ከትራምፕ ንግግር በኋላ የነዳጅ ዋጋ ሲቀንስ፣ ኢራን ስምምነቱ ገና አልተቋጨም አለች
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከኢራን ጋር የሚደረገውን ጦርነት የሚያስቆም ስምምነት ላይ መደረሱን ሲያስታውቁ ኢራን ግን ገና መቋጫ ላይ አለመደረሱን ገለጸች።
በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የሚካሄደው ጦርነት የበለጠ ይባባሳል ተብሎ በተሰጋበት ጊዜ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን ላይ እንደሚፈጸም የተናገሩትን ጥቃት ሰርዘው የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ ለአገራቸው ቴሌቪዥን ከስምምነት ተደርሷል መባሉን “ግምታዊ” በማለት “ከመደምደሚያው ላይ እንዳልተደረሰ” ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከዚህ ቀደምም ሁለቱ አገራት ጦርነቱን ወደሚያበቃ ስምምነት እየተቃረቡ መሆናቸውን በተደጋጋሚ ተናግረው እንደነበር ይታወሳል።
ይህ የትራምፕ ንግግር ከተሰማ በኋላ ውጥረቱ በተባባሰባቸው ባለፉት ቀናት ጭማሪ እየሳየ የነበረው የዓለም ገበያ ዋጋ ከአራት በመቶ በላይ ቅናሽ በመሳየት በበርሜል ወደ 89 ዶላር ወርዷል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በጽሕፈት ቤታቸው ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "ኢራን ፈጽሞ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዳይኖራት የሚያደርግ ስምምነት ላይ ደርሰናል፤ ይህንን ለማሳካት ስንል ነበር በዚህ ሁሉ ውስጥ ያለፍነው። በጣም ትልቅ ስምምነት ነው” ብለዋል።
ጨምረውም የስምምነቱ ሰነድ ተዘጋጅቶ ሲያበቃ “በጣም በፍጥነት” ሁለቱ አገራት “ምናልባትም ፊርማው አውሮፓ ውስጥ” ይካሄዳል ብለዋል።
በጦርነቱ ምክንያት የተዘጋው ወሳኙ የባሕር መተላለፊያ መስመር ሆርሙዝም “ስምምነቱ ሲፈረም ወዲያውኑ ይከፈታል” በማለት በጉዳዩ ላይ ከእስራኤል እና ከመካከለኛው ምሥራቅ አጋር አገራት ጋር መነጋገራቸውን እነሱም “ደስተኛ” መሆናቸውን ተናግረዋል።
ለውጤቱ ለትራምፕ ያላቸውን አድናቆት የገለጹት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ስምምነቱ “[የኢራንን] የዳበረ ዩራኒየም ማስወገድ፣ የዩራኒየም ማበልጸጊያ ተቋማትን ማውደም፣ የሚሳዔል ምርቷን መገደብ እና በቀጣናው ላሉ ሽብርተኛ ቡድኖች ድጋፏን ማቆም” የሚሉ እንደሚገኙበት ገልጸዋል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እንዳሉት ደግሞ የሚፈረመው የመግባቢያ ሰነድ “ቢጠናቀቅም” አሜሪካ “ከልክ ያለፉ እና አዳዲስ ጥያቄዎችን እያቀረበች ነው” በማለት ኢራን ካስቀመጠችው “ቀይ መስመር ፈቀቅ እንደማትል” አስታውቀዋል።