ኢራን ከዕውቅናዋ ውጪ በሆርሙዝ በኩል የሚደረጉ ጉዞዎች አደገኛ እንደሚሆኑ አስጠነቀቀች

በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚደረግ የመርከቦች እንቅስቃሴ በሙሉ ከኢራን ጋር በመቀናጀት ካልተደረገ ደኅንነቱ አስተማማኝ እንደማይሆን የኢራን ባለሥልጣን አስታወቁ።
የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካዚም ጋሪባባዲ እንደተናገሩት በሆርሙዝ በኩል የሚደረግ ጉዞ ከኢራን ዕውቅና ውጪ ከሆነ ዋስትና እንደማይኖረው በማመልከት የትኛውም በመተላለፊያው ላይ የሚከፈት የባሕር መስመር ከኢራን ጋር በመቀናጀት ካልሆነ ዕግድ እንደሚጣልበት አስጠንቅቀዋል።
ባለሥልጣኑ ይህንን ማስጠንቀቂያ በኤክስ ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት ኦማን ከተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የባሕር ትራንስፖርት ድርጅት ጋር በመሆን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ጊዜያዊ የመርከቦች የመተላለፊያ መስመር መክፈቷ ከተገለጸ በኋላ ነው።
ቀደም ሲል ኢራን አዲስ ያቋቋመችው የሆርሙዝ ወሽመጥ እንቅስቃሴን የሚቆያጠረው ባለሥልጣን ዕውቅና ባልተሰጠው የባሕሩ ክፍል በኩል የሚተላለፉ መርከቦች ላይ ለሚያጋጥሙ ችግሮች ኃላፊነቱን የመርከቦቹ ካፒቴኖች እና የመርከቦቹ ባለቤቶች የሚወስዱ ይሆናል በማለት አስጠንቅቆ ነበር።
የተባበሩት መንግሥታት መውጫ አጥተው በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ለወራት የቆዩ መርከቦችን ለማሳለፍ በከፈተው መንገድ ጉዞ በጀመረ መርከብ ላይ ሐሙስ ዕለት ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ እንቅስቃሴዎች ተገትተዋል።
ጥቃቱ የተፈጸመው የኢራን አብዮታዊ ዘብ በተባበሩት መንግሥታት የተከፈተው አዲስ የመርከቦች መተላለፊያ መስመር ከኢራን ዕውቅና ውጪ መሆኑን በማመልከት “ተቀባይነት የሌለው እና ሙሉ ለሙሉ አደገኛ” መሆኑን ካሳወቀ በኋላ ነው።
የብሪታኒያ የባሕር ላይ ጉዞ ደኅንነት ተቋም ሐሙስ ዕለት እንዳለው መርከቡ ከኦማን ወደብ ደቡብ ምሥራቅ ላይ “ምንነቱ ባልታወቀ ተወንጫፊ” መመታቱን እና በሰው ላይ ጉዳት አለመድረሱን አስታውቋል።
ኢራን በመርከቡ ላይ ጥቃቱን መፈጸሟን የአሜሪካ ባለሥልጣናት መናገራቸውን የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።




















