የዓለም ነዳጅ ዋጋ መጨመርን ተከትሎ የተፈጠሩ ስጋቶች

የነዳጅ ዋጋን የሚያሳይ ግራፊክስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በበርሜል ከ126 ዶላር በላይ በመሸጥ ከዩክሬን ጦርነት ወዲህ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

አሜሪካ እና ኢራን ከሁለት ወር በፊት የገቡበት ጦርነት የመቋጨት አዝማሚያ እያሳየ አለመሆኑን ተከትሎ በዓለም አቀፍ ገበያ የነዳጅ ዋጋ ከአውሮፓውያኑ 2022 ወዲህ ባልታየ ሁኔታ ጨምሯል።

የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋው በሰባት በመቶ ገደማ ጨምሮ በበርሜል ከ126 ዶላር በላይ ተሽጧል። አሁን የተመዘገበው የነዳጅ ዋጋ ሩሲያ ዩክሬን ላይ ሙሉ ወረራ ከከፈተች ወዲህ የታየ ከፍተኛ ጭማሪ ሆኗል።

የአሜሪካው የዜና ምንጭ አክሲዮስ የአሜሪካ ወታደራዊ አዛዦች ኢራን ውስጥ ሊፈጸሙ የሚችሉ "አጭር እና ኃይለኛ" ተከታታይ ጥቃቶችን የተመለከተ እቅድ ለፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሊያቀርቡ መሆኑን ዘግቧል።

አክሲዮስ ለጉዳዮ ቅርበት ያላቸው ምንጮችን ጠቅሶ ያወጣው ዘገባ እንደሚያስረዳው ከሆነ የአሜሪካን መካከለኛው ምሥራቅ ዘመቻዎች የሚመራው ማዕከላዊ ዕዝ አዛዥ በሆኑት አድሚራል ብራድ ኩፐር የሚቀርበው እቅድ የኢራን መሠረተ ልማቶችን ማጥቃትን ሊያካትት ይችላል።

የትራምፕ አስተዳደር ኢራን ላይ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድን እያጤነ ያለው ጥቃት መፈጸም ከቴህራን ጋር የሚደረገው ድርድርን ከገባበት ቅርቃር ያስወጣል በሚል ተስፋ እንደሆነ ተገልጿል።

ይህ የአሜሪካ መንግሥት እርምጃ ተጽዕኖው ከነዳጅ ዋጋ የሚያልፍ ነው። የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ተጽዕኖ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ እያሳረፈው ያለው ተጽዕኖ እየገዘፈ መምጣቱን ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ጦርነቱ ያለው አሉታዊ ተጽዕኖ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ የግብይት ሰንሰለቶችን እያፋለሰ መምጣቱ ጭምር ነው።

ጦርነቱ በዚህ የተነሳ ለዋጋ ንረት መንስዔ መሆኑም እየተነገረ ነው። የኢራን ጦርነት ከሁለት ወራት በላይ ሲዘልቅ፣ ከሰላም ይልቅ ተጨማሪ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ሲሰማ፣ የምርት እና የአገልለግሎት ዋጋዎች ላይ ያልታሰበ ጭማሪ እያስከተለ መጥቷል።

በተለይ ሸቀጣ ሸቀጦች፣ የሕዝብ መጓጓዣዎች የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ላይ ጭማሪው ተስተውሏል።

የኬፕለር ከፍተኛ ተንታኝ የሆኑት ናቬን ዳስ፣ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ተያያዥ የሆኑ ምርቶች፣ የዋጋ ግሽበት በመሠረታዊነት በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል ይላሉ።

አክለውም "ነገሮችን ለማርገብ የምንሰማቸው ትልልቅ የንግግር ዜናዎች ይኖራሉ" ብለዋል።

1. ነዳጅ በጣም ይወደዳል

ይህ የመነሻ ነጥብ ነው። የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ አቅርቦት ላይ ባለ ስጋት፣ በቀጣናው ግጭት ወይም በገበያ ትንበያ ምክንያት ይጨምራል።

የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ለአጭር ጊዜ ወደ 7 በመቶ ገደማ ከፍ ብሎ በአንድ በርሜል ከ126 ዶላር በላይተሽጧል።

የሰላም ጥረቶች ሳይሰምሩ በመቅረታቸው የተነሳ እና የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ በመዘጋቱ በዚህ ሳምንትም የነዳጅ ዋጋ ጨምሯል።

ይህም ለአሽከርካሪዎች የነዳጅ ዋጋ እንዲጨምር አድርጓል።

አሜሪካ እና እስራኤል ቴህራን ላይ ጥቃት ከመክፈታቸው በፊት የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በአንድ በርሜል 70 ዶላር አካባቢ ነበር። ይህ ማለት ሐሙስ ዕለት ከተሸጠበት ዋጋ በ80 በመቶ ያነሰ ነበር።

ድፍድፍ ነዳጅ ቤንዚን እና ናፍጣን ለማምረት ቁልፍ ነው። ይህም ማለት ከፍ ያለ የዋጋ ጭማሪ በሌሎቹም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል።

አሁን የሚገዛው የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ በሰኔ ወር የሚረከብ ሲሆን ውሉም ሐሙስ ዕለት እኩለ ለሊት ላይ ያበቃል። በተመሳሳይ ሁኔታ ለሐምሌ ወር የሚደረገው ግብይት በበርሜል 110 ዶላር ሆኗል።

የወደፊት የውል ስምምነቶች አንድን ንብረት ወደፊት በሚመጣው ቀን በተወሰነ ዋጋ ለመግዛት ወይም ለመሸጥ የሚደረጉ ስምምነቶች ናቸው።

2. ከነዳጅ ጋር ተያያዥ የሆኑ ምርቶች መናር

የእርሻ ቦታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በሆርሙዝ ወሽመት መዘጋት፣ በዓለም ነዳጅ ዋጋ መናር ምክንያት የዓለም ግብርና ይሽመደመዳል የሚል ስጋት ተፈጥሯል

ነዳጅ ለተለያዩ ምርቶች ቁልፍ ግብዓት ነው። በዚህም ምክንያት ከፍተኛ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ መጨመር እንደ የአውሮፕላን ነዳጅ፣ ፕላስቲኮች፣ ማሸጊያዎች፣ ኬሚካሎች እና ማዳበሪያዎች ባሉ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ከፍተኛ የምርት ወጪን ያስከትላል።

መንግሥታት በጦርነቱ ምክንያት የተነሳ እያንዳንዱ ቤት ከፍተኛ የኃይል ወጪ፣ የምግብ ዋጋ መናር እና የአውሮፕላን ትኬት ዋጋ መጨመር ሊገጥመው እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

አንዳንድ አየር መንገዶች አስቀድመው የዋጋ ጭማሪ ወይም የበረራ መስመሮችን መሰረዝ ጀምረዋል። የማዳበሪያ ዋጋዎችም እየጨመሩ ሲሆን ይህም በመጨረሻ ወደ ከፍተኛ የምግብ ወጪዎች ሊሸጋገር ይችላል።

የኢንቨስትመንት አማካሪ የሆነችው ሱዛና ስትራይተር የዋጋ ጭማሪዎች እስከሚቀጥለው ዓመት ድረስ ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ትናገራለች።

የዓለም ግብርና ግብዓትነት በብዛት የሚጠቀምበት ዩሪያ ግማሽ ያህሉ በሆርሙዝ ወሽመጥ አድርጎ ወደ ሌሎች አገራት የሚጓጓዝ በመሆኑ ለከፋ መስተጓጎል ተጋልጧል።

"የባሕር መስመሩ በመዘጋቱ ዩሪያ የተባለውን የአፈር ማዳበሪያ ማጓጓዝ አልተቻለም። በዓለም ዙሪያ ያሉ ገበሬዎች አስቀድመው ካልገዙ በስተቀር ዋጋ ጨምሮባቸዋል" ትላለች።

"ጭንቀቱ እነዚህ ወጪዎች ወደ አቅርቦት ላይ መተላለፋቸው ነው። የዕለት ተዕለት ፍጆታዎች ላይ የሚታየው ጭማሪ ከዚህ ዓመት ባሻገር ወደሚቀጥለው ዓመት ሊሸጋገር ይችላል።"

3. መጓጓዣ የበለጠ ውድ ይሆናል

ነዳጅ በፕላስቲክ የሚቀዳ ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, Saqib Majeed / SOPA Images / LightRocket via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በኢራን ጦርነት የተነሳ በሕንድ ካሽሚር ግዛት ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት ተከስቷል

የዓለም ሕዝብ ሕይወት፣ ምግብ፣ የፍጆታ እቃዎች እና ጥሬ እቃዎች የተመሰረቱት በመጓጓዣ ላይ ነው። ከፍተኛ የነዳጅ ዋጋ የመጓጓዣ ወጪን ይጨምራል።

ሸቀጦችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማጓጓዝ ውድ በሚሆንበት ጊዜ፣ ንግዶች እነዚህን ወጪዎች ወደ ሸማቾች ያስተላልፋሉ። ይህም በችርቻሮ ዋጋዎች ላይ ተጨማሪ ጫና ይፈጥራል።

4. የዋጋ ግሽበት መናር

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የነዳጅ ዋጋን ተከትሎ እየጨመረ የሚሄደው ወጪ በዓለም አቀፍ ምጣኔ ሃብት ውስጥ ቀስ በቀስ ይከማቻል።

የኢነርጂ ዋጋ እየጨመረ ሲሄድ፣ ንግዶች ከፍተኛ የማንቀሳቀሻ ወጪዎች ያስፈልጋቸዋል። ፋብሪካዎችን ከማንቀሳቀስ እስከ እቃዎችን ማጓጓዝ ድረስ ያሉ ከፍተኛ የሥራ ማስኬጃ ወጪዎች ያጋጥሟቸዋል።

የምግብ ዋጋም ይጨምራል። ምክንያቱም እርሻ፣ ማሸጊያ እና ስምሪት የሚመሰረተው ከነዳጅ ዘይት ጋር በተያያዙ ነዳጅ እና ማዳበሪያዎች ላይ ነው።

ከአልባሳት እስከ ኤሌክትሮኒክስ ያሉ የዕለት ተዕለት ምርቶች በተመሳሳይ መልኩ ለማምረት እና ለማድረስ የበለጠ ውድ ይሆናሉ።

እነዚህ የዋጋ ንረቶች በአንድ ጊዜ በበርካታ ዘርፎች እየታዩ ሲሄዱ፣ የዋጋ ጫናዎች በስፋት እና በተከታታይነት እየጨመሩ ይሄዳሉ።

ይህ አዝማሚያ የአጭር ጊዜ ጭማሪ ከመሆን ይልቅ በጊዜ ሂደት ሲቀጥል፣ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በአጠቃላይ የኑሮ ውድነት ላይ ቀጣይነት ያለው ጭማሪ ወይንም የዋጋ ግሽበት ብለው ይገልጹታል።

ብራዚላዊ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ አንድሬ ፐርፌቶ "መላው ዓለም ይህ እያጋጠመው ነው። አንዳንድ አገሮች የበለጠ፣ ሌሎች ደግሞ ያነሰ" ሲሉ ተናግረዋል።

"ለምሳሌ ብራዚል ብዙ እየተሰቃየች ነው" የሚሉት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው በቅርብ ወራት ውስጥ የአገሪቱ የዋጋ ግሽበት ማዕከላዊ ባንክ ከገመተው በላይ መሆኑን አስረድተዋል።

እአአ በ2025 አጋማሽ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ከ5 በመቶ በላይ ከደረሰ በኋላ፣ የብራዚል ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት ቀስ በቀስ እየቀነሰ ቢመጣም በ2026 መጀመሪያ ላይ ከ4.3–4.4 በመቶ አካባቢ ደርሶ ነበር።

የአገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ የቅርብ ጊዜ ትንበያ በመካከለኛው ምሥራቅ በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት የአገሪቱ ግሽበት 4.86 በመቶ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ይህ ግን የብራዚል ብቻ ሳይሆን በርካታ አገሮችም ተመሳሳይ ነገር ገጥሟቸዋል።

5. በዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ ያለው ተጽዕኖ

በነዳጅ ማምረቻ አካባቢ የምትጠልቅ ፀሐይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ባለሙያዎች እና ተቋማት የነዳጅ ዋጋ መጨመር ዓለም አቀፍ የገበያ መውደቅ ያስከትላል የሚል ስጋት አላቸው

የነዳጅ ዋጋ መናር በእያንዳንዱ ቤተሰብ በዕለት ተዕለት ኑሮ ውስጥ በብዙ መንገዶች ይታያል። የፍጆታ እቃዎች ይንራሉ፤ የመጓጓዣ ወጪዎች የበለጠ ይወደዳሉ፤ እና የመገልገያ ወጪዎች ይጨምራሉ።

የኑሮ ውድነት እየጨመረ ሲሄድ፣ ሠራተኞች ከፍተኛ የደሞዝ ጭማሪ በመጠየቅ የዋጋ ግሽበቱ ላይ ጫና ሊፈጥሩ ይችላሉ።

ይህም ተጨማሪ የዋጋ ግሽበት ጫና ሊጨምር ይችላል። በምላሹም ማዕከላዊ ባንኮች የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር የወለድ መጠንን ሊጨምሩ ይህም የቤት ብድር እና ብድርን የበለጠ እንዲወደድ ያደርገዋል።

እንደ ፓኪስታን እና ባንግላዲሽ ባሉ አንዳንድ አገሮች መንግሥት ነዳጅ ለመቆጠብ እና ወጪዎችን ለመቀነስ ትምህርት ቤቶችን ዘግቷል።

"ይህ ሁሉ ለዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ውድቀት ቦታ እየፈጠረ ነው" ይላሉ ፐርፌቶ።

"የአጭር ጊዜ መፍትሄን በተመለከተ ብዙ የምናስብበት መንገድ የለም። ትራምፕ ቢያንስ ለጊዜው ይህንን ይፈታሉ ብዬ አላምንም" በማለት አክለዋል።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) በቅርቡ ባወጣው የዓለም ኢኮኖሚ ምልከታ ሪፖርት የኢራን ግጭት የዓለም ኢኮኖሚን ​​"ከመስመር ውጪ" እንደሚያደርገው አስጠንቅቋል።

ይህም ለረዥም ጊዜ እየጨመረ የመጣው ውጥረት የዓለም ኢኮኖሚን የማናጋት አቅሙን እንደሚጨምር አስጠንቅቋል።

በተጨማሪም ማዕከላዊ ባንኮች ለሚፈጠረው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ምላሽ ለመስጠት የወለድ መጠንን ከፍ እንዳያደርጉ አሳስቧል።

ይሁን እንጂ የአሜሪካ የግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሴንት ለቢቢሲ "ለሳምንታት በሚቆይ ትንሽ የኢኮኖሚ ጫና" የኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ማምረት መግታት ከቻልን ተገቢ ነው ብለዋል።

ኃላፊው አክለውም "ለረጅም ጊዜ ደህንነት ሲባል የአጭር ጊዜ ትንበያዎች ብዙም አያስጨንቁኝም" ብለዋል።