ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለአራት አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ ምድር ስለመኖሩ ቁርጡ ያልታወቀው አውራሪስ
አውራሪስ "ግርማ ሞገስ የተላበሰ፣ በባህሪው በጣም ኃይለኛ እና ቁጡ፣ በግዝፈታቸው ከሚታወቁ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት አንዱ ነበር" ይላሉ፣ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና ልማት ባለሙያው ዶ/ር ዘላለም ተፈራ፡፡
ቀደም ባሉት ዓመታት የኢትዮጵያ መለያ እና ውበት ሆነው ከኖሩት እንስሳት መካከል አንዱ እንደነበረም ያወሳሉ፡፡
በዱር እንስሳት ጥበቃ እና ምርምር ለ37 ዓመታት ያገለገሉት እና ከ1982 እስከ 1985 ዓ.ም የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ኃላፊ ሆነው መሥራታቸውን የሚናገሩት ዶ/ር ዘላለም፣ በአንድ ወቅት አውራሪስ የዚያ ፓርክ ሀብት እንደነበረ ይናገራሉ፡፡
በፓርኩ የመመሥረቻ ሰነድ ላይ፣ "በዚያ ፓርክ ውስጥ ጥበቃ ይደረግላቸዋል" ተብለው ከተዘረዘሩ የዱር አጥቢ እንስሳት ዝርዝር ውስጥ አውራሪስ መካተቱን እንደሚያውቁም ጠቅሰዋል፡፡
በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙ፣ ከደቡብ ምሥራቅ እስከ ደቡብ ምዕራብ ያሉ፣ በልምላሜያቸው የሚያስደንቁ፣ በተፈጥሮ ሀብታቸው የሚታወቁ፣ ለዘመናት በደኖች ተሸፍነው የኖሩ፣ ከቦረና ጫፍ እስከ ጋምቤላ ጥግ ድረስ የሚታዩት አካባቢዎች አውራሪስን ጨምሮ የበርካታ የዱር እንስሳት መጠለያዎች እንደነበሩም ባለሙያው ተናረዋል፡፡
ሆኖም፣ ላለፉት አራት አስርት ዓመታት አውረሪስ በኢትዮጵያ ምድር እንዳልታየ ነው እየተነገረ ያለው፡፡ በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ፋኑኤል ከበደ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከዛሬ 44 ዓመታት በፊት፣ አውራሪስ ለመጨረሻ ጊዜ በኦሞ ብሔራዊ ፓርክ፣ "ኢልባ" በሚባል ሜዳ ላይ ነው የታየው።
"የፓርኩ 10ኛ ኃላፊ የነበሩት አቶ አውግቸው ተሾመ በዚያ ቦታ ላይ አውራሪስ መታየቱን ሪፖርት አድርገዋል" ይላሉ ተመራማሪው፡፡ ከዚያ በኋላ ላለፉት አርባ ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ያንን እንስሳ አይቻለሁ የሚል ሰው አልተገኘም፣ ምልክትም የለም።"
የመጨረሻውን የዳሰሳ ጥናት ያደረገው ዚምባብዌያዊ ባለሙያ መሆኑን የገለፁት ዶ/ር ፋኑኤል ከበደ፣ እሱም አውራሪስ በቅርቡ እንዳልታየና ምንም ዓይነት ምልክት እንዳልተገኘ መናገሩን አውስተዋል፡፡ አውራሪስ ይገኝባቸዋል በተባሉ አካባቢዎች ሁሉ ከሁለት እስከ ሦስት ጊዜ ድረስ የዳሰሳ ጥናት ተደርጎ፣ የተገኘ ነገር እንደሌለ አመክተዋል።
ዶ/ር ዘላለም ተፈራም የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ኃላፊ እያሉ ዶ/ር ሒልማን ከሚባል የዱር እንስሳት ጥበቃ አማካሪ ጋራ ሁለት ጊዜ በፓርኩ ውስጥ በአውሮፕላን ፍለጋ አድርገው እንዲሁም ከሌላ ባለሙያ ጋር ነዋሪዎች አነጋግረው ስለ እንስሳው በአካባቢው መኖር ምንም ዓይነት ፍንጭ እንዳላገኙ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ፎቶው እንኳን ያልተገኘው አውራሪስ
ባለፉት አስርት ዓመታት የአውራሪስ ዱካን በኢትዮጵያ ውስጥ ማግኘት ባይቻልም፣ እንስሳው እንደነበረ የሚያሳዩ ምልክቶች ግን በየቦታው በቅርስነት ይታያሉ፣ በፅሑፍ ይነበባሉ ፣ በመዝገብ ላይም ሰፍረው ይገኛሉ፡፡
"በዐይናችን አይተናል፣ እንስሳውን አድነናል፣ ቅሪቱንም ይዘናል" የሚሉ ሰዎችም በየአካባቢው አልጠፉም፡፡ የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ የቀድሞ ኃላፊው ዶ/ር ዘላለም ተፈራ፣ በፓርኩ ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች በነዋሪዎች ቤት፣ "ከአውራሪስ ቀንድ የተሰራ ዋንጫ እና ሌሎችም ቅሪቶችን ማየት የተለመደ ነው" ብለዋል፡፡
ቀደም ብለው የነበሩ የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ የጥበቃ ሠራተኞች እና ኃላፊዎችም እንደዚሁ፣ በዘመናቸው እንስሳውን የማየት ዕድል ገጥሟቸው እንደነበር ይገልፃሉ፡፡ "በ1970ዎቹ የፓርኩ ኃላፊ የነበሩ አቶ ለይኩን የሚባሉ ባለሙያ፣ በፓርኩ ደቡባዊ ምዕራብ ክፍል አውራሪስ ይታይ ነበር" ብለው መናገራቸውን ዶ/ር ዘላለም አውስተዋል፡፡
ከዚያም አልፎ በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉ የውጭ ዜጎች ምስክርነታቸውን ሲሰጡ ይሰማል፣ አውራሪስ ስለማየታቸውም ፅፈዋል፡፡ "አንድ ስዌይን የተባለ የውጭ ሀገር ተጓዥ፣ በ1893 ገደማ፣ ወደ ሐረር በኩል አሁን የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ባለበት አካባቢ አውራሪስ ማደኑን በፅሑፍ ማስረጃ አስቀምጧል" በማለት ዶ/ር ፋኑኤል ከበደ ተናግረዋል፡፡
አውራሪስ በኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ብቻ ሳይሆን በሶማሌ ክልል ገራይሌ ብሔራዊ ፓርክ ፣ በቦረና፣ በኦጋዴን፣ በከፋ፣ በጋሞ ጎፋ፣ በጋምቤላ እና በሲዳማ አካባቢዎች ይገኝ እንደነበር ባለሙያዎቹ ገልፀዋል፡፡
አሁንም አውራሪስ ሊኖርባቸው ይችላል ተብለው የሚጠረጠሩት፣ ፍለጋም ይካሄድባቸዋል ተብለው የሚጠበቁት አካባቢዎች የኦሞ ሸለቆ፣ በኬንያ ጠረፍ የሚገኘው ቦረና እና ገራይሌ ብሔራዊ ፓርክ አካባቢዎች ናቸው፡፡
ቢቢሲ በዚህ ዘገባው እንስሳው በኦሞ ብሔራዊ ፓርክ የተመዘገበ ስለመሆኑ የሚያመለክቱ የፅሑፍ ማስረጃ ቢጠይቅም ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ማግኘት አልተቻለም፡፡ በተቋሙ ማኅደር ውስጥ አውራሪስ በኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ተመዝግቦ የነበረ እንስሳ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ አልተገኘም ሆነ የእንስሳው ቅረተ-አካልም የለውም፡፡
ከዚህም ባለፈ "በኢትዮጵያ የተነሳ የአውራሪስ ፎቶ አለኝ ወይም አይቻለሁ" የሚል ሰው አልተገኘም፡፡ ቢቢሲ ለዚህ ዘገባው ከተለያዩ አካላት የአውራሪስ ፎቶ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡
በዚህ ዓመት ከመጋቢት ወር ጀምሮ እስከ ሐምሌ ድረስ 60ኛ ዓመቱን ያከበረው የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ባለሥልጣን፣ አውራሪስን በኢትዮጵያ ለመጥፋት የተቃረቡ (Critically endangered) ተብለው ከተለዩ የዱር እንስሳት ጎራ መድቦታል፡፡
እንደ ባለሙያዎቹ ገለፃ፣ በኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ላይ የተጋረጠው አደጋ በአውራሪስ ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች በአገሪቱ ለመጥፋት የተቃረቡ የዱር እንስሳት በርካታ መሆናቸው ይነገራል፡፡ ከእነዚህም መካከል፣ የአፍሪካ የዱር ውሻ እና የአፍሪካ የሜዳ አህያ ይገኙባቸዋል፡፡
የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ አስራ አራት የዱር እንስሳትን የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸው በማለት መድቧቸዋል፡፡ በዚህ ምድብ ውስጥ ከተዘረዘሩት መካከል የኢትዮጵያ ተኩላ፣ አጋዘን፣ ግሬቪስ የሜዳ አህያ፣ ኒያላ እና ዋሊያ ተጠቅሰዋል፡፡
እንደ አንበሳ፣ የኑቢያ ቀጭኔ፣ ሽልም ጅብ፣ ጉማሬ፣ አቦ ሸማኔ እና ነብር የሚገኙባቸው ሀያ አንድ የዱር እንስሳትም ለችግር የተጋለጡ ተብለው ተለይተዋል፡፡ በጥቅሉ በመላ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ አርባ አንድ የዱር እንስሳት በተለያየ የስጋት ደረጃ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠዋል ይላል የባለሥልጣኑ ሰነድ፡፡
ዶ/ር ፋኑኤል ከበደ፣ ችግሩ በዘመናት ሒደት የተፈጠረ እንደሆነ እና ባለፉት ስልሳ ዓመታት በተለያዩ አካበቢዎች የነበሩ የዱር እንስሳት እየጠፉ በመሆናቸው አንዳንድ ቦታዎች ከእንስሳቱ ጋር ተያይዞ ያገኟቸውን ስያሜዎችን ብቻ ይዘ ውቀርተዋል።
"ለምሳሌ ሐረር ውስጥ አሰበ ተፈሪ አካባቢ አርባ ረከቲ፤ አርባ ጉጉ፤ ጋራ ቆርኪ፤ ጋራ ሌንጫ የሚባሉ ቦታዎች አሉ፡፡ እነዚህ ቦታዎች በዝሆን፣ በአንበሳ፣ በአጋዘን የተሰየሙ ናቸው፡፡ ዛሬ እንስሳቱ የሉም፡፡
". . . በአዋሽ ፓርክ ሰጎን፣ ቀጭኔ፣ ጎሽ እና ዝሆን እንደነበሩ በፅሑፍ ሰፍሯል፡፡ ነገር ግን ዛሬ እነዚህ እንስሳት የሉም፡፡ ባለፉት ስልሳ ዓመታት በፓርኮች ተመዝግበው የነበሩ፣ አሁን ግን የማይታዩ እና የጠፉ እንስሳት እንዳሉ ግልፅ ነው" ይላሉ ዶ/ር ፋኑኤል፡፡
በኢትዮጵያ የነበረው የጥቁር አውራሪስ ዝርያ በዓለም ቁጥሩ እየተመናመነ ለመጥፋት መቃረቡን፣ ዓለም አቀፉ የአውራሪስ ፋውንዴሽን እንዲሁም ዓለም አቀፍ የተፈጥሮ ጥበቃ ማኅበር ያጋሯቸው መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
ነገር ግን ባለፉት ዓመታት በአፍሪካ ያለው የእንስሳቱ ቁጥር መጠነኛ መሻሻል እያሳየ እንደሆነና ቁጥሩም ወደ 6 ሺህ 788 መድረሱን ያመለክታሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ እንስሳው በኬንያ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በዚምባብዌ፣ በታንዛኒያ እና በናሚቢያ ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያ አውራሪስ እንዴት ለመጥፋት ተቃረበ?
አውራሪስ በአደን ብዛት እየተገደለ አልቆ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ ቅሪተ-አካሉ ከመካከለኛው ምሥራቅ እስከ ሩቅ ምሥራቅ እና እስያ ድረስ ለመድኃኒትነት በከፍተኛ ደረጃ የሚፈለግ መሆኑን ዶ/ር ዘላለም ተፈራ ይናገራሉ፡፡
በተለይም በቻይና እና ሕንድ የአውራሪስ ቅሪተ-አካል ለመድኃኒትነት፣ በተለይም "ለወሲብ ፍላጎት ማነቃቂያ ይጠቅማል" እየተባለ ስለሚታመን፣ የአፍሪካን የአውራሪስ ሀብት ችግር ላይ የጣለ ጉዳይ ሆኗል፡፡ እናም፣ "አሁን በአፍሪካ ያሉት አውራሪሶች በወታደር የሚጠበቁ ናቸው" ይላሉ፡፡
በመካከለኛው ምሥራቅ፣ ለምሳሌም በየመን "እጀታው ከአውራሪስ ቀንድ የተሠራ ሰይፍ ወይም ጎራዴ መያዝ በእጅጉ ክብር የሚያስገኝ ነገር ነው" የሚሉት ባለሙያው፣ የመን ለኢትዮጵያ ቅርበት ስላላት አውራሪስ እየታደነ ለዚህ ዓላማ ይውላል ባይ ናቸው፡፡
በቀደመው ዘመን የዝሆን ጥርስ፣ የአውራሪስ ቀንድ፣ የነብር እና የአንበሳ ቆዳን የመሳሰሉ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ውጤቶች በስፋት ለውጭ ንግድ ይውሉ እንደነበር የሚያስታውሱት ዶ/ር ዘላለም፤ ለምሳሌ በአመት እስከ 45 ሺህ ኪሎ ግራም የዝሆን ጥርስ ወደ ውጭ ይላክ እንደነበረ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ታሪክ ሰነዶች አረጋግጠዋል ይላሉ።
ሌላኛው ምክንያት በኢትዮጵያ ትላልቅ የዱር እንስሳትን ማደን በማኅበረሰቡ ዘንድ የጀግንነት መገለጫ ተደርጎ መታየቱ ነው፡፡ እንደ ባለሙያው አገላለፅ፣ ይህ የቆየ ባህል ለእንስሳቱ ቁጥር መመናመን እና መጥፋት ተጨማሪ መንስኤ ሆኗል፡፡
የደን ጭፍጨፋን ተከትሎ የዱር እንስሳት መጠለያ መመናመንም ለችግሩ መባባስ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ በተለይም የመንግሥታት ለውጥን ተከትሎ በሚኖሩ የሽግግር ወቅቶች በፓርኮች ላይ ከፍተኛ የደን ጭፍጨፋ እና የዱር እንስሳት አደን እንደሚኖር ዶ/ር ዘላለም ተናግረዋል፡፡
"ባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ለምሳሌ ከደርግ ወደ ኢህአዴግ ዘመን በነበረው ሽግግር ወቅት፣ በጣም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ኒያላ ተገድሏል፡፡ ኒያላ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ ሲሆን፣ በወቅቱ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ ግድያው የቆመው ሕብረተሰቡ ባደረገው ርብርብ ነው፡፡ በስንቅሌ የቆርኪዎች መጠለያም እንደዚሁ፣ በደኑ እና በእንስሳቱ ላይ ከፍተኛ ችግር ደርሷል።"
የጦር መሳሪያ ይዞታ መስፋፋት እንዲሁም ሰፋፊ የልማት ፕሮጀክቶች መምጣት፣ የሰዎች ሰፈራ መበራከት፣ የእርሻ መሬት መስፋፋት እንደዚሁም የተፈጥሮ ሀብት መራቆት ለዱር እንስሳቱ ቁጥር ማሽቆልቆል ከፍተኛ ሚና ነበራቸው፡፡
የዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ መሥሪያ ቤት ተቋማዊ መረጋጋት አለመኖር፣ በሰው ኃይል እና የፋይናንስ ችግር እንዲሁም እንስሳቱን ለመጠበቅ የሚያስችሉት አስፈላጊ ሁኔታዎች አለማግኘቱ ሥራውን ለመወጣት ትልቅ ተግዳሮት መሆናቸውን ዶ/ር ዘላለም ይናገራሉ፡፡
የዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ተመራማሪው ዶ/ር ፋኑኤል በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች የበርካታ የዱር እንስሳት ቁጥር ማሽቆልቆሉን እና አንዳንዶቹም ለመጥፋት መቃረባቸውን በመጥቀስ፣ የጠፉትን እንስሳት "ጠፍተዋል" ብሎ ለማወጅ ግን የራሱ የሆነ ሳይንሳዊ አካሔድ እንዳለው ይናገራሉ፡፡
አሁንም አውራሪስ ጠፍቷል ተብሎ ድምዳሜ ላይ አልተደረሰም፡፡ ከዚያ በፊት የተጠናከረ ጥናት በማካሔድ ፍለጋው ይቀጥላል ባይ ናቸው፡፡
"ሳይንሱ የሚለው አንድ እንስሳ ጠፍቷል ተብሎ ለማወጅ ብዙ መሟላት ያለባቸው መስፈርቶች አሉ፡፡ እንስሳው እስካሁን አልታየም ማለት፣ በአገሪቱ የለም ማለት አይደለም" የሚሉት ዶ/ር ፋኑኤል፣ በሙያው በተካኑ ባለሙያዎች ልዩ ጥናት ተደርጎ ነው መኖሩ እና መጥፋቱ የሚረጋገጠው ብለዋል፡፡
ይህንንም ተከትሎ አውራሪስ መጥፋቱ ከተረጋገጠ፣ ኢትዮጵያ አንድ የዱር እንስሳ ዝርያ አጥታለች ተብሎ በሰፊው ይነገራል፡፡
ያኔ "አውራሪስ" የሚለው ስያሜ "ነበረ" ለሚባለው እንስሳ መታሰቢያነት ሆኖ የሚቀር ይሆናል፡፡