አሜሪካ የተቃወመችው የአፍሪካን ትክክለኛ የቆዳ ስፋት የሚያሳይ አዲስ ካርታ በተባበሩት መንግሥታት ፀደቀ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ፣ የተለመደው የዓለም ካርታ የአፍሪካን የቆዳ ስፋት ይበልጥ ትክክለኛ በሆነ መጠን እንዲቀመጥ በሚያደርግ አዲስ ካርታ እንዲተካ ወሰነ።
በቶጎ አቅራቢነት እና በአፍሪካ ኅብረት አባል አገራት ድጋፍ የቀረበው ይህ 'ኮሬክት ዘ ማፕ' የተሰኘው የውሳኔ ሃሳብ፣ ፈረንሳይ እና ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ 164 አገራት ድጋፍ ሰጥተውት ፀድቋል።
አሜሪካ ውሳኔውን የተቃወመች ብቸኛ አገር ስትሆን፣ ስድስት አገራት ደግሞ ድምፀ ተአቅቦ አድርገዋል።
ይህ የተመድ ውሳኔ አስገዳጅ አይደለም። ይሁን እንጂ ባይሆንም፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ተቋማት የሚጠቀሙባቸውን ካርታዎች እንደሚቀይር ይጠበቃል።
አሁን ያለው የ'መርኬተር' ካርታ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በስፋት ጥቅም ላይ ውሏል።
በዚህ ካርታ ላይ በስፋት 14 እጥፍ የምትበልጠውን አፍሪካን ከግሪንላንድ ጋር በእኩል መጠን በማስቀመጡ ከፍተኛ ትችት ሲቀርብበት ቆይቷል።
ይህ መሆኑ የምድር ወገብ አካባቢ የሚገኙ አገራት የልማት ፍላጎት እና አቅምን አሳንሶ እንዲታይ ማድረጉን ተቺዎች ይናገራሉ።
የመርኬተር ካርታ በአውሮፓውያኑ 1569 የተነደፈው በቤልጂዬማዊው የካርታ ባለሙያ ጄራርደስ መርኬተር ነው። ካርታው የተሠራውም አውሮፓውያን አሳሾች በዓለም ዙሪያ ለሚያደርጉት ጉዞ እገዛ ለማቅረብ ነበር።
የአፍሪካ ቅርፅ አንሶ እንዲቀመጥ ያደረገው የካርታ መዛባት የተፈጠረው፣ የሉል ቅርጽ ያለውን የመሬት ገጽታ በባለ ሁለት ገጽታ ወረቀት ላይ በትክክል ማስቀመጥ ስለማይቻል ነው። በዚህም የተነሳ የዓለም ካርታ በሚዘጋጅበት ጊዜ የተወሰኑ ማመቻመቾችን ማድረግ ግዴታ ሆኗል።
የመርኬተር ካርታ የምድርን ኩርባ የሚያሳየው በምድር ወገብ አካባቢ ያሉትን አገራትን ትክክለኛ ስፋት በማሳነ ስነው። ወደ ምድር ዋልታዎች የተጠጉትን አገራት ደግሞ ስፋታቸውን ጨምሮ ያስቀምጣል።
ከስምንት ዓመት በፊት በአውሮፓውያኑ በ2018 አንድ የካርታ ባለሙያዎች ቡድን ይህንን ክፍተት ለማስተካከል የሚያስችል 'ኢኳል ኧርዝ' የተባለ እና የአገራትን ትክክለኛ የመሬት ስፋት የሚያሳይ ካርታ አዘጋጅቷል።
ባለፈው የካቲት ላይ የተሰበሰቡት 54ቱ የአፍሪካ ኅብረት አባል አገራት ይህንን ካርታ አጽድቀውታል። አገራቱ ካርታው "የሁሉንም አህጉራት፣ በተለይም የአፍሪካን ስፋት ይበልጥ በትክክል ይወክላል" ሲሉም በወቅቱ ገልጸዋል።
'#CorrectTheMap' የተባለው በበይነ መረብ ላይ ዘመቻ የሚያደርግ ቡድን በበኩሉ "አፍሪካ ውስጥ አሜሪካን፣ ቻይናን፣ ሕንድን፣ ጃፓንን፣ ሜክሲኮን እና አብዛኛውን የአውሮፓ ክፍል አካትቶ እንኳ፣ የሚተርፍ የመሬት ስፋት ይኖራል" ብሏል።
ትናንት አርብ በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ድምፅ ከመሰጠቱ አስቀድሞ ከዜና ወኪሉ ሮይተርስ ጋር ቆይታ ያደረጉት የቶጎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሮበርት ዱሴይ፣ "ፍትሐዊ ዓለም የሚጀምረው በፍትሐዊ ካርታ ነው" ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከውሳኔው በፊት ለድርጅቱ ባቀረቡት ማብራሪያ፣ "ካርተው በጭራሽ ገለልተኛ አይደለም። አመለካከቶችን ይቀርጻል፤ ሕዝቦች እና አህጉራት ዓለም ውስጥ ስላላቸው ስፍራ የሚረዱበትን መንገድን ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል" ሲሉ ተናግረዋል።
ይህንን ሀሳብ የደገፉት የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዣን ኖኤል ባሮት በበኩላቸው መሥሪያ ቤታቸው የመርኬተርን ካርታ መጠቀም እንደሚያቆም ገልጸዋል።
"ካርታውን መቀየር ዓለምን እንደማይለውጥ ግልጽ ነው። ነገር ግን ዓለምን አዛብቶ የሚያሳይን ምሥል ማረም በራሱ የእውነት ድርጊት ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።
የአሜሪካ ተወካይ የሆኑት ያሪና ፈረንሴቪች ግን የውሳኔ ሃሳቡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ሥራ እና ዓላማ ላይ ያፌዘ ነው ሲሉ ተችተዋል።
"ይህ ተቋም እንደ ሰላም፣ ብልፅግና ወይም መልካም ግንኙነት ባሉ እውነተኛ ችግሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ፣ የ16ኛው ክፍለ ዘመን የካርታ ሥዕሎች ላይ እየተከራከረ ነው" በማለት ተቃውሞ አሰምተዋል።
ባለፈው የካቲት ላይ የተባበሩት መንግሥታት አትላንቲክ ውቂያኖስን ተሻረሮ የተፈጸመውን የባሪያ ንግድን "በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ አስከፊ ወንጀል" ብሎ በፈረጀበት ወቅትም አሜሪካ በተመሳሳይ ተቃውሞ አሰምታ ነበር።















