ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ 5,000 ወታደሮቿን ከጀርመን ልታስወጣ ነው
የጀርመን መራሄ መንግሥት በኢራን ጦርነት ምክንያት ዶናልድ ትራምፕን ከተቹ ከቀናት በኋላ የአሜሪካ መከላከያ መስሪያ ቤት 5,000 ወታደሮችን ከጀርመን ለማስወጣት ማቀዱን አስታወቀ።
መስሪያ ቤቱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው የጀርመኑ መራሄ መንግሥት ፍሬድሪክ መርዝ፤ አሜሪካ በኢራን ተደራዳሪዎች "ተዋርዳለች" በማለት የዋሽንግተንን አካሄድ ከተቹ ከቀናት በኋላ ነው።
ሐሙስ ዕለት ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ መርዝን "አሳፋሪ ሥራ እየሰራ ነው" ሲሉ ነቅፈው የስደተኞች እና ኢነርጂ ጨምሮ "የሁሉም ዓይነቶች ችግሮች" አሉበት ሲሉ ኮንነዋቸዋል። ትራምፕ በጣሊያን እና ስፔን የሚገኙ ወታደሮችን ለማስወጣት ሃሳብ አንዳላቸው ገልጸዋል።
አሜሪካ፣ ጀርመን ውስጥ ከፍተኛ የሠራዊት አባላትን ያሰፈረች ሲሆን እስከ በመላ አገሪቱ በሚገኙ ጦር ሰፈሮች 36,000 ወታደሮች እንዳሏት ታህሳሥ ላይ የወጣ መረጃ ያመልክታል ።
የፔንታጎን ቃል አቀባይ ሺን ፓርኔል በሰጡት መግለጫ ውሳኔው የተላለፈው በመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴት መሆኑን ተናግረዋል።
"ይህ ውሳኔ በአውሮፓ ውስጥ የመምሪያውን የኃይል አቀማመጥ በጥልቀት በመገምገም የቲያትር መስፈርቶችን እና በመሬት ላይ ያለውን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው" ብለዋል።
ወታደሮቹ መቼ ጀርመንን ለቅቀው እንደሚወጡ ሲያስረዱም "ከስድስት ወራት እስከ 12 ወራት ባሉት ጊዜያት ውስጥ ተጠቃልለው ይወጣሉ ብለን እንጠብቃለን" ሲሉ ተናግረዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ለረዥም ጊዜ የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ጥምረትን (ኔቶ) በመተቸት ይታወቃሉ። አባል አገራቱ የሆርሙዝ ወሽመጥን ዳግም ለማስከፈት በሚደረግ ዘመቻ ላይ ለመሳተፍ እምቢተኛ በመሆናቸው በተደጋጋሚ ተችተዋቸዋል።
ትራምፕ ሐሙስ ዕለት አሜሪካ በጣሊያን እና ስፔን ያሏትን ወታደሮች ታስወጣ እንደሆን ተጠይቀው "ልመለከተው እችላለሁ፤ ስለምን ላልመለከተው እችላለሁ?" ሲሉ መልሰዋል።
አገራቱ በኢራን ጦርነት ላይ የሰጡትን ምላሽ በመተቸት "ጣሊያን እኛን ምንም እየረዳች አይደለም፤ ስፔንም እንዲሁ አስቸጋሪ ናት" ሲሉ አክለዋል።
የጀርመኑ መራሄ መንግሥት መርዝ አሜሪካን የሚተቸውን ንግግራቸውን ያሰሙት ሰኞ ዕለት ማርስበርግ ውስጥ በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው ለተማሪዎች ባደረጉት ንግግር ወቅት ነው።
መርዝ "አሜሪካ ምንም ስትራቴጂ እንደሌላት ግልጽ ነው" ሲሉ ለተማሪዎቹ ተናግረዋል።
"ኢራናውያኑ ድርድር ላይ እጅግ የተካኑ መሆናቸው ወይም ድርድር አለማድረግ ላይ በጣም ጎበዝ መሆናቸው ግልጽ ነው። አሜሪካውያን ወደ ኢስላማባድ እንዲጓዙ እና ያለ ውጤት በድጋሚ እንዲመለሱ አድርገዋል" ብለዋል።
"መላ አገሪቱ" በኢራን አመራር "እየተዋረደ" ነው ሲሉም አክለዋል።
ዶናልድ ትራምፕ በምላሹ የመርዝ ሃሳብ "ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ቢኖራት ችግር የለውም ማለት ነው" ካሉ በኋላ "ስለምን እንደሚያወራ አያውቅም" ብለዋቸዋል።
"በምጣኔ ሃብቱም ሆነ በሌሎች መስኮች ጀርመን ደካማ ብትሆን አይደንቅም" ሲሉ በልጥፋቸው ላይ መርዝን እና አመራራቸውን ወርፈዋል።
ቢቢሲ በዋሺንግተን የሚገኘውን የጀርመን ኤምባሲ አስተያየት ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም
አሜሪካ በአውሮፓ ካሏት ወታደሮች ሁሉ በጀርመን ውስጥ የሚገኙት ከፍተኛ ቁጥር የሚይዙ ሲሆን፣ በጣሊያን 12,000 በዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ 10,000 ወታደሮች አስፍራለች።
አብዛኞቹ ወታደሮች በደቡብ ምዕራብ ጀርመን፣ ከካይሴርስላውተርን ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው በራምስቴይን የአየር ኃይል ጦር ሠፈር ይገኛሉ።
ትራምፕ ከዚህ ወደም በጀመርመን የሚገኙ ወታደሮችን ስለመቀነስ አንስተው የነበረ ቢሆንም እስከአሁን ድረስ ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቷል።
እአአ በ2020 በጀርመን የሚገኙ 12,000 ወታደሮችን ለማስወጣት ወይንም በአውሮፓ በሚገኙ ሌሎች የኔቶ አባል አገራት ለማዘዋወር የቀረበው ዕቅድ በኮንግረስ ውድቅ የተደረገ ሲሆን ጆባይደን ወደ ሥልጣን ሲመጡ ውሳኔውን ቀልብሰውታል።
በወቅቱ ትራምፕ ጀርመን ለጦር ሠራዊቷ የምትመድበው በጀት ኔቶ ካስቀመጠው እና ከአገራዊ ጥቅል ምርት (ጂዲፒ) 2 በመቶ መሆን አለበት ከሚለው መመሪያ በታች በመሆኑ "ቸልተኛ" ሲሉ ተችተዋት ነበር። ይህ ግን በመርዝ አስተዳደር በከፍተኛ ሁኔታ ተለውጧል።
ጀርመን በሚቀጥለው ዓመት፣ እአአ በ2027 አጠቃላይ አገራዊ ምርቷ 3̏.1 በመቶ እንደሚደርስ በመገመት 105.8 ቢሊዮን ዩሮ ለመከላከያ ለማውጣት ውሳኔ አሳልፋለች።
ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው ያላትን ወታደራዊ ግዴታ ከአውሮፓ ወደ ኢንዶ ፓስፊክ ቀጣና ለማዞር በመወሰናቸው ባለፈው ዓመት በሮማኒያ የሚገኙትን የአሜሪካ ወታደሮች ቁጥር ለመቀነስ ወስነዋል።
የሮማኒያ መከላከያ ሚኒስትር ውሳኔው የተሰማው ሄግሴት ሮማኒያውያን ለመከላከያቸው የሚሰጡትን ትኩረት ከፍ እንዲያደርጉ ካሳመኗቸው በኋላ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ ውሳኔ ግን በትራምፕ ፓርቲ አባላት ዘንድ ተቀባይነት ያላገኘ ሲሆን ሩሲያ ላይ ስጋት ያላቸው የኮንግረስ አባላትም ጥያቄ አንስተውበታል።