በኬንያ የነዳጅ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ መደረጉን የተቃወሙ አሽከርካሪዎች ሥራ አቆሙ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ኬንያውያን አሽከርካሪዎች እና የመኪና ባለንብረቶች ባለፈው ሳምንት የተደረገውን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በመቃወም ሥራ በማቆማቸው በሺህዎች የሚቆጠሩ መንገደኞች እና ንግዶች ተስተጓጉለዋል።
በኬንያ ናይሮቢ ዋና ዋና መንገዶች እንቅስቃሴ አልባ ሆነው ያረፈዱ ሲሆን፣ የተወሰኑ መንገደኞች በእግራቸው ከቦታ ወደ ቦታ ለመንቀሳቀስ ተገድደዋል።
በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎችም የትራንስፖርት አገልግሎት በመቋረጡ ሥራ መስተጓጎሉ ተሰምቷል።
በዋና ከተማዋ ናይሮቢ የንግድ ሱቆች የተዘጉ ሲሆን፣ ተማሪዎችም ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ ተደርገዋል።
የመንግሥትን የዋጋ ጭማሪ የተቃወሙ ሰዎች መንገዶችን በድንጋይ በመዝጋት ጎማዎችን አቃጥለዋል።
አሽከርካሪዎች እና የመኪና ባለቤቶች ተቃውሟቸውን የገለጹት ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የነዳጅ ዋጋ ላይ የ20 በመቶ ጭማሪ በመደረጉ ነው።
ኬንያ ነዳጅ የምታስገባው ከባሕረ ሰላጤው አገራት በመሆኑ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ በኋላ አቅርቦቱ ተስተጓጉሏል።
ምንም እንኳን በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተኩስ አቁም ቢደረስም የዓለም አንድ አምስተኛ የሆነው ነዳጅ የሚተላለፍበት ሆርሙዝ አሁንም እንደተዘጋ ይገኛል።
በኬንያ ዋና መዲና ናይሮቢ እና በሌሎች አካባቢዎች ፖሊስ ለተቃውሞ አደባባይ ከወጡ ሠልፈኞች ጋር መጋጨቱን እና ለመበተን አስለቃሽ ጋዝ መጠቀሙ ተሰምቷል።
ይህ የተሰማው አንዳንድ ተቃዋሚ ሠልፈኞች አሽከርካሪዎችን እያስቆሙ ማስፈራራታቸው ከተገለጸ በኋላ ነው።
ከተቃውሞው በፊት ፖሊስ የደኅንነት እና ፀጥታን በሚመለከት ዝግጁ መሆኑን እና ተቃዋሚዎች ሌላውን የሕብረተሰብ ክፍል ከሚያውክ ተግባር እነዲቆጠቡ አስጠንቅቋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የአሽከርካሪዎች እና ተሽከርካሪዎች ማኅበራት ቀደም ሲል የግል አሽከርካሪዎች፣ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች እና የጭነት መኪና አሽከርካሪዎችን ጨምሮ ሁሉም የተሽከርካሪ ተጠቃሚዎች አድማውን እንዲቀላቀሉ እና ከእንቅስቃሴ አንዲቆጠቡ አስጠንቅቀው ነበር።
"ይህ እርምጃ ለትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ብቻ ሳይሆን ለእያንዳንዱ የኬንያ ዜጋ ጭምር ነው" ሲል የትራንስፖርት ሴክተር አሊያንስ (ቲኤስኤ) በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
ጥምረቱ መንግሥት በዚህ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት በተከሰተበ ጊዜ ኬንያውያንን ከነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ለመከላከል በቂ ጥረት አላደረገም ሲል ከስሷል።
ባለፈው ሳምንት የተገለጸውን የዋጋ ጭማሪ እንዲቀለበስ እና የነዳጅ ዋጋ በ35 በመቶ እንዲቀንስ ጥሪ አቅርቧል።
የኢነርጂ እና የነዳጅ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ናፍጣ እና ቤንዚን በአንድ ሊትር ወደ 242 ሽልንግ (1.8 ዶላር እና 1.65 ዶላር) ከፍ አድርጓል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ ጆን ምባዲ ሰኞ ዕለት ለኤንቲቪ እንደተናገሩት የነዳጅ ዋጋ መጨመር "አሳዛኝ" መሆኑን ገልጸው ይህም ኢኮኖሚውን እየጎዳ መሆኑን ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ተቃውሞውን "ፈጽሞ አላስፈላጊ" ሲሉ ጠርተው መንግሥት "ከስሜት ይልቅ በመረጃ ላይ የተመሠረቱ ውሳኔዎችን" ብቻ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
"ለምን አንድን ዓለም አቀፍ ችግር በአገር ውስጥ መንገዶች ለመፍታት እንሞክራለን?" ሲሉም ጠይቀዋል።
የነዳጅ ዋጋ በመጨመሩ የምግብ እና ለሌሎች መሠረታዊ ሸቀጦች እና አገልግሎቶች ዋጋ እንዲጨምር ማድረጉ የተገለጸ ሲሆን፣ የሕዝብ አገልግሎት ተሽከርካሪዎች የመጓጓዣ ዋጋን አስቀድመው ጨምረዋል።
ባለፈው ወር መንግሥት እስከ ሐምሌ ወር ድረስ በነዳጅ ላይ ያለውን የተጨማሪ እሴት ታክስ ከ16 በመቶ ወደ 8 በመቶ የቀነሰ ቢሆንም ተጨማሪ እርምጃዎችን እንዲወስድ ተጠይቋል።














