ቀጥታ, የየመን መንግሥት የሁቲ ታጣቂዎች ላይ ሁሉን አቀፍ ጦርነት ማወጁን አስታወቀ

ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው የየመን መንግሥት መሪ ሁቲዎች የያዝዋቸውን ግዛቶች ለማስለቀቅ ሁሉን አቀፍ ጦርነት ማወጃቸውን አስታወቁ። የየመን መንግሥት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በሳዑዲ በሚመራው ጥምረት እና በሁቲዎች መካከል የተኩስ ልውውጥ ከተደረገ በኋላ ነው። የየመኑ ፕሬዝዳንት ራሻድ አል-አሊሚ እሁድ ዕለት በቴሌቪዥን ባደረጉት ንግግር "ዛሬ፣ የሪፐብሊኩን ቀሪ ግዛት መልሶ ለመቆጣጠር እንዲሁም የመንግሥትን እና የተቋማቱን ሥልጣን በመላው አገሪቱ ለማስፋት የሚያስችሉ ወታደራዊ ዘመቻዎች መጀመራቸውን አበስራለሁ" ብለዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ኢራን፣ ዋሽንግተን ወረራ ከፈጸመችባት የአሜሪካን ጦር ሠፈሮች እና የጦር መርከቦችን እንደምታጠቃ ዛተች

    የኢራን ሚሳዔል

    ዋሽንግተን ቴህራን ላይ ወረራ የምትፈጽም ከሆነ ኢራን ሁሉንም የአሜሪካ ጦር ሠፈሮች እና መርከቦችን እንደምታጠቃ የኢስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ኃይል ከፍተኛ አዛዥ አስጠነቀቁ።

    የአብዮታዊ ዘቡ ዋና አዛዥ አማካሪ አሊ ፋዳቪ እሁድ ምሽት በኢራን መንግሥት በሚተዳደር ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው በሰጡት አስተያየት ነው የማስጠንቀቂያ መልዕክቱን ያስተላለፉት።

    “አሜሪካውያን የመሬት ጥቃት ከፈጸሙ፣ ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት ያለው ማንኛውንም ስፍራ፣ የአሜሪካን ጦር ሠፈሮችና ከአሜሪካ ጋር የተያያዘ ማንኛውንም መርከብ እናጠቃለን” ብለዋል።

    አሜሪካውያን “ሚሳዔሎቻችን የጦር መርከቦቻቸውን እና የጦር ሰፈሮቻቸውን ሲመቱ” ስለ ጦር ኃይላችን ተገንዝበዋል ሲሉም ፋዳቪ ተናግረዋል።

    ኢራን የምታመርተው የጦር መሣሪያ መጠን ከምትጠቀምበት ፍጥነት እንደሚበልጥ አንስተው፣ የአገሪቱ አሁናዊ የጦር አቅም ከቀደሙት ሁለት ጦርነቶች ወቅት ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ ማደጉን ገልፀዋል።

    ስለ ሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ ሲናገሩ ደግሞ፣ ኢራንና ኦማን ይህ ስትራቴጂያዊ የውኃ መተላለፊያ የሚተዳደርበትን ሕግች በጋራ አዘጋጅተው እየተገበሩ እንደሆነም አስረድተዋል።

    በተጨማሪም ዋሽንግተን መርከቦቿን ወደ ቀጣናው ካሰማራች፣ ለኢራን ጥቃት ተጋላጭ እንደሚሆኑ አስጠንቅቀዋል።

    አክለውም “አሜሪካውያን ውጥረትን ሊፈጥሩ የሚችሉት አየር ላይ ብቻ ነው፤ ውጥረቱ ከጨመረ ደግሞ ተጎጂዎቹ ራሳቸው አሜሪካውያን ይሆናሉ” ብለዋል።

    ቴህራን “በምንም መልኩ ሙስሊም አገሮችን አላጠቃችም” ያሉት ፋዳቪ፣ ይልቁንም አገራቸው ዒላማ ያደረገችው በግዛታቸው የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሠፈሮችን እንደሆነ በመጥቀስ አብራርተዋል።

    የአብዮታዊ ዘቡ ባለሥልጣን ይህን አስተያየት የሰጡት፣ በቀጣናው የአሜሪካ ወታደራዊ እንቅስቃሴ በጨመረበትና በዋሽንግተን እና በቴህራን መካከል ያለው ውጥረት በተባባሰበት ወቅት ነው።

    አሜሪካ በቅርቡ ተጨማሪ የጦር መርከቦችን እና የባሕር ላይ ኃይል አባላትን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አሰማርታለች። አውሮፕላን ጫኝ መርከብ እና የአየር እና የሚሳዔል መከላከያዎችም በቀጣናው ያሉ ጦር ሠፈሮቿን ለማጠናከር ካሰማራቻቸው ወታደራዊ ግብዓቶች መካከል ናቸው።

  2. በፈረንሳይ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ 500 የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ተዘጉ

    አድማ በታኝ ፖሊሶች
    የምስሉ መግለጫ, ተቃውሞዎችን ለመቆጣጠር አርብ ዕለት አድማ በታኝ ፖሊሶች ተሰማርተው ነበር

    ባለፉት ቀናት በፈረንሳይ የአድማ ብተና ፖሊሶች እና ተቃዋሚ ተማሪዎች መካከል ግጭቶች ከተከሰቱ በኋላ፣ እስከ 500 የሚደርሱ ትምህርት ቤቶች በዛሬው ዕለት [ሰኞ] በሙሉ ወይም በከፊል እንደሚዘጉ የፈረንሳይ የትምህርት ሚኒስትር ገለጹ።

    ኤዱዋር ጄፍሬይ እንዳሉት፣ በ“400 እስከ 500” የሚደርሱ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ “የደኅንነት ሁኔታዎች ስላልተሟሉ” ትምህርት በሙሉ ወይም በከፊል ይቋረጣል። እንዲሁም ከተቃውሞዎቹ መጀመር በኋላ 24 ትምህርት ቤቶች “ተቃጥለዋል ወይም ጉዳት ደርሶባቸዋል” ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

    በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች በትምህርት ጥራት ላይ ተቃውሞ ያደረጉ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት በፓሪስ የጀመረው እንቅስቃሴ ወደ ሞንፔሊየ፣ ናንትስ እና ማርሴይን ጨምሮ ወደ ሌሎች ከተሞችም ተስፋፍቷል።

    የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እና ሌሎች ተቃዋሚዎች የመምህራን እጥረት፣ የተጨናነቁ ክፍሎች እና ያረጁ እና የተበላሹ የትምህርት ቤት ሕንፃዎችን ሁኔታ በመቃወም ወደ አደባባይ ወጥተዋል።

    የፈረንሳይ የፍትሕ ሚኒስትር ጄራልድ ዳርማኒን አርብ ዕለት እንደተናገሩት፣ ከፈረንሳይ 3,700 ትምህርት ቤቶች ውስጥ 735 የሚሆኑት “በአንድ ወይም በሌላ መልኩ” ኃይል በተቀላቀለባቸው ተቃውሞዎች ተፅእኖ ደርሶባቸዋል።

    የትምህርት ሚኒስትሩ ዛሬ ሰኞ ችግር የሚገጥማቸው ትምህርት ቤቶች ቁጥር ካለፈው ሳምንት አሃዝ ጋር ተመሳሳይ ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀው፣ ቢሆንም “ትምህርት በከፊል እና በደረጃ በደረጃ” እንደሚጀመር ቃል ገብተዋል።

    ጨምረውም ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ 78 የትምህርት ዘርፍ ሠራተኞች መቁሰላቸውን ገልጸው፣ ይህንንም “ከዚህ በፊት አይተነው የማናውቀው ነገር ነው” ሲሉ ገልጸውታል።

    የፈረንሳይ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሎራን ኑኔዝ እንዳሉት፣ ዓርብ ዕለት ብቻ 1,747 ሰዎች ታስረዋል።

    ነገር ግን የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ እንደዘገበው፣ እንቅስቃሴው ከተጀመረ ወዲህ በአጠቃላይ ከ5,000 በላይ ሰዎች ታስረዋል፤ ከእነዚህም ውስጥ 85 በመቶ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች እና ወጣቶች ናቸው።

    እሁድ እለት የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሴባስቲያን ሌኮርኑ መንግሥታቸው “የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችና የትምህርት ዘርፉ ሠራተኞች የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት” ተጨማሪ እርምጃዎች እየወሰደ መሆኑን ተናግረዋል።

  3. የየመን መንግሥት የሁቲ ታጣቂዎች ላይ ሁሉን አቀፍ ጦርነት ማወጁን አስታወቀ

    የየመኑ ፕሬዝዳንት ራሻድ አል-አሊሚ
    የምስሉ መግለጫ, የየመኑ ፕሬዝዳንት ራሻድ አል-አሊሚ እሁድ ዕለት በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው ንግግር ሲያደርጉ

    ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው የየመን መንግሥት መሪ ሁቲዎች የያዟቸውን ግዛቶች ለማስለቀቅ ሁሉን አቀፍ ጦርነት ማወጃቸውን አስታወቁ።

    የየመን መንግሥት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በሳዑዲ በሚመራው ጥምረት እና በሁቲዎች መካከል የተኩስ ልውውጥ ከተደረገ በኋላ ነው።

    በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች በሳዑዲ የሚመራው ጥምረት በ12 ሰዓት ውስጥ ለፈጸመው 50 የአየር ድብደባዎች ምላሽ ለመስጠት በሚል የአሀገሪቱ ብሔራዊ ነዳጅ ኩባንያ፣ አራምኮን አጥቅተዋል።

    ሳዑዲ አረቢያ ስለጥቃቱ እስካሁን ድረስ ምላሽ አልሰጠችም።

    ሁቲዎች ባለፈው ወር ወሳኙን የባብ አል-ማንዳብ የባህር መስመርን ጨምሮ የአገሪቱን የባህር ዳርቻዎች በቁጥጥራቸው ስር ያደረጉበትን ጥቃት ተከትሎ፣ የየመን መንግሥት ጠንካራ መግለጫ ያወጣል ተብሎ ይጠበቅ ነበር።

    የየመኑ ፕሬዝዳንት ራሻድ አል-አሊሚ እሁድ ዕለት በቴሌቪዥን ባደረጉት ንግግር "ዛሬ፣ የሪፐብሊኩን ቀሪ ግዛት መልሶ ለመቆጣጠር እንዲሁም የመንግሥትን እና የተቋማቱን ሥልጣን በመላው አገሪቱ ለማስፋት የሚያስችሉ ወታደራዊ ዘመቻዎች መጀመራቸውን አበስራለሁ" ብለዋል።

    የየመን ዋና ከተማ የሆነችው ሰነዓ በሁቲዎች ቁጥጥር ሥር ከገባች ከ10 ዓመት በላይ አልፏታል።

    ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የመንግሥት ኃይሎች የታጣቂ ቡድኑን አቅም ለማዳከም በሚል ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሲፈጽሙ ቆይተዋል።

    በሁቲዎች ላይ የሚፈጸመው ድብደባ በመላው አገሪቱ የተስፋፋ ሲሆን ይህም የቡድኑ ዋና መቀመጫ የሆነችው እና በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል የምትገኘው ሳዳን ክልልን ይጨምራል።

    ነገር ግን በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች በርካታ ስፍራዎችን እየተቆጣጠሩ ስለመምጣታው ምንጮች ተናግረዋል።

    ሳዑዲ አረቢያ በተደጋጋሚ በሁቲ አማፂያን ጥቃትን ያስተናገደች ሲሆን ይህም የአገሪቱ የገቢ ምንጭ የሆነው የነዳጅ ሃብቷ ላይ ያተኮረ ነው።

    እሁድ ዕለት የሁቲ አማፂያን ቃል አቀባይ ያህያ ሳሬ ቡድኑ በሳዑዲ አረቢያ ሪያድ በሚገኘው እና የአራምኮ ነዳጅ ኩባንያ ንብረት በሆነ ማጠራቀሚያ ላይ የባሌስቲክ ሚሳዔል እና የድሮን ጥቃት መፈጸማቸውን ተናግረዋል።

    "ሁለቱም ኦፕሬሽኖች ግባቸውን በተሳካ ሁኔታ አሳክተዋል" ያሉት ቃል አቀባዩ "ጥቃቶቹ ትክክለኛ ዒላማቸውን የመቱ ሲሆን፣ በተመቱት ቦታዎች ላይም ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ አስከትለዋል" ሲሉ የደረሰውን ጉዳት አብራርተዋል።

    ቡድኑ የሳዑዲን የነዳጅ ማዕከላት መምታቱን ሲገልጽ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ሳዑዲ አረቢያ በእሁዱ ጥቃት ላይ እስካሁን ምንም ዓይነት አስተያየት አልሰጠችም።

    ሆኖም ከዚህ ቀደም አንዳንድ ተመሳሳይ መግለጫዎችን "አሳሳች" በማለት ውድቅ ማድረጓ እንዲሁም ሁቲዎችን "ምናባዊ ድሎችን በማሳደድ" ላይ ናቸው በማለት መተቸቷ ይታወሳል።

    የመን በዓለም ላይ ካሉት እጅግ ድሃ አገራት አንዷ ስትሆን፣ አሁንም ድረስ በከባድ ሰብአዊ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች።