ኢራን የባሕረ ሰላጤው አገራት እና አሜሪካ ያወጡትን መግለጫ ተቃወመች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢራን የባሕረ ሰላጤው ትብብር ምክር ቤት አባል አገራት እና አሜሪካ በጋራ ያወጡት መግለጫን “ጣልቃ ገብነት፣ ኃላፊነት የጎደው እና ጠብ ጫሪ” ስትል አወገዘች።
ባህሬን ውስጥ የተካሄደውን ስብሰባ ተከትሎ የወጣውን መግለጫ በመቃወም ኢራን በሰጠችው ምላሽ የአሜሪካ ጦር ሠራዊት በባሕረ ሰላጤው አካባቢ መገኘቱ ለአካባቢው አለመረጋጋት እና ክፍፍል ምክንያት ነው ብሏል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳለው አሜሪካ እና አስራኤል ለፈጸሙት ጥቃት በቀጣናው ያሉትን የአሜሪካ ጦር ሰፈሮችን መጠቀማቸው ዋሽንግተን ለአካባቢው ደኅነንት ግድ እንደሌላት ያሳያል።
ጨምሮም የሆርሙዝ ወሽመጥን የማስተዳደሩ ጉዳይ በኢራን እና በኦማን መካከል በሚኖር ትብብር እንዲሁም ከአሜሪካ ጋር በተደረሰው የመግባቢያ ሰነድ አማካኝነት የሚፈጸም መሆኑን አመልክቷል።
ሐሙስ ዕለት በተካሄደው የባሕረ ሰላጤው አገራት ትበብር ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የተገኙ ሲሆን፣ በቀጣናው ባለው ውጥረት ላይ ተወያይቷል።
ከስብሰባው በኋላ በወጣው የጋራ መገግለጫ ላይ አባል አገራቱ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረሰውን ስምምነት የተቀበሉት ሲሆን፣ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የበላይነት ለመያዝ እንዲሁም መርከቦችን ለማስከፈል ያሚታሰብ የትኛውንም ፖሊሲ ተቃውመዋል።
ባህሬን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኳታር፣ ኦማን፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ኩዌት የባሕረ ሰላጤው አገራት ትብብር ምክር ቤት አባላት ናቸው።



















