የህወሓት ሊቀ መንበር ደብረፅዮን እየተካሄደ ስላለው ጦርነት ምን ተናገሩ?

የፎቶው ባለመብት, Tigrai TV
የህወሓት ሊቀ መንበር የሆኑት ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በተለያዩ ቦታዎች አዲስ ጦርነት መጀመሩን ተናግረዋል።
ደብረፅዮን (ዶ/ር) በትግራይ ቴሌቪዥን በተላለፈ መግለጫቸው የትግራይ ሕዝብ "የፖለቲካ ልዩነቶቹን ወደ ጎን ትቶ ለኅልውናው እንዲቆምም" አሳስበዋል።
ደብረፅዮን ትናንት መስከረም 21/2019 ዓ. ም. ምሽት በሰጡት መግለጫ፤ በውጊያው ያለውን ወታደራዊ ሁኔታ ሲያብራሩ የትግራይ ጦር "በተለያዩ አካባቢዎች እየተዋጋ መሆኑን" ገልጸዋል።
አያይዘውም ውጊያው "ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀስ" እንደሆነ ጠቅሰው፤ የፌዴራል ኃይሎች የትግራይን "አንዳንድ ክፍሎች ሊይዙ እንደሚችሉ" ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ይህ "ሆነ ተብሎ የተደረገ ስትራቴጂካዊ እርምጃ" መሆኑን ገልጸዋል።
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተጠናክሮ በቀጠለበት እና የፌደራል መንግሥቱ እና አጋሮቹ የህወሓት ታጣቂዎች ይዘዋቸው የነበሯቸውን አንዳንድ ስፍራዎች ማስለቀቃቸው በተሰማበት ወቅት መግለጫ የሰጡት ደብረፅዮን "ጠላትን የምንወጋው እሱ በመረጠልን ቦታ ሳይሆን እኛ በመረጥነው ቦታ ነው" ብለዋል።
ደብረፅዮን ውጊያውን ከስድስት ዓመታት በፊት በተካሄደው ጦርነት ወቅት ከነበረው 'አሉላ ኦፕሬሽን' እንዲሁም ከቀደሙት 17 ዓመታት የትጥቅ ትግል ልምድ ጋር አያይዘው ገልጸዋል።
"ጉዞው ረዥም እና መስዋዕትነት የሚጠይቅ ቢሆንም፣ የትግራይ ኃይሎች በወታደሮች ብዛት ወይም በጦር መሣሪያዎች አልተሸነፉም ብለዋል"።
በሌላ በኩል ከህወሓት ተነጥሎ የወጣው 'የትግራይ የሰላም ኃይል' አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ገብረእግዚአብሔር በየነ ቲቢኤስ ለተባለው የዩቲዩብ ሚዲያ "ጦራቸው እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በርካታ የትግራይ አካባቢዎችን ተቆጣጥረው እንደነበር" ተናግረዋል።
"አብዛኛዎቹ የራያ አካባቢዎች እና አንዳንድ የእንደርታ፣ የሰማር እና የተምቤን አካባቢዎች በቁጥጥር ሥር መዋል ጀምረዋል" ብለዋል።
አክለውም "በቅርቡ ወደ ትግራይ መሃል እንገባለን" በማለት ሚሊሻዎች እና ፖሊሶች ሰላምን በማረጋገጥ እና የሰዎችን ንብረት በመጠበቅ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
ቢቢሲ ሁለቱም ወገኖች የተናገሩትን በገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም።
የህወሓት ሊቀ መንበር ደብረፅዮን፤ በቅርቡ ህወሓትን ጨምሮ ስምንት ታጣቂ ቡድኖች የፌዴራል መንግሥትን ለመጣል የፈጠሩትን ጥምረት በማመልከት ጦርነቱን "ከአጋሮች ጋር የተደረገ" ሲሉ ገልጸውታል።
ግጭቱ ቀይ ባሕርን "ለመቆጣጠር" ከሚደረገው ጥረት እና ከሱዳን "ጣልቃ ገብነት" ጋር የተያያዘ መሆኑን አክለዋል።
"ይህ ጦርነት የአብይ አሕመድ ብቻ አይደለም" ያሉት ደብረፅዮን የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን ጨምሮ ሌሎችም አገራት በጦርነቱ ውስጥ ተሳትፈዋል ሲሉ ከሰዋል።
ሆኖም ግን ቢቢሲ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን እና ሌሎች አካላትን ጣልቃ ገብነት በተመለከተ የተሰነዘረውን ክስ ማረጋገጥ አልቻለም።
ከኢትዮጵያ መንግሥትም ምንም ዓይነት ይፋዊ ምላሽ አልተገኘም።
የኢትዮጵያ መከላከያ ኤታማዦር ሹሙ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ "እየተዋጋን ያለነው የውጪ ኃይሎችን ፍላጎት ለማስፈጸም ከተሰባሰቡ እና ከተደራጁ ኃይሎች ጋር ነው" ብለው ነበር።
"ሻዕቢያ [ኤርትራ] እና ቲፒኤልኤፍ [ህወሓት] ያለ ሱዳን፣ ያለ ግብፅ እና ከዚያም ባሻገር ያሉ ኃይሎች ካልደገፏቸው ብቻቸውን ተጣምረውም ቢሆን ዋጋ የላቸውም። ሲነጣጠሉ ደግሞ ትርጉም የላቸውም" ሲሉ ተናግረዋል።
የኤርትራ መንግሥት በበኩሉ ብዙም ባልተለመደ መልኩ ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ ሰባት ታጣቂ ቡድኖች የመሠረቱትን ጥምረት በመደገፍ የቀረበበትን ክስ ውድቅ አድርጓል።
በኢትዮጵያ የተከሰሰችው ሌላኛዋ አገር ግብፅ፤ ኢትዮጵያ "የውጭ ኃይሎችን ለውስጣዊ ውድቀቶቿ እና ዘላቂ ቀውሶቿ ተጠያቂ ታደርጋለች" ስትል ወንጅላለች።
ኢትዮጵያ የግብፅ ዲፕሎማት አሕመድ ሞሐራን አሕመድ ሶሊማን በ48 ሰዓታት ውስጥ ከአገር እንዲወጡ ስትወስን ግብፅም የአጸፋ እርምጃ መውሰዷን አስታውቃለች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ባወጣው መግለጫ ዲፕሎማቱ ከአገር እንዲወጡ የተወሰነው "ዲፕሎማሲያዊ ጥሰት" በመፈጸማቸው መሆኑን አመልክቷል።
የግብፁ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን መና እንደዘገበው፤ ካይሮ የኢትዮጵያን ውሳኔ "አሳዛኝ" እና "ምክንያታዊ ያልሆነ" ስትል ኮንናለች።
ግብፅ በካይሮ ያሉት የኢትዮጵያ ዲፕሎማት በ48 ሰዓታት ውስጥ ከአገር እንዲወጡ አሳስባለች።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በኤርትራ መዲና አሥመራ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ለመዝጋት መወሰኗን እና 10 የኤርትራ ዲፕሎማቶች ከአገሪቱ እንዲለቁ ትዕዛዝ መስጠቷን ተከትሎ፤ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉንም የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች ማቋረጧን አስታውቃለች።
ኢትዮጵያ ይህንን እርምጃ የወሰደችው ኤርትራ "ቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ" በሆነ መንገድ ለምትፈፅመው "የጠብ ጫሪነት እና የትንኮሳ" ድርጊቶች ምላሽ ለመስጠት እንደሆነ ተገልጿል።
የኤርትራ ኤምባሲ ይህንን ተከትሎ ትናንት ባወጣው መግለጫ፤ ኢትዮጵያ "እነዚህን ያልተገቡ የጠብ አጫሪነት ድርጊቶች ምክንያታዊ ለማድረግ ኤርትራን ከስሳለች" ብሏል።
ኤምባሲው "ላለፉት ሦስት ዓመታት ኢትዮጵያ የኤርትራ ወደቦችን እና የባሕር ዳርቻዎችን በመውረር፣ ባሕር በር ማግኘት ግዴታ ነው ስትል በአደባባይ ጦርነት በማዋጅ በኤርትራ ላይ የማያባራ የጥላቻ አጀንዳ ስታራምድ የቆየችው ኢትዮጵያ ናት" ሲልም ከስሷል።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ግብፅ መካከል የተካረረው ውጥረት እንዳሳሰበው ገልጿል።
ሦስቱ የኅብረቱ አባል አገራት "ውጥረቱን ከሚያካርሩ እንዲሁም የቀጣናውን ሰላም እና መረጋጋት ከሚያናጉ ድርጊቶች እና መግለጫዎች እንዲቆጠቡ" አሳስቧል።
ሦስቱ አገራት ልዩነታቸውን በአፍሪካ ኅብረት መርሕ መሠረት "በዲፕሎማሲያዊ መስመሮች እና በሰማላዊ ንግግር እንዲፈቱ" ኮሚሽኑ አሳስቧል።

የፎቶው ባለመብት, ETV
እንደ አዲስ የተቀሰቀሰው ጦርነት በንጹኃን ዜጎች እና በመሠረተ ልማት ላይም ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው።
ደብረፅዮን ትናንት በሰጡት መግለጫ "የፌዴራል ኃይሎች የእህል መኪናዎችን ማቃጠላቸውን እና በሲቪሎች ላይ ግድያ መፈፀማቸውን" ቀጥለዋል ሲሉ ከሰዋል።
በትግራይ የቴሌኮም እና የኢንተርኔት አገልግሎቶች ተቋርጠዋል።
ሕዝቡ ከዚህ ቀደም በነበረው የእርስ በርስ ጦርነት እንደነበረው ሁሉ የእንቅስቃሴ ገደብን በመፍራት መሠረታዊ ሸቀጦች በብዛት እየሸመተ እንደሆነ ተዘግቧል።
በአላማጣ እና አካባቢው ደረሰ በተባለ የከባድ መሣሪያ ጥቃት ባለፉት ሦስት ቀናት ብቻ ቢያንስ ከ50 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪ እና አንድ የሆስፒታል ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ነዋሪዎቹ በአላማጣ እና አካባቢው ከመስከረም 16 እስከ 19፣ 2019 ዓ.ም. ድረስ ከባድ ውጊያ መካሄዱን ጨምረው ገልጸዋል።
ከመስከረም 12 እስከ መስከረም 15፣ 2019 ዓ. ም. ድረስ በኮረም እና አላማጣ ሆስፒታሎች የገቡ ታካሚዎች ቁጥር በ48 ሰዓታት ውስጥ ከ180 ወደ 420 ከፍ ማለቱን ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) ገልጿል።
በተቋሙ ድጋፍ መስከረም 15፣ በሰሜን ምዕራብ ትግራይ፣ ሽረ ወደሚገኘው ስኹል ሆስፒታል የገቡ በጦርነት የተጎዱ ታካሚዎች ከ300 በላይ እንደሚሆኑ አስታውቋል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሰብአዊ ቀውስ እየተባባሰ ሲመጣ ግጭቱ በአስቸኳይ እንዲቆም ጥሪ ማቅረቡን ቀጥሏል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በትግራይ ውስጥ ያለውን ውጥረት ለማርገብ "እርምጃ እንዲወስድ" ለአገሪቱ ሕግ አውጪዎች ጥያቄ አቅርበዋል።
የአውሮፓ ኅብረት እና የተባበሩት መንግስታትም አዲሱ ጦርነት ከሁለት ዓመት በፊት በፕሪቶሪያ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት አደጋ ላይ እንደሚጥል በመግለጽ ስጋታቸውን አስተጋብተዋል።
ውጊያው በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር አዋሳኝ አካባቢዎች ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን ከትናንት በስትያ ረቡዕ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ሦስት ግለሰቦች ሌሊት ከ6 ሰዓት በኋላ ከባድ ፍንዳታ መስማታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ፍንዳታው መድረሱ የተሰማው የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት በአዲስ አበባ እና አካባቢው ከረቡዕ ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ማንኛውንም ድሮን ለማብረር ፈቃድ እንደማይሰጥ ካስታወቀ በኋላ ነው።



































