ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ መርከብ ከአራት ወራት ገደማ በኋላ ከሆርሙዝ ወሽመጥ ወጥታ ወደ ጂቡቲ ጉዞ ጀመረች
በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል መተላለፊያ አጥታ የነበረችው 'ኤምቪ ጊቤ' የተባለች የኢትዮጵያ የጭነት መርከብ ጉዞ መጀመሯ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አስታወቀ።
በየካቲት መጨረሻ የባሕረ ሰላጤው ጦርነት መጀመሩን ተከትሎ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በመዝጋቷ መርከቧ አራት ወራት ለሚጠጋ ጊዜ ቆማ እንደነበር የተቋሙ ማርኬቲንግ መምሪያ ኃላፊ እና የኮሚዩኒኬሽን ተወካይ ኃላፊ የሆኑት አቶ ደምሰው በንቲ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አቶ ደምሰው እንደሚናገሩት መርከቧ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ሻርጃ ወደብ በመነሳት ጉዞ የጀመረችው አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ ጥቃት መፈጸም በመጀመሩበት የካቲት 21/2018 ዓ.ም. ነበር።
23 መርከበኞችን ይዛ የነበረችው መርከብ የሕክምና መሳሪያዎች እና ፍራ ፍሬዎችን ጨምሮ የተለያዩ "ኮንቴይነራይዝድ የሆኑ ጭነቶችን" ይዛ እንደነበረም ገልጸዋል።
"ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አጋጣሚ ያ ክስተት ሲፈጠር በዚያው ቦታ ላይ ልትቆም ተገድዳለች" ያሉት የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊው፤ "አራት ወር ሊሞላት ምናልባት ሦስት ወይም አራት ቀናት" ቀርቶ እንደነበርም አስታውሰዋል።
መርከቧ በቆመችባቸው ወራት ውስጥ በኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ እንዲሁም "በጊቤ መርከበኞች መካከል ተከታታይ ግንኙነት" እንደነበረ አስረድተዋል።
"ግንኙነታችን አልተቋረጠም። በየጊዜው እንገናኛለን። የሚያስፈልጋቸውን ነገር በወቅቱ ይዘው ነበረ የወጡት። ግን እንደ አስፈላጊነቱ ደግሞ ባስፈለገ ጊዜ አስፈላጊውን ነገር እንዲያገኙ… ስናደርግ ነው የቆየነው" ሲሉም አብራርተዋል።
እንደ ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊው ገለጻ መርከቧ "ምግብ እና ሌሎች አስፈላጊ" ነገሮችን ጭና ስለነበር አራት ወራት በሚጠጋው የባሕርተኞቹ ቆይታ "ያጋጠመ ችግር የለም።"
ይሁን እንጂ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ መቆየት በራሱ "ከባድ" እንደነበር አንስተዋል።
'ጊቤ' መርከብ በአሁኑ ሰዓት "በሰላም ከአካባቢው መውጣቷን" እና በኦማን ባሕረ ሰላጤ ላይ እየቀዘፈች መሆኑንም አስታውቀዋል።
መርከቧ "የተወሰነ የባሕር ላይ እንቅስቃሴ ካላስቸገራት በስተቀር" ከሁለት ሳምንት ገደማ በኋላ በመጪው "ሰኔ 30" ገደማ ወደ መዳረሻዋ የጂቡቲ ወደብ ትደርሳለች ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
መርከቧ በምን አግባብ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ማለፍ እንደቻለች የተጠየቁት የኮሚዩኒኬሽን ተወካይ ኃላፊው አቶ ደምሰው "ይህ የፖሊሲ አውጪዎች" ጉዳይ መሆኑን በመጥቀስ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
አሜሪካ እና ኢራን ለሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት ምክንያት የሆነውን ጦርነት ለማቆም በር የሚከፍት የመግባቢያ ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ቅዳሜ ዕለት ብቻ 42 መርከቦች እንዳለፉ የደኅንነት መረጃ ተቋም ከሆነው 'ክፕለር' የተገኘ ዳታ አሳይቷል።
ከዓለም የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ውስጥ 20 በመቶ የሚጓጓዝበት ሆርሙዝ ወሽመጥ ከመዘጋቱ በፊት በየቀኑ 138 ገደማ መርከቦች ይተላለፉበት ነበር።
ኢራን ወሽመጡን ከዘጋች በኋላ 1,150 የጭነት መርከቦች እና ከ20 ሺህ በላይ የመርከቦቹ ሠራተኞች ለወራት ቆመው ለመጠበቅ ተገድደዋል።