ታዋቂዋ ግብፃዊት የቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢ እና በርካታ ሰዎች በስቅላት እንዲቀጡ ተፈረደባቸው

ሳራ ኻሊፋ የወንጀል ጉዳዮች የሚቀርቡበት የቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢ ናት

የፎቶው ባለመብት, Sarah Khalifa Instagram account

የምስሉ መግለጫ, ሳራ ኻሊፋ የወንጀል ጉዳዮች የሚቀርቡበት የቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢ ናት
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ታዋቂዋ የግብፅ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢ ሳራ ኻሊፋ እና ሌሎች 11 ሰዎች ከአደንዛዥ ዕፅ እና ከሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ጥፋተኛ ተብለው በስቅላት እንዲቀጡ ተፈረደባቸው።

መንግሥታዊው አል አህራም ጋዜጣ እንደዘገበው፣ እነዚህ ግለሰቦች ዕፅ ለማምረት የሚያገለግሉ ጥሬ እቃዎችን ከውጭ በማስመጣት እና አደንዛዥ ዕፅ ለሽያጭ ለማቅረብ ያቀደ የወንጀል ቡድን አባላት ነበሩ።

በተጨማሪም ሕገወጥ የጦር መሣሪያዎች እና ጥይቶች ይዘው እንደተገኙ ተነግሯል።

የ39 ዓመቷ ሳራ ኻሊፋ በወንጀል ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር የቴሌቪዥን ፕሮግራም በማቅረብ የምትታወቅ ሲሆን፣ ከተከሰሰችባቸው ክሶች ሁሉ ንጹህ መሆኗን በመግለጽ ስትከራከር ቆይታለች።

ሞት ከተፈረደባቸው ሰዎች በተጨማሪ ሌሎች ዘጠኝ ሰዎች የዕድሜ ልክ እስራት ሲፈረድባቸው፤ ሰባት ሰዎች ደግሞ ከክሱ ነጻ ተብለው ተለቀዋል።

የኻሊፋ ጠበቃ በሞት ፍርዱ ላይ ይግባኝ እንደሚጠይቁ አስታውቀዋል።

የሞት ቅጣት ፍርዱ መጀመሪያ ላይ የተገለጸው ባለፈው ወር ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ከግብፅ ዋና ሙፍቲ ሃይማኖታዊ አስተያየት ካገኘ ከአንድ ወር በኋላ ተግባራዊ እንዲሆን በይፋ አጽንቶታል። ይህም በግብፅ የሞት ቅጣት ጉዳዮች ላይ የሚፈጸም ሕጋዊ ሂደት ነው።

በፍርድ ሂደቱ ወቅት ባለሥልጣናት ከ750 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን አደገኛ ዕፅ እና እነሱን ለማምረት የሚያስፈልጉ ጥሬ እቃዎች መያዛቸው ተነግሯል።

አል አህራም እንዳስታወቀው 20 ምስክሮች ለዐቃቤ ሕግ ቃላቸውን ሰጥተዋል፤ በተጨማሪም ውይይቶችን እና የቪዲዮ ቅጂዎችን የሚያካትት ኤሌክትሮኒክ ማስረጃዎች ቀርበዋል።

በመንግሥት የሚተዳደረው አክባር አል ዩም ጋዜጣ እንደዘገበው፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢያዋ ባለፈው መስከረም ችሎት በቀረበችበት ወቅት ዳኛው ስለተጠረጠረችበት ክስ ጠይቀዋት የምታውቀው ነገር እንደሌለ ቃሏን ሰጥታ ነበር።

ሳራ ኻሊፋ በወቅቱ በሰጠችው ምላሽ በቁጥጥር ሥር ውላ በአገሪቱ ፀረ ናርኮቲክስ ባለሥልጣን ቢሮ ውስጥ ተያዙ ከተባሉት ዕፆች ጋር አብራ ፎቶ እንድትነሳ ከመደረጓ በፊት ዕፅ ምን እንደሚመስል አይታ እንደማታውቅ ተናግራለች።

ባለፈው 2025 የአውሮፓውያን ዓመት በወጣው የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት መሠረት፣ በዓመቱ ከተለያዩ ወንጀሎች ጋር ተያይዞ ግብፅ ውስጥ 492 የሞት ፍርዶች የተላለፉ ሲሆን፣ 23 ሰዎች ተገድለዋል።

ሪፖርቱ እንደሚለው፣ ተከሳሾቹ በዕፅ ዝውውር እና በመዳፈር ወንጀል ጥፋተኛ ተብለው ቢፈረድባቸውም፣ እነዚህ ወንጀሎች በዓለም አቀፍ ሕግ እና መስፈርቶች መሠረት የሞት ቅጣት ሊጣልባቸው የሚገባ አይደሉም ብሎ ነበር።