ለዓለም ዋንጫ አሜሪካ እንዳይገባ የተከለከለው ሶማሊያዊው ዳኛ የአውሮፓ ጨዋታን እንዲመራ ተመረጠ
አሜሪካ እንዳይገባ ተከልክሎ በዓለም ዋንጫ ላይ የመዳኘት ዕድልን የተነፈገው ሶማሊያዊ የእግር ኳስ ዳኛ ኦማር አርታን የአውሮፓ ሱፐር ካፕ ጨዋታን እንዲዳኝ ተመረጠ።
ሶማሊያዊው ዳኛ በዓለም ዋንጫ ላይ እንዳያጫውት መደረጉ ከበርካቶች ዘንድ ተቃመሞን ያስከተለ ሲሆን፣ የአውሮፓ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ግን ሌላ ጨዋታ እንዲዳኝ መርጦታል።
የ34 ዓመቱ አርታን በነሐሴ ወር በፈረንሳዩ ፓሪስ ሳን ዠርሜን እና በእንግሊዙ አስቶንቪላ መካከል ኦስትሪያ ሳልዝበርግ ውስጥ የሚካሄደውን ግጥሚያ እንዲመራ መመረጡን ፌዴሬሽኑ አረጋግጧል።
ሶማሊያዊው ዳኛ ከአውሮፓውያኑ 2018 ጀምሮ በዳኝነት በፊፋ የተመዘገበ ሲሆን፣ ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ደግሞ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን የዓመቱ ዳኛ ብሎ መርጦታል። በተጨማሪም የዚህ ዓመቱን የዓለም ዋንጫ ከሚዳኙ ዳኞች መካከል አንዱ ነበር።
አሜሪካ ዳኛውን ወደ ግዛቷ እንዳይገባ በመከልከሏ በዓለም ዋንጫ የማጫወት ዕድሉ የተጨናገፈበነት አርታን ወደ አገሩ ሲመለስ ደማቅ አቀባበል በተደረገለት ጊዜ በቀጣዩ የዓለም ዋንጫ በዳኝነት እንደሚሳተፍ ተስፋውን ገልጿል።