የአሜሪካ ፍርድ ቤት የጽንስ ማቋረጫ ክኒን በፖስታ ቤት እንዳይላክ የሚከለክል ውሳኔ አስተላለፈ

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካ ፍርድ ቤት ጽንስ ለማቋረጥ የሚያገለግለው ማይፌፕሪስቶን የተባለ መድሃኒት በፖስታ ቤት እንዳይላክ የሚከለክል ውሳኔ አስተላለፈ።

አርብ ዕለት የይግባኝ ሰሚ ችሎት ጽንስ ማቋረጥ የሚፈልጉ ሰዎች በፖስታ ቤት ወይም በቴሌሜዲስን በኩል መቀበል ሳይሆን በአካል መገኘት አለባቸው የሚል ጊዜያዊ ውሳኔ አስተላልፏል።

የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በአሜሪካ ጽንስ ለማቋረጥ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውለውን መድሃኒት የሚገኝበትን መንገድ የሚገድብ ነው ተብሏል።

ክሱ መጀመርያ ለፍርድ ቤቱ የቀረበው በሉዊዚያና ግዛት ሲሆን ዶክተሮች ግለሰቧን ሳያዩ መድሃኒቱን እንዲልኩ የሚፈቅደውን እአአ በ2023 የወጣ የምግብ እና መድሃኒት አስተዳደር (ኤፍዲኤ) መመሪያን ያስቆማል።

የይግባኝ ሰሚ ችሉቱ በውሳኔው ላይ "በኤፍዲኤ ውሳኔ መሠረት የሚካሄድ እያንዳንዱ ጽንስ ማቋረጥ ሉዊዚያና የጣለችውን እገዳ ይጥሳል። 'እያንዳንዱ ያልተወለደ ልጅ ከተፀነሰበት ጊዜ ጀምሮ ሰው ነው፤ ስለዚህ ሕጋዊ ሰው ነው' የሚለውን የግዛቲቱን ፖሊሲ ይጻረራል" ሲል አስፍሯል።

ጉዳዩ በፍርድቤት መታየቱ በሚቀጥልበት ወቅት ውሳኔው እንደጸና እንደሚቆይ ተገልጿል።

ማይፌፕሪስቶን (mifepristone) ጽንስን ለማቋረጥ በአሜሪካ የምግብ እና መድሃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ከሚመከሩ ሁለት መድሃኒቶች መካከል አንዱ ነው።

ጽንስ ማቋረጥ ሕጋዊ በሆነባቸው የአሜሪካ ግዛቶች መድሃኒቱ በስፋት ይገኛል።

እአአ በ2021 ሚያዚያ ወር በኮቪድ ወረርሽኝ የተነሳ የመድሃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን በአካል ተገኝቶ መድሃኒቱን መረከብ ግዴታ መሆኑን የሚጠቅሰውን መመሪያ በማንሳቱ በስፋት ጥቅም ላይ መዋል ጀምሯል።

እአአ በ2023 የቁጥጥር ባለሥልጣኑ መመሪያውን በቋሚነት ያነሳ ሲሆን ይህም መድሃኒቱ በፖስታ ወደ ግለሰቧ እንዲደርስ አስችሏል።

እአአ በ2023 የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማይፌፕሪስቶንን ለማገድ የቀረበውን ክስ በሙሉ ደምጽ ውድቅ አድርጎቶ ነበር።

ነገር ግን ይህ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የመጣው በአገር አቀፍ ደረጃ ጽንስን ማቋረጥ ሕጋዊ ከሆነ ከሁለት ዓመት በኋላ ቢሆንም መድሃኒቱን ማግኘት ለመገደብ የሚደረጉ ሌሎች ጥረቶች ግን ቀጥለው ሆነው ቆይተዋል።

አርብ ዕለት የይግባኝ ሰሚ ችሎቱ ያሳለፈው ውሳኔ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ክሱ እንዲቋረጥ ያደረገውን የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ የሻረ ነው።

የሉዊዚያና ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሊዝ ሙሪል የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አድንቀው የባይደን አስተዳደር "በሺህዎች የሚቆጠሩ የሉዊዚያና ሕጻናት እንዲሞቱ መንገድ ጠርጎ ነበር፤ በሌሎች ግዛቶች ደግሞ ሚሊዮኖችን" ብለዋል።

"ይህ ጉዳይ መታየቱን ሲቀጥል ሴቶች እና ሕጻናትን መከላከሌን እቀጥላለሁ" ብለዋል።

የአሜሪካ ሲቪል ሊበርቲስ ዩኒየን ጠበቃ የሆችው ጁሊያ ካዬ ግን በሰጠችው መግለጫ "ይህ ውሳኔ በግልጽ ሳይንስን እና የተቀመጠ ሕግን የሚጻረር እና በአሜሪካ ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላገኘውን የጸረ ውርጃ አጀንዳን የሚያራምድ ነው" ብላለች።

የኒው ዮርክ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሌቲሺያ ጀምስ አርብ ዕለት ፍርድ ቤቱ ይህንን ቢወስንም በግዛታቸው ጽንስ ማቋረጥ ሕጋዊ ሆኖ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ማይፌፕሪስቶን (Mifepristone ) የሚሰራው እርግዝና እንዲቀጥል አስፈላጊ የሆነውን ፕሮጄስትሮን የተባለውን ሆርሞን በመከልከል ነው። ሚሶፕሮስቶል (misoprostol) ደግሞ ማኅጸንን ባዶ ያደርጋል።

እንደ አሜሪካ የምግብ እና መድሃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን መረጃ ከሆነ እአአ ከ2000-2018 ባሉት ዓመታት ከ3.7 ሚሊዮን በላይ ሴቶች መድሃኒቱን ተጠቅመዋል።

የአሜሪካ የማህጸን እና ጽንስ ኮሌጅ እና ሌሎች የሕክምና ድርጅቶች ማይፌፕሪስቶንም ሆነ ሚሶፕሮስቶል ደኅንነታቸው የተጠበቁ መድሃኒቶች መሆናቸውን ይናገራሉ።