ኢትዮጵያዊን ጨምሮ የአራት የአፍሪካ አገራት ዜጎች ከአሜሪካ ተባርረው ካሜሩን ገቡ

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ኢትዮጵያዊ ስደተኛን ጨምሮ ከአሜሪካ የተባረሩ የአራት አገራት ዜጎች በዚህ ሳምንት ወደ ካሜሮን መድረሳቸውን ጠበቆቻቸው እንደተናገሩ የዜና ወኪሉ ኤኤፍፒ ዘገበ።

ዘጠኙ ስደተኞች ወደ ማዕከላዊ አፍሪካዊቷ አገር የተላኩት ካሜሮን እና አሜሪካ በገቡት ስምምነት መሠረት መሆኑ ተገልጿል።

ኤኤፍፒ ያወጣው ዘገባ እንደሚያመለክተው የኢትዮጵያ፣ ጋና፣ አንጎላ እና ኮንጎ ብራዛቪል ዜግነት ያላቸው ስደተኞች ካሜሮን የገቡት ረቡዕ ሚያዝያ 21/2018 ዓ.ም. ነው።

ስደተኞች ላይ የሚወስደውን እርምጃ ያጠናከረው የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ወደ አገራቸው መመለስ የማይችሉ ስደተኞች ወደ ሦስተኛ አገራት የሚልክበት አወዛጋቢ አሰራር እየተከተለ ነው። አሜሪካ ስደተኞችን ከሚቀበሉላት በርካታ የአፍሪካ አገራት ጋር ስምምነት የፈጸመች ሲሆን ግለሰቦቹ ወደ አገራቸው እስከሚመለሱ ድረስ በተቀባይዋ አገር ይቆያሉ።

ከትራምፕ አስተዳደር ጋር ይህንን ዓይነት ስምምነት ከፈጸሙት አገራት አንዷ ካሜሩን ነች። የረቡዕ ዕለቱን ጨምሮ ከጥር ወር ወዲህ ሦስት ጊዜ ስደተኞች ወደ ካሜሩን መባረራቸውን የዜና ወኪሉ ያነጋገራቸው በአሜሪካ የኢሚግሬሽን ጠበቃ አልማ ዴቪድ ገልጸዋል።

በዚህ ሳምንት የደረሱት ስድስት ሴቶች እና ሦስት ወንዶች ከዚህ ቀደም ከአሜሪካ ወደ ካሜሩን የተባረሩት ሌሎች 17 ስደተኞችን ይቀላቀላሉ ተብሏል።

የተደረጉትን የመጀመሪያዎቹ ሁለት በረራዎች የተከታተሉት ካሜሩናዊው ጠበቃ ጆሴፍ አዋህ ፍሩ ረቡዕ ዕለት ሦስተኛው አውሮፕላን መድረሱን ለዜና ወኪሉ አረጋግጠዋል።

የአሜሪካው ጋዜጣ ኒው ዮርክ ታይምስ ያውጣው ዘገባ እንደሚሳየው ካሜሩን ዜጋዎቿ ያልሆኑ ስደተኞችን በመቀበሏ 300 ሚሊዮን ዶላር ከዋሽንግተን ታገኛለች።

ይህንን ዓይነቱን ስምምነት ከአሜሪካ ጋር ከፈጸሙት ሌሎቹ የአፍሪካ አገራት ሩዋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኢኳቶሪያል ጊዜ፣ ጋና፣ ኢስዋቲኒ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ናቸው።

ወደ ሦስተኛ አገር ከሚላኩት ስደተኞች ውስጥ አብዛኛዎቹ በደኅንነት ስጋት ምክንያት ወደ አገራቸው እንዳይባረሩ በአሜሪካ የፍትሕ ሥርዓት እገዳ የተቀመጠላቸው ናቸው። በዚህም ምክንያት የትራምፕ አስተዳደር ወደ ሦስተኛ አገር የሚልካቸው ሲሆን፤ ተቀባዩ አገርም ወደ መጡበት ሊያባርራቸው ይችላል።

ከዚህ ቀደም ወደ ካሜሩን ከተወሰዱት ስደተኞች ውስጥ አራቱ ወደ መገኛ አገራቸው ሞሮኮ፣ አንጎላ እና ሴኔጋል እንዲባረሩ ተደርጓል።

የአሜሪካ ፍርድ ቤቶች ሁለቱ ሞሮኮውያን ሴቶች ወደ አገራቸው ቢመለሱ ሊደርስባቸው ስለሚችለው የደኅንነት ሥጋት ያቀረቡት አቤቱታ ተገቢ እንደሆነ ወስነው ነበር። ቢሆንም ግን ተባርረዋል።

አሜሪካዊው ጠበቃ ለዜና ወኪሉ እንደተናገሩት ስደተኞቹ ወደ ሞሮኮ እንዲመለሱ ከተደረጉ በኋላ ሕይወታቸውን እየገፉ ያሉት ተደብቀው ነው።

የካሜሩን ባለሥልጣናት ከዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ጋር በመተባበር በሚያስተዳድሩት ማዕከል ውስጥ የሚገኙት የቀሩት አሥራ ሦስት ሰዎች ከፈለጉ ካሜሩን ውስጥ የፖለቲካ ጥገኝነት መጠየቅ እንደሚችሉ በዘገባው ተጠቅሷል።

ዓለም አቀፉ ሰብአዊ መብቶችተቋም ሂውማን ራይትስ ዎች መስከረም ላይ ባወጣው መግለጫ፤ የትራምፕ አስተዳደር በፈጸማቸው "ግልጽነት በጎደላቸው ስምምነቶች" አማካኝነት የሚደረጉ የማባረር እርምጃዎች ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጥሱ በመሆናቸው ውድቅ ሊደረጉ እንደሚገባ አሳስቦ ነበር።