ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥ አሁንም በቁጥጥሯ ስር መሆኑን አስታወቀች
ከአሜሪካ ጋር የሚደረገው ጦርነት ጋብ ማለቱን ተከትሎ ኢራን ወሳኝ የሆርሙዝ ወሽመጥ በቁጥጥሯ ስር መሆኑን እንዲሁም የተቋረጠው የሰላም ንግግር እንዲጀመር አለመጠየቋን አስታወቀች።
አሜሪካ ለ13 ተከታታይ ቀናት በኢራን ላይ ጥቃቶችን በፈጸመችበት ወቅት፤ ቴህራንም በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ውስጥ የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮችን በሚሳዔል እና ድሮን ዒላማ ስታደረግ ቆይታለች።
ትራምፕ ለሁለት ሳምንት ገደማ የቆየውን የአየር ጥቃት ያቆሙት፣ ዘመቻው ኢራን በሆርሙዝ ላይ ያላትን ቁጥጥር ለመስበር የወጠነውን ግብ እንዳላሳካ በአማካሪዎቻቸው ከተገለጸላቸው በኋላ መሆኑ ተዘግቧል።
አሜሪካ ጥቃቱን እስካቆመች ድረስ፣ ኢራን በበኩሏ የምትወስደውን እርምጃ እንደምትገታ አስታውቃለች።
አንድ ባለሥልጣን ለሮይተርስ እንደገለጹት የአሜሪካ ወታደራዊ አዛዦች ዘመቻው ዓላማውን እየሳተ ነው በማለት ፕሬዝዳንቱን መክረዋቸዋል።
ባለሥልጣኑ ጨምረውም የአሜሪካ ጦር ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የሆኑት ጄነራል ዳን ኬይን በቀጣናው ያሉ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮችን ከጥቃት ለመከላከል የሚያስችል የመሳሪያ ክምችታቸው እየተመናነመነ መሆኑን መናገራቸውን አመልክተዋል።
የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የፕሬዝዳንት ትራምፕ ሲቪል እና ወታደራዊ አማካሪዎች በኢራን ላይ የሚፈጸመው ጥቃት እንዲቆም ምክር መስጠታቸውን ዘግበዋል።
በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ማይክ ዋልትዝ በኢራን ላይ የሚፈጸመው ጥቃት የቆመው ለድርድር በር ለመክፈት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን ከአሜሪካ ጋር የሚካሄደው የሰላም ንግግር መልሶ እንዲጀመር ጥያቄ እንዳላቀረበች አሳውቋል። የአሜሪካ ጥቃት አለመሳካቱን እና ወሳኙ የሆርሙዝ ወሽመጥ በቁጥጥሯ ስር መሆኑን ኢራን አስታውቃለች።
አሜሪካ ሁለት ሳምንት ለሚጠጋ ጊዜ በኢራን ላይ ባካሄደችው ጥቃት ምክንያት የነዳጅ ዋጋ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቶ ነበር። ባለፉት ቀናት ጥቃቱ ጋብ ማለቱን ተከትሎ ደግሞ ከፍተኛ ቅናሽ ማሳየቱ ተዘግቧል።