ቀጥታ, ኢራን እስራኤል ላይ ጥቃት ከፈጸመች በኋላ ጦሯ የአጸፋ ምላሽ ሰጠ

ኢራን በሚያዝያ ወር ከአሜሪካ ጋር የተኩስ አቁም ከደረሰች ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ እስራኤል ሚሳዔሎችን አስወነጨፈች። የእስራኤል ጦር የቴህራን ጥቃትን ተከትሎ በምዕራብ እና ማዕከላዊ ኢራን በሚገኙ ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ ድብደባ መፈጸሙን አስታውቋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የኢራን ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ሜክሲኮ ገባ

    የኢራን ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን

    በ2026 የዓለም ዋንጫ ላይ የሚሳተፈው የኢራን ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ሜክሲኮ መግባቱ ተገለጸ።

    ቡድኑ ከቪዛ እና በአሜሪካ ከሚገኙ ስታዲየሞችን ከመጠቀም ጋር በተነሳ ውዝግብ ውስጥ ገብቶ ነበር።

    የኢራን ሦስቱም ጨዋታዎች የሚካሄዱት በአሜሪካ ቢሆንም፣ ተጫዋቾቹ እና የድጋፍ ሰጪዎች በጨዋታው ዕለት አሜሪካ ገብተው መውጣት ይጠበቅባቸዋል።

    ኢራን 15 የቡድኑ ልዑካን አባላት እና ባለሥልጣናት ቪዛ መከልከላቸውን አስታውቃለች። እርምጃውንም በስፖርቱ ላይ የሚካሄድ ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ስትል ኮንናዋለች።

    ቡድኑ ለዓለም ዋንጫ ማለፉን ያረጋገጠው የኢራን ጦርነት ከመጀመሩ አንድ ዓመት ቀድም ብሎ ነበር።

    የኢራን ቡድን ቲዋና የደረሰው በአገሬው አቆጣጠር እሁድ ማለዳ ሲሆን የልምምድ ሜዳቸውን ከአሪዞና ወደ ሜክሲኮ ያዞሩት በግንቦት ወር ላይ ነበር።

    የዘንድሮው የዓለም ዋንጫን አሜሪካ ከሜክሲኮ እና ካናዳ ጋር በመሆን በጥምረት ታዘጋጃለች።

  2. ትራምፕ፣ ኔታንያሁ ስምምነቱን ከመቀበል ውጭ አማራጭ የለውም አሉ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Kevin Dietsch via Getty Images

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የሚያደርጉትን ማንኛውም ስምምነት ኔታንያሁ ከመቀበል ውጭ አማራጭ የላቸውም ሲሉ ለፋይናንሻል ታይምስ ተናገሩ።

    ትራምፕ ለፋይናንሻል ታይምስ “አማራጭ የለውም” ሲሉ በስልክ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ወቅት ተናግረዋል። “እኔ ነኝ ውሳኔውን የምሰጠው። እኔ ነኝ ሁሉንም ውሳኔ የምሰጠው። እርሱ [ኔታንያሁ] አይደለም ውሳኔ ሰጪው” ብለዋል።

    ትራምፕ ከአክሲዮስ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ወቅት ኔታንያሁ የሰላም ስምምነቱ እንዳይከሽፍ ለማድረግ ለኢራን ጥቃት የአጸፋ ምላሽ እንዳይሰጡ እንደሚነግሯቸው ገልጸው ነበር።

    ትራምፕ ከፋይናንሻል ታይምስ ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ ላይ ደግሞ የተፈጸመው ጥቃት “በስምምነቱ ላይ ምንም ተጽዕኖ አይኖረውም” ብለዋል።

    አክለውም “እንዴት ሆኖ እንደሚጠናቀቅ እናያለን። ላለፉት 3000 ዓመታት 47 ዓመታት ሲሆን የነበረው ነገር ነው፤ ወይም እንደምትቆጥርበት መንገድ ይወሰናል” ብለዋል።

  3. ኢራን እስራኤል ላይ ጥቃት ከፈጸመች በኋላ ጦሯ የአጸፋ ምላሽ ሰጠ

    የኢራን ጦር ወደ ሰሜን እስራኤል ያስወነጨፈው ሚሳዔል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ኢራን በሚያዚያ ወር ከአሜሪካ ጋር የተኩስ አቁም ከደረሰች ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ እስራኤል ሚሳዔሎችን አስወነጨፈች። የእስራኤል ጦር የቴህራን ጥቃትን ተከትሎ በምዕራብ እና ማዕከላዊ ኢራን በሚገኙ ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።

    የኢራን አብዮታዊ ዘብ ሚሳዔሎቹ “ለሳምንት የሚቀጥለው ጥቃት” የመጀመሪያ ነው ሲል አስታውቋል።

    የእስራኤል ጦር በቴሌግራም ገጹ ላይ "ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት የእስራኤል አየር ኃይል የኢራን አሸባሪ አገዛዝ ንብረት የሆኑ በምዕራብ እና ማዕከላዊ ኢራን የሚገኙ ወታደራዊ ዒላማዎችን ደብድቧል" ሲል ጽፏል።

    እስራኤል በበኩሏ በሰሜናዊ እስራኤል ሚሳዔሎችን ማክሸፏን ገለጻ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ ግን ያለችው የለም።

    እሁድ ዕለት እስራአል በደቡባዊ ቤይሩት የሄዝቦላህ ዒላማዎች ላይ ድብደባ መፈጸሟን አስታውቃለች።

    የጦሩ ቃል አቀባይ ኢራን “ትልቅ ስህተት ሰርታለቸ” ሲሉ ተናግረዋል። ፎክስ ኒውስ በበኩሉ ትራምፕ ኢራንን “ይበቃል ወደ ድርድር ጠረጴዛው ተመለሽ” ሲሉ መናገራቸውን ዘግቧል።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለአክሲዮስ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ለኢራን ሚሳዔሎች የአጸፋ ምላሽ እንዳይሰጡ እንደሚናግሯቸው ገልጸዋል።

    “አሁን ለቢቢ እደውልለታለሁ እና የአጸፋ ምላሸ እንዳሰጥ እነግረዋለሁ” ብለዋል። “ሁለቱም የራሳቸው ደስታን አግኝተዋል። እስራኤል አጥቅታለች እናም ኢራን አጥቅታለች። ተጨማሪ አንፈልግም።”

    “ከኢራን ጋር ወደ መጨረሻው ስምምነት ተቃርበናል። ጥሩ ስምምነት ነው የሚሆነው። አሁን እየሆነው ባለው የተነሳ ይህንን ማጣት አልፈልግም” ማለታቸውን አክሲዮስ ዘግቧል።

    ትራምፕ አክለውም እስራኤል ዳግም ጥቃት ከፈጸመች ግጭቱ “ለ47 ዓመታት ወይም እንደ 3000 ዓመታቱ” ይቀጥላል ብለዋል። አክሲዮስ ትራምፕ ለኔታንያሁ መደወላቸውን ጨምሮ ዘግቧል።

    የእስራኤል ጦር በበኩሉ በቴሌግራም ገጹ ላይ ሌተናል ጄነራል ኢያል ዛሚርን በመጥቀስ “ጠላትን በቁርጠኝነት ትዕዛዝ እንደተሰጠን መደብደብ አንጀምራለን” ብሏል።