"አያቴ እኔ ሳላውቅ ልጄን አስገረዘቻት"

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ማስጠንቀቂያ፡ ይህ ጽሑፍ ግርዛትን የሚመለከቱ አገላለጾች ይዟል።
ባለፈው ሳምንት ኮሎምቢያ በላቲን አሜሪካ ግርዛትን ሕገ ወጥ ያደረገች የመጀመሪያዋ አገር ሆናለች። ይህም ትልቅ ድል መሆኑን የመብት ተሟጋቾች እየገለጹ ነው።
ሕጉ የጸደቀው በምክር ቤት አባላት ሙሉ ድምጽ ነው።
በምሥጢር የሚከናወነው እና እጅግ አደገኛ የሆነው ግርዛትን በሕግ ለማሳገድ ለዓመታት ትግል ተደርጓል።
የካርላ ኩዊኖኔዝ (ስሟ ተለውጧል) ልጅ ገና የስድስት ወር ጨቅላ ሳለች ቅድመ አያቷ አስገርዘዋታል።
ካርላ እንደምትለው አያቷ ልጇን ሲሰጧት ከፍተኛ ሙቀት ነበራት። ጨቅላዋ ሰውነቷ አብጦ፣ እየደማች ነበር። ያለማቋረጥ ታለቅሳለች።
"አያቴን ተጋፈጥኳት፤ የተለመደ ነገር እንደሆነ እና ለማንም መናገር እንደማልችል ነገረችኝ።"
በቅርቡ የነበረው የጤና ተቋም ብዙ ርቀት ያስኬዳል። አዋላጅ የሆነችው የካርላ እናት የጨቅላዋን ሕመም ለመቀነስ ባህላዊ ቅጠላ ቅጠሎች ትጠቀም ጀመር።
እሷም ቢሆን አያትየውን በጥያቄ አፋጥጣለች። በዕድሜ የገፉት ሴት ግን ምንም ሊዋጥላቸው አልቻለም።
"ቂንጥር ያላቸው ሴቶችን ወንዶች ይቀልዱባቸዋል አለችን።"

የሴት ልጅ ግርዛት በኮሎምቢያ
ግርዛት የሴት ልጅ ብልት ውጭኛውን ሽፋን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ማስወገድ ነው።
በሴት ልጅ ብልት ላይ ሌሎችም ሕክምና የማይደግፋቸው ሌሎች ጉዳቶች ይደርሳሉ።
ይህም ከልክ ያለፈ ደም መፍሰስ እና ኢንፌክሽንን ጨምሮ ለተለያዩ ለውስብስብ ሕመሞች ያጋልጣል።
ሴቶች ዕድሜያቸው ከፍ ብሎ በወር አበባ እና በወሊድ ወቅትም ተጽዕኖ የሚያሳድሩባቸው የጤና እክሎች በግርዛት ሳቢያ ይገጥሟቸዋል።
ሴቶች ከወሲብ እርካታን እንዳያገኙም የሚያደርግ ነው።
የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው በመላው ዓለም ከ230 ሚሊዮን በላይ ታዳጊ እና አዋቂ ሴቶች ተገርዘዋል። አብዛኛው ሴቶች የሚገኙት በአፍሪካ ነው።
የ30 ዓመቷ ካርላ ግርዛት በኮሎምቢያ ሕገ ወጥ እንዲሆን ስትታገል ነበር።
እንደ ኢምቤራ ያሉ ቀደምት ማኅበረሰቦች ግርዛት ይፈጽማሉ። ካርላ የተወለደችው ከዚህ ማኅበረሰብ ነው።
ከሌሎች የመብት ተሟጋቾች እና ከኮሎምቢያ ምክር ቤት ጋር በመሆን ግርዛት ሕገ ወጥ እንዲሆን ንቅናቄ አድርገዋል።
በምሥጢር ግርዛት እየተፈጸመ እንደሆነ ያወቀችው ዕድሜዋ ከጨመረ በኋላ ነው።
"ከወሊድ በኋላ ከወንድ ልጆች ይልቅ ሴት ልጆች ለምን እንደሚሞቱ ይገርመኝ ነበር" ትላለች።
"እናቴ ያዋለደቻት የአክስቴ ልጅ ጤናማ ሆና ስትወለድ አስታውሳለሁ። ከሦስት ቀናት በኋላ ሞተች። እናቴን ስጠይቃት ልጅቷ የሞተችው ጥንታዊ በሆነ 'ጃይ' በተባለ ሕመም ምክንያት እንደሆነ ነገረችኝ።"
'ጃይ' ገድሏቸዋል የሚባሉት ጨቅላ ሴቶች የሞቱበት ምክንያት ከግርዛት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ታምናለች።

የፎቶው ባለመብት, Courtesy of Diana Ramos / Photo by David Jiménez
የሕክምና ባለሙያዎች ምን ይላሉ?
በአውሮፓውያኑ ከ2020 እስከ ሰኔ 2026 ባለው ወቅት በኮሎምቢያ 240 ግርዛቶች መፈጸማቸው ተመዝግቧል።
በአብዛኛው ግርዛት የተፈጸመባቸው ሴቶች ዕድሜያቸው ከስድስት ያነሰ ነው።
የሕጻናት ሕክምና ባለሙያ ዲያና ራሞስ ሞስኩዌራ እንደምትለው የተጠቀሰው ቁጥር የግርዛትን ሰፊ መጠን በትክክል አያሳይም።
በፒሬራ ግዛት በሚገኘው ሳን ጆርግ ዩኒቨርስቲ የምትሠራው ባለሙያዋ እንደምትናገረው፤ በምርመራ ወቅት በሴቶች ላይ የጠባሳ ምልክት፣ የቃጠሎ እና የትልተላ ምልክቶችም አይታለች።
እነዚህ ሴቶች ለሌላ ሕክምና ወደ ተቋሙ ያመሩ ናቸው።
አንዲት ሴት የብልቷ ከንፈር ተሰፍቶ አግኝታታለች። የወር አበባዋ ሊወርድ ወይም ስታድግ ወሲብ ልትፈጽምም አትችልም ማለት ነው።

የፎቶው ባለመብት, José Carlos Cueto / BBC Mundo
"ሰውነቷን መልሶ ለማስተካከል ቀዶ ሕክምና ማድረግ ያስፈልግ ነበር" ትላለች ዶ/ር ዲያና።
ግርዛት እንደ ወሲባዊ ጥቃት ወይም ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት እንደሚወሰድ ትናገራለች።
ግርዛት ዕድሜ ልክ የሚዘልቅ ጉዳት እንደሚያሳድር እና ግርዛትን ለማስቀረት ቅጣት ብቻ ሳይሆን ትምህርትም እንደሚያስፈልግ ትገልጻለች።
"አንዳንድ የዚህ ማኅበረሰብ አባላት የእውነታቸውን ጉዳት አያስከትልም ብለው ያምናሉ" ትላለች።

'ባህል አይገድልም'
ከኮሎምቢያ ቀደምት ማኅበረሰቦች አንዱ መሆነው ኤምቤራ ኔሽን ሥር ወደ 300 ሺህ ሰዎች ይገኛሉ።
እነዚህ ማኅበረሰቦች በኢኳዶር እና ፓናማም ይኖራሉ።
በሌሎች የላቲን አሜሪካ አገራት በማይታይ መልኩ ይህ ማኅበረሰብ ግርዛት መፈጸም የሚስተዋልበት መላ ምት ተብሎ የተቀመጠው ድርጊቱ በቅኝ ግዛት ከአፍሪካ ከሄዱ ሰዎች ጋር አብሮ ባህሉ መለመዱ ነው።
አብዛኞቹ አፍሪካውያን-ኮሎምቢያውያን የሚኖሩበት አካባቢ አጎራባች በሆኑር የሪሳራልዳ፣ ቾኮ እና ባሊ ደል ካውካ ግርዛት የሚፈጸመውም ለዚህም ይሆናል።
ሌላኛው መላ ምት ከመቶ ዓመታት በፊት ባለ ሁለት ፆታ ልጅ "ቂንጥር በመፍራት" ከማኅበረሰቡ መውጣታቸው ነው። በብዛት ዕድሜ የገፉ ሴቶች ካልተቆረጠ የወንድ ብልት ሆኖ ያድጋል ብለው ያምኑ ነበር።
ሌሎች እንደሚሉት አባታዊ ሥርዓት የተጫነው ማኅበረሰብ ሴት ልጅ ከወሲብ ደስታ ማግኘቷ ተቀባይነት የሌለው አድርጎ መውሰዱ ነው።
በብሔራዊ ኮንፌደሬሽን የማኅበረሰቡ አማካሪ እና ሕጋዊ ተወካይ ጁሊያና ዶሚኒኮ ግርዛት ባህላዊ ክንውን ነው መባሉን አትቀበልም።
"ባህላችን አለባበሳችን፣ ጌጣ ጌጣችን፣ ቋንቋችን ነው እንጂ የሚገድል ድርጊት አይደለም። ባህል አይገድልም" ትላለች።
አዲሱ ሕግ ለዓመታት በማኅበረሰቡ የተደረገ ንቅናቄን ተከትሎ የመጣ እንደሆነ ትናገራለች።
"ሕጉ የሥነ ሕዝብ ፖሊሲ ሆኖ፣ በሰፊ ግብዓት ታግዞ ይተገበራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።"
ካርላ ለለውጥ ሲታገሉ ከነበሩት አንዷ ናት። በንቅናቄዋ ምክንያት በተለይ ከወንዶች ማስፈራሪያ እንደደረሳት ትናገራለች።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ወንዶች ስለ ግርዛት ባያውቁም ግርዛትን ለማስቆም የሚደረግ እንቅስቃሴ ላይ ጎልተው የሚታዩት ወንዶች ናቸው። ለዚህም ምክንያቱ የማኅበረሰቡ ሴቶች በብዛት ስፓኒሽ ሳይሆን የአካባቢውን ቋንቋ ብቻ መቻላቸው ነው።
በዚህ ምክንያት ሴቶች ለልጆቻቸው ከሕክምና ባለሙያዎች እርዳታ ማግኘትም ይቸገራሉ።
አንዳንዴም አመለካከታቸው የተዛባ እና ሰውን የሚገምቱ የጤና ባለሙያዎች እንደሚገጥሟቸውም ካርላ ትናገራለች።
የሽንት ትቦ ኢንፌክሽን ልጇ ላይ ባስከተለው ትኩሳት ምክንያት ወደ ሆስፒታል ስትወስዳት "በጣም ጨካኝ" እንደሆነች ነግራት ልጇ ላይ የደረሰው እንደሚገባት ነግራታለች።
"ልጄን ወስደው በሕጻናት ማቆያ ለማስገባትም ሲዝቱብኝ ነበር። አሁን ልጄን ሆስፒታል አለመውሰድ እመርጣለሁ። በቅጠላ ቅጠል አክማታለሁ። ከጎኗ አልለይም።"
ካርላ በማኅበረሰቧ ዘንድ ለውጥ እንዳለ ትናገራለች። ሴቶች ግርዛት መፈጸም አለበት ወይስ የለበትም በሚለው ላይ ውይይት መጀመራቸውን ትጠቅሳለች።
አንድ አያት የልጅ ልጆቿን መገረዝ የፈጠረባትን ስሜት መግለጿን ታስታውሳለች።
"ለክፋት ብላ የፈጸመችው ድርጊት እንዳልሆነ ተናግራለች። የልጅ ልጆቿን ወንዶች እንዳይተቿቸው በሚል ያደረገችው ነው።"
ግርዛት እንዴት ሕይወትን ከባድ እንደሚያደርግ ውይይቶች መጀመራቸው "ሴቶች ጤናማ ሰውነት ሮሯቸው እንዲያድጉ" ያደርጋል ትላለች።
የሆነ ወቅት ላይ ስለዚህ ጉዳይ ከልጇ ጋር መነጋገሯ አይቀርም።
"ሁላችንም ሰውነታችንን ማወቅ እና ስለ ሰውነታችን ማውራት የሚያሳፍር እንዳልሆነ መገንዘብ አለብን።"















