የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዕቅድ፡ የባሕር በር ማግኘት፣ ሕገ መንግሥት ማሻሻል እና ሌሎችም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ለቀጣይ አምስት ዓመታት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው እንዲቀጥሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተሰየሙ በኋላ ዐቢይ አሕመድ ባደረጉት ንግግር መንግሥታቸው ያከናውናቸዋል ያሏቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች አንስተዋል።

በዚህም ባለፉት ዓመታት በእርሳቸው መሪነት ኢትዮጵያ ሉዓላዊ የባሕር በር እንድታገኝ ሲደረግ የነበረው ጥረት እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአሁኑ ወቅት "ጠላቶቻችን" ያሏቸው በስም ያልጠቀሷቸው አካላት ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር አካባቢ ሚና እንዳይኖራት ለማድረግ እየጣሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ዐቢይ "የጠላቶቻችን ትኩረት ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር እንዳትነግሥ መገደብ ብቻ ሆኗል. . . [አገሪቱን] የማፍረስ ነገር ቅዠት ሆኖባቸዋል" ብለዋል።

አክለውም ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጥያቄዋ መልስ የሚያገኘው "በሰጥቶ መቀበል" መርኅ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

"የኢትዮጵያ ዘላቂ ችግር የሚፈታው ኢትዮጵያ ሥልጣኔ ስትገነባ ብቻ ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ያለ ባሕር በር "እውን አይሆንም" ብለዋል።

መንግሥታቸው ባለፉት ዓመታት አጥብቆ ይዞት የነበረውን የባሕር በር ጥያቄ አሁንም እንደሚገፋበት እና "ኢትዮጵያ ወጥቶ መግቢያ በር እንዲኖራት" በቀጣይ የሥልጣን ዘመናቸው ተግተው እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል።

የሕገ መንግሥት ማሻሻያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አዲስ በሚመሠርቱት አስተዳደራቸው በቀጣይ ዓመታት ይከናወናሉ ካሏቸው ተግባራት መካከል በአገሪቱ ሕገ መንግሥት ላይ የሚደረጉ ማሻሻያዎች እንደሚገኝበት አመለክተዋል።

ከኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተገኙ የአጀንዳ ነጥቦች እና ምክረ ሐሳቦች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለፌደራል መንግሥቱ እንዲሁም ለክልል መንግሥታት መቅረባቸው ይታወሳል።

በእነዚህ ምክረ ሐሳቦች መሠረትም ከሦስት አሥርት ዓመታት በላይ በሥራ ላይ በቆየው የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ላይ ማሻሻያዎች እንደሚደረጉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በቀጣዩ የሥራ ዘመን ይከናወናሉ ካሏቸው ተግባራት መካከልም ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በጋራ መሥራት ይገኝበታል።

በምርጫው ንቁ ተሳትፎ ከነበራቸው ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመሥራት "መንግሥት ዝግጁ ነው" ብለዋል።

አክለውም መንግሥታቸው "የውይይት እና የይቅርታ መንገድ ይከተላል" በማለት ለሌሎችም ኃይሎች በራቸው ክፍት መሆኑን አመልክተዋል።

በሌላ በኩል የመገናኛ ብዙኃን ምኅዳሩ "ሕግ፣ አገራዊ እሴት እና ፍላጎትን ባከበረ መልኩ እንዲንቀሳቀስ ይደረጋል" ብለዋል።

ኢትዮጵያ እና ቀጣናው

ጠቅላይ ሚኒስር ዐቢይ ዛሬ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር በአፍሪካ ቀንድ፣ በቀይ ባሕር፣ በፋርስ ባሕረ ሰላጤ እንዲሁም በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን "የለውጥ ማዕበል" ያነሱ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በቀጣናው "አንከር" [ወሳኝ] አገር የመሆን ሚና እንዳላት ደጋግመው ተናግረዋል።

በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ እያካሄደችው ባለው ለውጥ ደስተኛ ያልሆኑ ወገኖች እንቅፋት እየፈጠሩባት መሆናቸውን ነገር ግን የአገሪቱ "ትንግርታዊ ጉዞ" መቀጠሉን ጠቅሰዋል።

"የኢትዮጵያ ለውጥ ያስደነገጣቸው አካላት በክፉ ዐይናቸው ያዩን ጀመር" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "ባልበላው ጭሬ አፈርሰዋለሁ ብለው ተነሱ. . . ከሮጠች አንይዛትም ብለው ተነሱ" ሲሉም ተደምጠዋል።

"የውስጥ ተላላኪ" እና "የውጭ ተላላኪ" ያሏቸው ኃይሎች "አብረው እንደተነሱ" ጠቅሰውም "ብዙ ደከሙ፣ ተሟሟቱ. . . ኢትዮጵያን ግን አልቻሉዋትም፤ አይችሏትም" ብለዋል።

"ውድቀቷን ሲመኙ ትነሳለች፤ ተበተነች አለቀላት ብለው ሳይጨርሱ ተሰብስባ ትገኛለች፤ የኢትዮጵያ ነገር ትንግርት ነው" ሲሉም አክለዋል።

ኢትዮጵያ በቀጠናው የምትወስን አገር መሆኗን "በሰዎች ችሮታ ሳይሆን በጉልበቷ ታረጋግጣለች. . . ዳግም ፍላጎቶቿን በራሷ መንገድ ታረጋግጣለች" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የሰላም ጥሪ

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ዳግመኛ በተቀሰቀሰበት ወቅት ለቀጣይ አምስት ዓመታት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ዐቢይ ባደረጉት ንግግር፤ አገሪቱ ፈተናዎችን የማለፍ አቅም እንዳላት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ባላንጣዎቻችን ተከፋፍለው ሊያጠቁን ሲከብዳቸው ለክፋት ተጣመሩ" በማለት በቅርቡ ተመሠረተ የተባለውን የታጣቂዎች ትብብር በተዘዋዋሪ ተችተዋል።

ነገር ግን አሁንም የመንግሥታቸው የሰላም እጅ እንደተዘረጋ መሆኑን በመጠቆም "በጫካ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ወደ ሰላም መንገድ ኑ" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ባለፉት ወራት የኢትዮጵያ መንግሥት በቀጣናው ካሉ አገራት አንዳንዶቹ ታጣቂዎችን እንደሚረዱ በመጥቀስ ሲከስስ የነበረ ከመሆኑ በተጨማሪ ከኤርትራ እ ናከግብፅ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ፍጥጫ ውስጥ መግባቱ ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ኢትዮጵያ ከቀጣናው ጎረቤት አገራት ጋር በትብብር እንደምትሠራ ጠቅሰው፤ "የውጭ ግንኙነታችን የኢትዮጵያን ተጽዕኖ በሚያሳይ መንገድ ይሆናል" ሲሉ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በከፍተኛ ሁኔታ የመከላከያ ኃይሏን እየገነባች መሆኑን እንዲሁም ወቅታዊ ሁኔታን ባገናዘበ መልኩ የአየር ኃይልን ጨምሮ ዘመናዊ የመከላከያ ኃይል እያሳደገች መሆኗን ጠቅሰዋል።