ቀጥታ, አሜሪካ በኢራን ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ማቆሟን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ቅናሽ አሳየ

የአሜሪካ እና የኢራን ግጭት ለሁለት ሳምንት ያህል ከቀጠለ በኋላ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ መቆሙን ተከትሎ ሰኞ ዕለት የዓለም አቀፉ የነዳጅ ዋጋ በ6 በመቶ ቅናሽ አሳየ። አሜሪካ ለተከታታይ ሁለት ሳምንት በኢራን ላይ የፈጸመችውን ድብደባ ካቆመች በኋላ ኢራን የአጸፋ ምላሽ እንደማትሰጥ በመግለጿ ግጭቱን ለማርገብ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ሊገኝ እንዲሁም የሆርሙዝ ወሽመጥ ሊከፈት ይችላል የሚል ተስፋ አጭሯል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ኢራን ከአሜሪካ ጋር ድርድር እያደረገች አለመሆኑን አስታወቀች

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አገራቸው ከአሜሪካ ጋር መልዕክቶችን መለዋወጧን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት መደበኛ የሆነ ድርድር እየተደረገ አለመሆኑን ገለጹ።

    ኢስማኤል ባጋይ ቴህራን አሁን ቅድሚያ የምትሰጠው ሉዓላዊነቷን መከላከል፣ የግዛት አንድነቷን ማስጠበቅ እና ለሕዝቧ መብት መሆኑን ገልጸው ወደ ድርድር ፈጥነው እንደማይገቡ ተናግረዋል።

    ቃል አቀባዩ ዋሺንግተን ዲፕሎማሲን በወታደራዊ እርምጃ ውድቅ ታደርጋለች ሲሉ የኮነኑ ሲሆን አሜሪካ ወደ ድርድር ለመመለስ ያለውን ሁኔታ አበላሽታዋለች ብለዋል።

    ባጋይ ከአውስትራሊያው ኦአርኤፍ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “መልዕክቶችን እየተለዋወጥን ነው፤ ነገር ግን አሁን ቅድሚያ የምንሰጠው ለኢራን ሉዓላዊነት፣ ለግዛት አንድነት እና ለሕዝቧ መብት መከበር ነው” ብለዋል።

    የቃል አቀባዩ አስተያየት ምንም እንኳ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል መደበኛ ድርድር ባይጀመርም ቀጥተኛ ያልሆነ ግንኙነት እየተካሄደ መሆኑን ይጠቁማል።

    ከዚህ ቀደም ቀጣናዊ አደራዳሪዎች ፓኪስታን እና ኳታር በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የመልዕክት ልውውጥ በማቀላጠፍ ረገድ ሚና ነበራቸው።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዩ አስተያየት የተሰማው አሜሪካ ለሁለት ሳምንት ስታካሄድ የነበረውን ጥቃት ማቆሟን ከገለጸች በኋላ ነው።

    የጥቃቶቹ መቆም ዳግም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሊጀመር ይችላል የሚል ተስፋ አጭሯል።

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን የነዳጅ አቅርቦት አስተጓጉሏል።

  2. አሜሪካ በኢራን ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ማቆሟን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ቅናሽ አሳየ

    የአሜሪካ እና የኢራን ግጭት ለሁለት ሳምንት ያህል ከቀጠለ በኋላ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ መቆሙን ተከትሎ ሰኞ ዕለት የዓለም አቀፉ የነዳጅ ዋጋ በ6 በመቶ ቅናሽ አሳየ።

    አሜሪካ ለተከታታይ ሁለት ሳምንት በኢራን ላይ የፈጸመችውን ድብደባ ካቆመች በኋላ ኢራን የአጸፋ ምላሽ እንደማትሰጥ በመግለጿ ግጭቱን ለማርገብ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ሊገኝ እንዲሁም የሆርሙዝ ወሽመጥ ሊከፈት ይችላል የሚል ተስፋ አጭሯል።

    የዓለም ነዳጅ ዋጋ ተመን የሆነው የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በ6.4 በመቶ ወርዶ በበርሜል 90.58 ዶላር እየተሸጠ ነው።

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ጦርነት ከተጀመረ በኋላ የሆርሙዝ ወሽመጥ በመዘጋቱ እና ግጭቱ ወደ ቀይ ባሕርም በመስፋፋቱ የብሬንት ዋጋ ባለፈው ሳምንት በበርሜል 100 ዶላር ደርሶ ነበር።

    በየመን የሚገኙት የሁቲ ታጣቂዎች የሳዑዲ አረቢያ መርከቦች በቀይ ባሕር ላይ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ላይ ባለፈው ሳምንት እገዳ ጥለዋል።

    ይህም የዓለም ከፍተኛ ነዳጅ ላኪ የሆነችው አገር ምርቷን ለውጭው ዓለም ገበያ እንዳታቀርብ ከፍተኛ እንቅፋት ፈጥሯል።

    በተባበሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ማይክ ዋልዝ ለፎክስ ኒውስ እሁድ ዕለት እንደተናገሩት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቴህራን ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት የገቱት ለዲፕሎማሲ ጥረት ዕድል ለመስጠት ነው ብለዋል።

    የኢራኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ ዛሬ ሰኞ በሰጡት መግለጫ የሆርሙዝ ወሽመት ዝግ እንደሆነ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

    የሁቲ ታጣቂዎች በቀይ ባሕር ላይ የሚቀዝፉ የሳዑዲ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸማችን ካስታወቁ በኋላም በባብ ኤል መንደብ በኩል የመርከቦች እንቅስቃሴ ተቀዛቅዟል።

  3. አዲሱ የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዩክሬንን መደገፍ እንደሚቀጥሉ ተናገሩ

    አዲሱ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ በርንሀም ለዩክሬን የሚያደርጉትን “ጽኑ ድጋፍ” ለመቀጠል ቃል ገቡ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ጋር ዛሬ ሰኞ ውይይት ያደርጋሉ።

    ከውይይቱ አስቀድመው እንደተናገሩትም ለዩክሬን የሚደረገውን ድጋፍ እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ከተረከቡ አንድ ሳምንታቸው ሲሆን፤ የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ጎብኚያቸው ዜሌንስኪ ይሆናሉ።

    ውይይቱ የሁለቱን አገራት ግንኙነት “እንደሚያጠናክር” ተገልጿል። መሪዎቹ የባሕር ኃይል ይጎበኛሉ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ “እንግሊዝ ከዩክሬን ጎን ትቆማለች፤ ድጋፋችን አይቋረጥም። ለዩክሬንን ዘላቂ ሰላም እና ፍትሕ ሳናሰፍን ወደኋላ አንልም” ብለዋል።

  4. ኔታንያሁ የኒው ዮርክ ከንቲባን “ጥላቻን በማነሳሳት” ወነጀሉ

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የኒው ዮርክ ከንቲባ በቁጥጥር ስር ሊያውሏቸው ቢዝቱም በመንግሥታቱ ድርጅት ጉባዔ ላይ ለመታደም ማቀዳቸውን ተናገሩ።

    የኒው ዮርክ ከንቲባ የሆኑት ዞህራን ማምዳኒ ባለፈው ሳምንት ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ያወጣውን የእስር ማዘዣ ለማስፈጸም ተናግረው የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ የሕግ ድጋፍ እንደሌላቸው በመግለጽ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ለፎክስ ኒውስ እሁድ ዕለት እንደተናገሩት ማምዳኒ ቀደም ሲሉ በሰጡት አስተያየት “ስጋት እንደማይገባቸው”ተናግረው ከንቲባው “ጥላቻን ያነሳሳሉ” ሲሉ ወንጅለዋቸዋል።

    ኔታንያሁ “እርሱ የሁሉም የኒውዮርክ ነዋሪዎች፣ አይሁዶች፣ ክርስቲያኖች፣ ሙስሊሞች ከንቲባ መሆን አለበት፤ ነገር ግን አንዱን ቡድን በሌላኛው ላይ ለማነሳሳት እየሞከረ ነው” ሲሉተናግረዋል።

    ኔታንያሁ ሐሙስ ዕለት በኒው ዮርክ የተፈፀመውን ሁለት የስለት ጥቃት ጠቅሰዋል፤ በዚህ ጥቃት አንድ ተጠርጣሪ አንድ አይሁዳዊ እና አንድ እስያዊን ወግቷል።

    ፖሊሶች ተጠርጣሪው በስለት ጥቃት ሲያደርስ "አላህ አክበር" እያለ ይጮህ ነበር። ከእያንዳንዱ ተጎጂ ጋር በተያያዘ በጥላቻ ወንጀሎች ክስ ተመስርቶበታል።

    ሁለቱም ሰዎች ከጥቃቶቹ የተረፉ ሲሆን ይህም ከከተማዋ የአይሁድ እና የእስያ አሜሪካውያን መሪዎች ውግዘት አስከትሏል።

    ከዚያ በኋላ ኔታንያሁ በሰጡት ቃለ ምልልስ በኒው ዮርክ የሚኖሩ አይሁዶች "ፈርተዋል" ብለዋል።

  5. የኢራን ሕግ አውጪዎች ዩክሬን በካስፒያን ባሕር ላይ ለፈጸመችው ጥቃት የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጡ ዛቱ

    ዩክሬን በካስፒያን ባሕር ላይ እየቀዘፈ የነበረ የኢራን የንግድ መርከብ ላይ የድሮን ጥቃት ከፈጸመች በኋላ አንድ ከፍተኛ የኢራን ሕግ አውጪ የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጥ አስጠነቀቁ።

    በኢራን ላይ የሚፈጸም ማንኛውም ጥቃት የአጻፋ ምላሽ አለው ያሉት የሕግ አውጪው ይህንን አሜሪካ እና እስራኤል ያውቃሉ ብለዋል።

    የኢራን ፓርላማ ብሔራዊ ደህንነት እና የውጭ ፖሊሲ ኮሚሽን ሰብሳቢ የሆኑት ኢብራሂም አዚዝ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባጋሩት መልዕክት አሜሪካ እና እስራኤል “ማንኛውም በኢራን ላይ የሚፈጸም ጥቃት ምንጊዜም ዋጋ እንደሚያስከፍል ያውቃሉ። ይህ ደግሞ ዛሬም እውነት ነው” ብለዋል።

    አክለውም “ዩክሬን በቅርቡ ኢራን ድርጊቱ ምላሽ ሳያገኝ እንደማትተወው ትማራለች” ብለዋል።

    አዚዝ “አሳንሰው የሚገምቱን ዝርዝር እየጨመረ ነው የመጣው” ብለዋል።

    እሁድ ዕለት የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ ዩክሬን በኢራን የንግድ መርከብ ላይ የፈጸመችው ጥቃት የመንግሥታቱን ድርጅት ቻርተር የጣሰ መሆኑን ተናግረዋል።

    አክለውም በጥቃቱ አንድ ባህረተኛ መገደሉን አሳውቀው “ምላሽ ሳይሰጠው አይቀርም” ብለዋል።

    የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ በኤክስ ገጻቸው ላይ አገራቸው በካስፒያን ባሕር ላይ ረዥም ርቀት ሚሳዔሎችን በማስወንጨፍ “ጠንካራ ውጤቶችን” ማግኘቷን አስታውቀዋል።

    አክለውም ጥቃቱ የተፈጸመው “ኢራን በተሳተፈችበት ወታደራዊ ጭነት በጫነች መርከብ ላይ” መሆኑን ተናግረዋል።

  6. የአሜሪካ አምባሳደር ትራምፕ ጥቃቱን ያስቆሙት ለንግግር ቦታ ለመስጠት ነው አሉ

    ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ላይ የሚፈጸመውን ድብደባ እንዲቆም ያደረጉት ለዲፕሎማሲ ተጨማሪ ጊዜ ለመስጠት መሆኑን በመንግሥታቱ ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር አስታወቁ።

    አምባሳደር ማይክ ዋልዝ እሁድ ዕለት ለፎክስ ኒውስ በሰጡት ቃለ ምልልስ ፕሬዚዳንቱ “ለንግግር የተወሰነ ቦታ ለመስጠት” ጥቃተ እንዲቆም ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

    የኢራን ጦር ቃል አቀባይ እሁድ ዕለት ቴህራን በቀጣናው ላይ የምትፈጽመውን “የአጸፋ” ጥቃቶች ማቆሟን ተናግረዋል።

    በዩናይትድ ስቴትስ እና ኢራን መካከል በሰኔ ወር የተደረሰው የተኩስ አቁም ከፈረሰ በኋላ የአሜሪካ ጦር ለሁለት ተከታታይ ሳምንቶች በየዕለቱ ኢራን ላይ ድብደባ ሲፈጽም ቆይቷል።

    ቴህራንም በምላሹ በጎረቤት አገራት የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሠፈሮች ላይ ሚሳዔሎችን ስታስወነጭፍ ቆይታለች።

    አምባሳደሩ ትራምፕ ጥቃቱ እንዲቆም ያደረጉት ለአጭር ጊዜ ስለመሆኑ kኤንቢሲ ተጠይቀው ሲመልሱ “ለአሁኑ እዚያ ድረስ ሄጄ መመለስ አልፈልግም። ፕሬዚዳንቱ ሁሉንም አማራጮች ጠረጴዛ ላይ አስቀምጠዋል” ብለዋል።

    ኒውዮርክ ታይምስ የአስተዳደሩ ባለሥልጣናት ጥቃቶች እየሰፉ የሚመጡ ከሆነ የአየር መከላከያ ጦር መሣሪያዎች እየሳሱ ይመጣሉ ማለታቸውን መዘገቡን በተመለከተ ዋልዝ ሲጠየቁ አጣጥለውታል።

    “የአሜሪካ ጦር . . . ዘመቻውን በሚፈለገው መልኩ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስፈልጉት ሁሉም ነገሮች አሉት” ብለዋል።

    እስከ እሁድ ምሽት ድረስ ትራምፕ ጥቃቱ ስለመቆሙ በይፋ ያሉት ነገር የለም።

    ነገር ግን ቀደም ሲል በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ የአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖች የኢራንን መርከቦች እና የኻርግ ደሴቶችን ሲደበድቡ የሚያሳይ በሰው ሠራሽ አስተውሎት የተሰራ ምስል አጋርተው ነበር።