ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቻይና እና አሜሪካ "አጋር እንጂ ጠላት" እንዳይሆኑ ዢ ጂንፒንግ ጠየቁ
የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ አሜሪካ እና ቻይና "አጋር እንጂ ጠላት" መሆን እንደሌለባቸው ተናገሩ።
ጂንፒንግን "ታላቅ መሪ" ያሉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው የሁለቱ አገራት ግንኙነት "ከመቼውም ጊዜ በላይ የተሻለ" መሆኑን ገልጸዋል።
ትራምፕ እና ጂንፒንግ ከመወያየታቸው አስቀድሞ በቀይ ምንጣፍ ላይ ሲጨባበጡ ታይተዋል።
ውይይታቸው በታሪፍ፣ በቴክኖሎጂ ፉክክር፣ በኢራን ጦርነት እና በታይዋን ጉዳይ ላይ እንደሚያተኩር ይጠበቃል።
የንቪዳ ዋና ሥራ አስጻሚ የንሰን ሁዋንግ እና የዓለም ቁጥር አንድ ባለሃብት ኢላን መስክም ከትራምፕ ጋር በቤጂንግ ተገኝተዋል።
ቻይናውያን ሕጻናት አበባ እና የአሜሪካን ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለቡ ለትራምፕ ደማቅ አቀባበል አድርገዋል።
ፕሬዝዳንት ጂንፒንግ በአሜሪካ እና በቻይና ግንኙነት "ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው" የታይዋን ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ታይዋንን በተመለከተ ከአሜሪካ ጋር "ግጭት" ሊፈጠር እንደሚችል ማስጠንቀቃቸውን የቻይና መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
በሌላ በኩል ከሁለቱ አገራት የተውጣጡ ልዑካን በደቡብ ኮርያ ንግድን በተመለከተ ያደረጉት ውይይት "አወንታዊ ውጤት" እንዳሳየ ተዘግቧል።
የአሜሪካ የግምጃ ቤት ጸሐፊ ስኮት ባሴት ከቻይና ምክትል የንግድ ሚኒስትር ሂ ሊፊንግ ጋር ትናንት ተወያይተዋል።
የቻይና እና የአሜሪካ ባለሥልጣናት ደቡብ ኮሪያ ውስጥ ተገናኝተው ባደረጉት ውይይት አንዳቸው በሌላኛቸው ምርት ላይ የናረ ታሪፍ ላለመጣል ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ትራምፕ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ከቻይናው ፕሬዝዳንት ጋር በመገናኘታቸው "ክብር" እንደሚሰማቸው ተናግረዋል።
"ተግባብተናል። ልዩነቶች ሲገጥሙን ፈትተናቸዋል። እንደዋወላለን። ችግር ገጥሞን እንደነበር ማንም አያውቅም። ለሁሉም ሰው የምናገረው ታላቅ መሪ መሆኑን ነው" ብለዋል ትራምፕ።
ትራምፕ በቤጂንግ ጉብኝታቸው "የዓለም ታላላቅ ነጋዴዎችን" ይዘው መጓዛቸውን ገልጸዋል።
ጂንፒንግ ባደረጉት መክፈቻ ንግግር "መላው ዓለም ውይይታችንን እየተከታተለ ነው" ብለዋል።
ዓለም ያልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ እንዳለች የተናገሩት የቻይናው ፕሬዝዳንት "ዓለም አዲስ መስቀለኛ መንገድ ላይ ደርሷል። ቻይና እና አሜሪካ መሰናክሉን አልፈው አዲስ ግንኙነት ይመሠርቱ ይሆን?" ሲሉ ጠይቀዋል።
በጋራ ዓለም አቀፍ ችግሮችን ለመፍታት እንዲሁም በጥምረት የወደፊቱን ዓለም የተሻለ ለማድረግ መሥራት ይችሉ እንደሆነም ለትራምፕ ጥያቄ አቅርበዋል።
እነዚህ ጥያቄዎች "ለታሪክ፣ ለዓለም እና ለሕዝቦች ጠቃሚ" መሆናቸውን ገልጸው "የሁለት ታላላቅ አገራት መሪ እንደመሆናችን ጥያቄዎቹን መመለስ አለብን" ብለዋል።
ሁለቱ መሪዎች ለሁለት ሰዓት የዘለቀ ውይይት ማድረጋቸው ተዘግቧል።
በውይይታቸው የኢራን ጦርነት ጉዳይም እንደሚነሳ ሲገለጽ ቆይቷል።
ትራምፕ ቤጂንግ ከመድረሳቸው አስቀድሞ ከኢራን ጋር የገቡበትን ጦርነት ለማስቆም የቻይናን እርዳታ እንደማይፈልጉ መናገራቸው ይታወሳል።
ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የምታደርገውን ቁጥጥር እያጠበቀች የመጣች ሲሆን በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበታል።