ትራምፕ እና ኔታንያሁ ያደረጉት "የተካረረ" የስልክ ምልልስ ከኢራን ጋር ያለውን ድርድር እንዳወሳሰበው ተነገረ

የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ እና የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ምንም እንኳን ብዙ ጊዜ አለመግባባቶች ቢፈጠሩም ኔታንያሁ ትራምፕን " የእስራኤል ታላቅ ወዳጅ" ሲሉ በተደጋጋሚ ጠርተዋቸዋል።
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

ዶናልድ ትራምፕ ከቤኒያሚን ኔታንያሁ ጋር ባለመግባባት የቅርቡ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ሆነዋል።

ይህ የተሰማው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር የዋሽንግተን እና ኢራንን ዲፕሎማሲ ቀውስ ውስጥ ያስገባውንና በሊባኖስ ላይ እየወሰዱት ያለውን እርምጃ በተመለከተ መጋጨታቸው ከተዘገበ በኋላ ነው።

ኢራን ከአሜሪካ ጋር ከምታደርግው ድርድር ልትወጣ እንደምትችል በማስፈራራት እስራኤል በሊባኖስ ላይ ለምትፈፅመው ጥቃት ምላሽ ሰጥታለች።

ይህም ብዙ ድጋፍ ላላገኘው እና ከኢራን ጦርነት ለመውጣት ትራምፕ እያደረጉት ያለውን ጥረት ወደ ኋላ የሚጎትት ሆኗል።

ትራምፕ ኔታንያሁን " የለየለት እብድ" እና "ክብረ ነክ" ሲሉ ሰኞ ዕለት በነበራቸው የስልክ ልውውጥ መናገራቸው ተዘግቧል።

ይህን ስለማለታቸው በጋዜጠኞች የተጠየቁት ትራምፕ "ብያለሁ" ብለዋል።

ትራምፕ ለፖድ ፎርስ ዋን ፖድካስት ረቡዕ ዕለት በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ "ተቆጥቻለሁ አልልም፤ ያለማቋረጥ ከሊባኖስ ጋር እያካሄደ ያለው ውጊያ ትንሽ አሳስቦኝ ነበር" ሲሉ ተናግረዋል።

"ቢቢን በጣም እወደዋለሁ፤ ከእርሱም ጋር ጥሩ ሰርቻለሁ" ሲሉም ትራምፕ ከኔታንያሁ ጋር ስላላቸው ግንኙነት አስረድተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ትራምፕ ከእራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትርን ጋር አተካራ ውስጥ የገቡ የቅርቡ ፕሬዚዳንት ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ የዋይት ሐውስን ትዕግስት በመፈተን ረዥም ታሪክ ያላቸው ሲሆን ማንኛውንም ፖለቲካዊ አለመግበባት ተቋቁመዋል።

የአሁኑ ግጭት የተሰማውም ትራምፕ የኢራንን ተኩስ አቁም ለማራዘም እና ለወደፊቱ የቴህራን ኒውክሌር ፕሮግራም ድርድር በር ለሚከፍት ስምምነት ፍላጎት ባሳዩበት ወቅት ነው።

የዓለም አብዛኛው ነዳጅ መተላለፊያ ሆነው የሆርሙዝ ወሽመጥ እንደገና መከፈትም ሌላኛው ወሳኝ ጉዳይ ነው።

ኔታንያሁ በበኩላቸው ከአሜሪካ አጋራቸው ጋር ስላለው ውጥረት ተጠይቀው በአግራሞት ሳቅ ብለው ነው የመለሱት።

"አንዳንዴ እንደ ጥሩ ቤተሰብ እንዲህ ዓይነት ስልታዊ አለመግባባቶች ይኖራሉ" ሲሉ ረቡዕ ዕለት ሲኤንቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ተናግረዋል።

"ሁል ጊዜም እነዚህን አለመግባባቶች ለመፍታት እንሰራለን፤ እንደ ጥሩ ጓደኛም ይህንን እናደርጋለን" ሲሉም አክለዋል።

ጨምረውም "ሁለቱ [አሜሪካ እና እስራኤል] ጠዋት ላይ ሳይስማሙ፤ ከሰዓት ሊስማሙ ይችላሉ።" ብለዋል።

ሆኖም ባለሙያዎች የስልክ ልውውጡ የካቲት ወር ላይ በኢራን ላይ ጥቃት ከከፈቱ ከ100 ቀናት በኋላ የአሜሪካ እና የእስራኤል ወታደራዊ እርምጃ እና ፖለቲካዊ ግብ አብሮ መሄዱን በተመለከተ በዋይት ሐውስ ቁጣ ሊፈጥር ይችላል ብለዋል።

የቀድሞው ዲፕሎማት እና የቀውስ ኮሚዩኒኬሽን ኤጀንሲ - ግሎባል ሲቹየሽን ሩም - ፕሬዚዳንት ብሬት ብሩን "ኔታንያሁ ከዋሽንግተን ምንም ዓይነት ነገር ቢሰማም በራሱ የፈለገውን የማድረግ የረዥም ጊዜ ታሪክ አለው" ሲሉም አለመግባባቱ እምብዛም ለውጥ እንደማያመጣ ጠቁመዋል።

"ትራምፕ ከእርሱ ጋር ለማበር ወስነዋል፣ አሁን ላይ አጀንዳቸው ትራምፕ ቅድሚያ ከሚሰጧቸው ጉዳዮች ጋር አብረው ከማይሄዱ ጨካኝ መሪ ጋር ጦርነት ውስጥ ሲገባ ስለሚመጣ ነገር ጥሩ ትምህርት እየወሰዱ ነው" ሲሉም አክለዋል።

ከግራ ወደ ቀኝ) የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዱላህ ቢን ዛይድ አል ናህያን፣ የባህሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዱላቲፍ ቢን ራሺድ አል ዛያኒ እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር በዋይት ሐውስ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, (ከግራ ወደ ቀኝ) የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዱላህ ቢን ዛይድ አል ናህያን፣ የባህሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዱላቲፍ ቢን ራሺድ አል ዛያኒ እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር በዋይት ሐውስ በተካሄደው የአብርሃም ስምምነት የፊርማ ሥነ ሥርዓት ላይ

ኔታንያሁ እና ትራምፕ በአብዛኛው የኢራንን የኒውክሌር ኃይል እንዳታበለፅግ ወይም እንዳትታጠቅ ለማድረግ በሚረዱ የአሜሪካ ቁልፍ ዓላማዎች ላይ ይስማማሉ።

ሆኖም በሊባኖስ ላይ ያላቸው ፍላጎት የተለያየ ሲሆን የአሜሪካ እና የኢራን ድርድር ቢቀጥልም እስራኤል በኢራን የሚደገፈውን የሄዝቦላህ ታጣቂ ዒላማ ለማድረግ እየዛተች ነው።

ኢራን በበኩሏ ማንኛውም የተኩስ አቁም ስምምነት ሊባኖስን ማካተት እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥታለች።

በኔታንያሁ እና በትራምፕ መካከል አለመግባባት መፈጠሩ የተሰማውም አሜሪካ ለረዥም ጊዜ ለእስራኤል እያደረገችው ያለውን ድጋፍ የሚተቹ ዜጎቿ ብዛት እየጨመረ በመጣበት ወቅት ነው።

የሕዝብ አስተያየትን የሚሰበስበው ዋን ኒው የጥናት ተቋም ሚያዝያ ወር ላይ ባካሄደው ጥናት 60 በመቶ የሚሆኑ አሜሪካውያን በእስራኤል ላይ አሉታዊ አመለካከት አላቸው።

በአውሮፓውያኑ በ2023 ከሐማስ ጋር ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት አሉታዊ አመለካከት ያላቸው 42 በመቶ የሚሆኑ አሜሪካውያን ነበሩ።

በርካታ ታዋቂ ወግ አጥባቂዎችም እስራኤል ትራምፕ ወደ ኢራን ጦርነት ተስበው እንዲገቡ በማሳመን ሚና እንዳላት በአደባባይ ተናግረዋል። ይህንን ግን ዋይት ሃውስ እና ኔታንያሁ አስተባብለውታል።

ጦርነቱን ከሚተቹት መካከል የሆኑት እና መጋቢት ወር ላይ ከመልቀቃቸው በፊት የብሔራዊ ፀረ ሽብር ማዕከልን ሲመሩ የነበሩት ጆ ኬንት አንዱ ናቸው።

ጆ ኬንት ሥራቸውን የለቀቁት " ይህንን ጦርነት የጀመርነው ከእስራኤል በመጣ ግፊት እና ጠንካራ ማግባቢያ ነው" ሲሉ አስተያየት ከሰጡ በኋላ ነበር።

የእስራኤል ደጋፊ የሆነው አግባቢ ቡድን - አሜሪካ እስራኤል ፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ- ለኬንት ሥራ መልቀቅ በሰጠው ምላሽ "ፀረ ሴማዊ የሆኑ አረጋውያን ተዋጊዎችን በማዘዋወር" ክስ አቅርቦባቸዋል።

በዚህ የፖለቲካ ምህዳር አንዳንድ ታዛቢዎች ትራምፕ በአገር ውስጥ የሚቀርብባቸውን ትችት ለመግታት ከኔታንያሁ ጋር እንዳይስማሙ ያነሳሳቸው ምክንያት አለ ብለው ያምናሉ።

ብሩን በበኩላቸው "በእስራኤል እና በአሜሪካ መካከል ብርሃን ለመፍጠር አሁን ላይ ፖለቲካዊ አስፈላጊነት አለ" ይላሉ።

" በሊባኖስም ሆነ በጋዛ ኔታንያሁ የመረጧቸው ነገሮች ለትራምፕ ወይም ለሪፐብሊካኖች ችግር የሚፈጥሩ ናቸው።" ብለዋል።

የወደመ አውሮፕላን
የምስሉ መግለጫ, ኢራን ከተነገረው በላይ በአሜሪካ ወታደራዊ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሷን ቢቢሲ አረጋግጧል

ሌሎች የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶችም በኔታንያሁ ስጋት ገብቷቸው ራሳቸውን አግኝተውታል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ከቢል ክሊንተን ጋርም ከኦስሎ የሰላም ስምምነት ጋር በተያያዘ ተጋጭተው ነበር።

ከፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ጋርም እንዲሁ በተለይ የኢራን ፖሊሲን በተመለከተ በአውሮፓውያኑ 2015 በኮንግረንሱ ንግግር ካደረጉ በኋላ አስቸጋሪ ግንኙነት ነበር የነበራቸው። ይህ ንግግራቸው ከዋይት ሐውስ እውቅና ውጭ የተደረገም ነበር።

ኔታንያሁ ከባይደን ጋር ያላቸው ግንኙነትም በተለይ የጦር መሣሪያዎችን እና ጥይቶችን ቀረጥ በማስከፈል አሜሪካ ላይ ክስ ካቀረቡ በኋላ የሻከረ ይመስል ነበር። በወቅቱ ዋይት ሃውስ ክሱን " ግራ የሚያጋባ እና የሚያበሳጭ" ብሎታል።

ተቀማጭነቱን በዋሽንግተን ያደረገው የመካከለኛው ምሥራቅ ተቋም ውስጥ የአሜሪካ እስራኤል ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት ናታን ሳቺስ " ኔታንያሁ ከአሜሪካ ፕሬዚደንቶች ጋር ጥሩ ያልሆነ ግንኙነት ነበረው" ብለዋል።

" በጣም አደገኛ ተደራዳሪ ነው። ጠንካራ ብቻ ሳይሆን ተጠራጣሪም ናቸው" ሲሉም ሳቺስ አክለዋል።

ትራምፕ ቀደም ብሎ ከኔታንያሁ ጋር ያላቸው ግንኙነት ላይ ያላቸውን ስጋት ገልፀው ነበር። ባለፈው ዓመት እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ከፈፀመች በኋላ እና የ12 ቀን ጦርነቱ ማብቃቱን ሲገልጹ ካሜራ ፊት 'ያልተገባ ቃል' ተጠቅመዋል።

ሆኖም በአጠቃላይ ግንኙነታቸው አዎንታዊ ነው። ኔታንያሁ ትራምፕን በአሜሪካ ታሪክ" የእስራኤል ወሳኝ ወዳጅ" ሲሉ በተደጋጋሚ ገልጸዋቸዋል።

"ኔታንያሁ መካከለኛው ምሥራቅ ለማንኮታኮት ፈቃደኛ የሆነ ሰው አግተኝዋል" ብለዋል ሳክስ

"ይህ ደግሞ ኔታንያሁ በቀላሉ የሚደግፉት ነገር ነው፤ የጨዋታን ሕግ መለወጥ እና የኢራንን አከርካሪ በወታደራዊ እርምጃ ለመስበር የአሜሪካ እና የእስራኤል ፈቃደነኝት ይፈልጋል"

በቅርቡ የተፈጠረው አለመግባባት በጊዜ ሒደት ያንን ጥሩ ግንኙነት ይለውጠው እንደሆነ ግልፅ አይደለም።

"በጣም ወሳኝ ነው። የአንድ ጊዜ ክስተት ይሁን ወይም የከፋ አለመግባባት አናውቅም" ብለዋል።

"ይህንን መወሰን አልችልም። ፕሬዚዳንቱ ከዚህ በፊትም ከበርካታ ሰዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት ላይ ሃሳባቸውን ለውጠዋል" ሲሉም አክለዋል።