው የአገሪቱ ዜጎች ጋር በሕንፃው ውስጥ ታስረዋል። ክብሮምን ጨምሮ ሦስት ስደተኞች ላይ የሞት ፍርዱ ሲፈጸም ግን 65ቱ ኢትዮጵያውያን ቀርተዋል።
"በሞት አፋፍ ላይ ነን። እዚህ ካለነው አብዛኛዎቻችን ከትግራይ የመጣን ሲሆን፣ አራቱ አማራ እና ሁለቱ ኦሮሞዎች ናቸው" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
"ከእኛ በፊት የታሰሩት እስር ብቻ ተፈረዶባቸው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል። እኛ ግን የሞት ፍርድ ነው የተፈረደብን።" ሲልም ይጨምራል።

'ሕክምና ባለማግኘቴ እግሬን አጣሁ'
ደስታ በሚገኝበት ህንፃ ውስጥ የሳዑዲ ድንበርን ለማቋረጥ ሲሞክር በጥይት የተመታ ሌላ ኢትዮጵያዊ ይገኛል። በክላሽ ከተመታ ከተወሰነ ግዜ በኋላ አንድ እግሩን እንዳጣ ይናገራል።
"በ2016 ከአገር ወጣሁ። ከአንድ ዓመት በኋላ ተያዝኩ። እስር ከተፈረደብኝ አንድ ዓመት አልፏል። በወቅቱ ሕክምና ማግኘት ባለመቻሌ እግሬ ተቆረጠ" ሲል ለቢቢሲ ገልጿል።
ከእስር ቤቱ ለቢቢሲ የደረሰ ቪዲዮ አንድ እግሩን አጥቶ በክራንች ሲራመድ ይታያል።
ስደተኛው እንደ እሱ በሳዑዲ የድንበር ጠባቂዎች በተከፈተባቸው ተኩስ እግራቸው፣ እጃቸው እና ሌሎች የአካል ክፍሎቻቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ይገልጻል።
ሞትን ያስከተሉ ፊርማዎች
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁሉም እስረኞች ሲታሰሩ የሞት ቅጣት እንደሚፈረድባቸው አልጠበቁም። ለዓመታት እስር ቤት ተፈርዶባቸው ከቆዩ በኋላ ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ነበር የሚያስቡት።
ሲታሰሩ በአረብኛ የተጻፈ ወረቀት ተሰጥቷቸው "በግዳጅ እንዲፈርሙ" እንደሚነገራቸው ይጠቅሳሉ። በኋላ ላይ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ የፈረሙት ወረቀት እጾችንና ሌሎች ሕገወጥ እቃዎችን ይዘው መገኘታቸውን የሚያመለክት ሆኖ እንደሚያገኙት ተናግረዋል።
ክሱን ለመቃወም ወይም በጠበቃ በኩል ለመከራከር ዕድል እንዳልተሰጣቸው ተናግረዋል። እንዲሁም የይግባኝ ሂደት አልተመቻቸላቸውም።
"በመጀመሪያው ቀን ዳኛ ፊት ስትቀርብ 'በዚህ ወንጀል ተከሰኻል፤ ክሱን ትቀበላለህ?' ብሎ ይጠይቅሃል። ለሁለተኛ ጊዜ ስትቀርብ ደግሞ የሞት ፍርድ ይፈርድብሃል። ከዛ በኋላ የምትከላከልበት ወይ ይግባኝ የምትልበት ዕድል የለም" ይላል ከሦስት ሌሎች ሰዎች ጋር አደንዛዥ ዕጽ በማዘዋወር የተፈረደበት ደስታ።
በ2013 ዓ.ም. በ19 ዓመቱ ከአገር የተሰደደው ሃብቶም ከ38 ወራት በላይ በእስር አሳልፏል።
"ስታሰር ወደተለያዩ ቦታዎች እየወሰዱ ወረቀቶች ላይ አስፈርመውኛል። ግን ቋንቋውን ስለማልችል ምን እንደሚል አልገባኝም ነበር። ሦስት ግዜ ዳኛ ፊት ለፍርድ ቀርቤያለሁ። ዳኛ ፊት የሚያቆሙህ ለደቂቃዎች ብቻ ነው።
"ወታደሮቹና ፖሊሶች ይዘውህ ስለሚሄዱ 'ፈርም' ሲሉህ መቃወም አትችልም። የግድ መፈረም አለብህ። ለሦስተኛ ግዜ ፍርድ ቤት ስንቀርብ ብቻ ነው ትግርኛ የሚናገር ሰው አምጥተው እየተባለ ያለውን በትርጉም እንዲነገረን ያደረጉት" በማለት የፍርዱን ሂደት ያብራራል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
'ከሞትኩ በኋላ መርዶ መንገር ይሻላል'
እነ ክብሮም ላይ የሞት ቅጣት ከተፈጸመ በኋላ ሌሎች የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ኢትዮጵያውያን መተኛትና የአእምሮ እረፍት ማግኘት አልቻሉም።
"የሚሰጠን ምግብ እንኳን መብላት አልቻልንም" ይላሉ።
በሳዑዲ አረቢያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና ቆንስላ ጉዳዩን ቢያውቁም ሊደርሱላቸው ግን እንዳልቻሉ እስረኞቹ አምርረው ይገልጻሉ።
በእስር ቤቱ ግድግዳ ላይ የተገጠመ ስልክ በመጠቀም ወደ ኤምባሲው ይደውላሉ። ሲደውሉ ስልኩ ብዙውን ጊዜ እንደማይነሳ፤ ከተነሳም ተስፋ ሰጪ ምላሽ እንደማያገኙ ይገልጻሉ።
"ሌላው ቀርቶ ፍርዳቸው ስለተፈጸመው ስደተኞች ለኤምባሲው ነገርናቸው፤ ሊያምኑን ግን አልቻሉም። 'አደንዛዥ ዕፅ በማዘዋወር የተገደለ ሐበሻ የለም' አሉን። ከሦስት ቀን በኋላ ግን መጥተው አረጋገጡ" ይላል ዘውዱ።
መንግሥት ለዜጎቹ ትኩረት ባለመስጠቱ ተስፋ እንደቆረጠ የሚናገረው ሀብቶም "ሌላው ቢቀር የሞት ፍርዱ ወደ እስራት እንዲቀየርልን መነጋገር ይቻል ነበር። ባለማወቅ አንዴ ተሳስተናል፤ በሞት ሳይሆን በእስራት እና በምህረት ማለፍ ይቻል ነበር" ይላል።
"ቤተሰቦቼ የሞት ፍርድ እንደተፈረደብኝ ሰምተው ከሚጨነቁ፤ ፍርዱ ከተፈጸመ በኋላ መርዶ ቢነገራቸው እመርጣለሁ" ሲልም አክሏል።
ሂዩማን ራይትስ ዎች ሚያዝያ 28 ባወጣው ሪፖርት የሳዑዲ ባለሥልጣናት በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ የሚጣለውን የሞት ቅጣት ባስቸኳይ እንዲያቆም ጥሪ አቅርቧል። ሁሉም ጉዳዮች በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት እንዲታዩ እና እንዲገመገሙም ተማጽኗል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ተወካዮቹ በፍጥነት ጣልቃ እንዲገቡ እና ዜጎቻቸው የቆንስላ ድጋፍ እንዲያገኙ የመብት ተሟጋቹ ጥሪ ኣቅርቧል።
የሚመለከታቸው መንግሥታት የሞት ቅጣትን ወይም ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዙ በወንጀሎች ላይ የሚፈረድ የሞት ቅጣትን እንዲያስወግዱ በሳዑዲ አረቢያ ላይ ጫና እንዲያደርጉ አሳስቧል።

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Foreign Affairs of Ethiopia
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማቲያስ በግንቦት 4/2018 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ "በሳዑዲ አረቢያ በሞት ጥላ ስር በጭንቀት ቀናቸውን እየቆጠሩ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን ኑሯቸውን ለማሻሻል በተሰደደቡት አገር ሊገደሉ ተቃርበዋል።
"ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግሥት የሞት ፍርዳቸው እንዲነሳ እና ወደ አገራቸው የሚመለሱበት ሁኔታ ለማመቻቸት ከሳዑዲ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ለሚደረጉ ውይይቶች ልዩ ትኩረት መስጠት አለበት" ብለዋል።
የኢትዮጵያውያኖቹ እስረኞች ጉዳይ በቅርቡ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ እና የሳዑዲ ዓረቢያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋሊድ አል ኻሪጂ በአዲስ ኣበባ ተገናኝተው ባደረጉት ውይይት ላይም ተነስቶ ነበር።
በዚሁ ወቅት ዶ/ር ጌዲዮን በሳውዲ አረቢያ የሚኖሩና የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን ደህንነት ማረጋገጥ እና ህጋዊ የስራ እድል መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አፅንኦት እንደሰጡ የሚኒስቴሩ መግለጫ አመልክቷል።
ቀደም ሲል የትግራይ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላላ ምክር ቤት በበኩሉ በተመሳሳይ ሁኔታ የእስልምና ታሪክ ከአቢሲኒያ ምድር ጋር ያለውን ግንኙነት እና የነቢዩ ሙሐመድን ምክር በመጥቀስ "የሳዑዲ መንግሥት በነቢዩ መሐመድ የተመሰከረውን ታሪካዊ ወንድማማችነት እና ውለታ አስታውሶ እነዚህን ኢትዮጵያውያን በእስልምና እና በሰው ልጅ ስም በሰላም ወደ አገራቸው እንዲመልሳቸው የምህረት ጥሪ እናቀርባለን" ብሏል።
ቢቢሲ በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ ምላሽ አላገኘም።
በጅዳ የሚገኘው የቆንስላ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አምባሳደር ጣፋ ቱሉ ዳዲ በስልክ ሲያነጋግሩን "በዚህ ጉዳይ ላይ እየሠራን ነው፤ ግን ስለ ዝርዝሩ ማውራት አልችልም" ሲሉ አጭር መልስ ሰጥተዋል።
ቢቢሲ ከሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ምላሽ ለማግኘት ያቀረበው ጥያቄም ጽሑፉ ለሕትመት እስከበቃበት ቀን ድረስ ምላሽ አላገኘም።
ከሁሉም በጉዳዩ ላይ ማብራርያ እንዲሰጡን ጥያቄ ያቀረብንላቸው አካላት የሚደርሱን ምላሾች ወይ አስተያየቶች ካሉ እናካትታለን።
ማስታወሻ፡ ከክብሮም የአጎት ልጅ መብራህቶም በስተቀር በዚህ ታሪክ ውስጥ የተጠቀሱ ስሞች በሳዑዱ እስር ቤት ላሉ ኢትዮጵያውያን እና ለቤተሰቦቻቸው ደህንነት ሲባል እንዲቀየሩ ተደርጓል።















