ቀጥታ, ኢራን ከዕውቅናዋ ውጪ በሆርሙዝ በኩል የሚደረጉ ጉዞዎች አደገኛ እንደሚሆኑ አስጠነቀቀች

በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚደረግ የመርከቦች እንቅስቃሴ በሙሉ ከኢራን ጋር በመቀናጀት ካልተደረገ ደኅንነቱ አስተማማኝ እንደማይሆን የኢራን ባለሥልጣን አስታወቁ።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. በቬንዙዌላ የመሬት መንቀጥቀጥ የሞቱ ሰዎች ቁጥር በእጥፍ መጨመሩ ተገለጸ

    በመሬት መንቀጥቀጡ የወደመ ሕንጻ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በቬንዙዌላ በደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ወደ 589 መድረሱን እና 2,980 ሰዎች መጎዳታቸውን የአገሪቱ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዴልሲ ሮዴሪጌዝ አስታወቁ።

    በፍርስራሾች ውስጥ ያሉ ሰዎችን ለማውጣት የሚደረገው ጥረት በቀጠለበት በአሁኑ ጊዜ ከተለያዩ አገራት እርዳታ ወደ ቬንዙዌላ እየገባ ነው።

    አሜሪካ ትናንት ሐሙስ ከፍተኛ መጠን ያለው እርዳታ ወደ አገሪቱ መላኳን ስታሳውቅ።ከስዊትዘርላንድ የተላኩ ሰማንያ የነፍስ አድን ሠራተኞች እና 18 ቶን ቁሳቁሶች ቬንዙዌላ መድረሳቸውን የአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘገበ።

    የቬንዙዌላ ቴሌቪዥን እንደዘገበው ከሆነ፣ ቡድኑ ዓርብ ማለዳ ላይ የደረሰ ሲሆን፣ ስምንት አነፍናፊ ውሻዎችም የተካተቱበት ነው።

    አክሎም፣ ከመሬት መንቀጥቀጡ ክስተት በኋላ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ በመስጠት ስዊትዘርላንድ ከመጀመሪያዎቹ አገራት መካከል መሆኗን ገልጿል።

    ከሜክሲኮም እንዲሁ ቁሳቁሶችን የያዙ የነፍስ አድን ሠራተኞች ወደ አገሪቱ መድረሳቸውን የቬንዙዌላ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ዴልሲ ሮድሪጌዝ ገልጸዋል።

    የዩናይትድ ስቴትስ ደቡባዊ ዕዝ ደግሞ አንድ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣኑ የዕዙን የድጋፍ ጥረት ለመከታተል መድረሳቸውን አስታውቋል።

  2. ኢራን ከዕውቅናዋ ውጪ በሆርሙዝ በኩል የሚደረጉ ጉዞዎች አደገኛ እንደሚሆኑ አስጠነቀቀች

    መርከብ

    በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚደረግ የመርከቦች እንቅስቃሴ በሙሉ ከኢራን ጋር በመቀናጀት ካልተደረገ ደኅንነቱ አስተማማኝ እንደማይሆን የኢራን ባለሥልጣን አስታወቁ።

    የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካዚም ጋሪባባዲ እንደተናገሩት በሆርሙዝ በኩል የሚደረግ ጉዞ ከኢራን ዕውቅና ውጪ ከሆነ ዋስትና እንደማይኖረው በማመልከት የትኛውም በመተላለፊያው ላይ የሚከፈት የባሕር መስመር ከኢራን ጋር በመቀናጀት ካልሆነ ዕግድ እንደሚጣልበት አስጠንቅቀዋል።

    ባለሥልጣኑ ይህንን ማስጠንቀቂያ በኤክስ ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት ኦማን ከተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የባሕር ትራንስፖርት ድርጅት ጋር በመሆን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ጊዜያዊ የመርከቦች የመተላለፊያ መስመር መክፈቷ ከተገለጸ በኋላ ነው።

    ቀደም ሲል ኢራን አዲስ ያቋቋመችው የሆርሙዝ ወሽመጥ እንቅስቃሴን የሚቆያጠረው ባለሥልጣን ዕውቅና ባልተሰጠው የባሕሩ ክፍል በኩል የሚተላለፉ መርከቦች ላይ ለሚያጋጥሙ ችግሮች ኃላፊነቱን የመርከቦቹ ካፒቴኖች እና የመርከቦቹ ባለቤቶች የሚወስዱ ይሆናል በማለት አስጠንቅቆ ነበር።

    የተባበሩት መንግሥታት መውጫ አጥተው በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ ለወራት የቆዩ መርከቦችን ለማሳለፍ በከፈተው መንገድ ጉዞ በጀመረ መርከብ ላይ ሐሙስ ዕለት ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ እንቅስቃሴዎች ተገትተዋል።

    ጥቃቱ የተፈጸመው የኢራን አብዮታዊ ዘብ በተባበሩት መንግሥታት የተከፈተው አዲስ የመርከቦች መተላለፊያ መስመር ከኢራን ዕውቅና ውጪ መሆኑን በማመልከት “ተቀባይነት የሌለው እና ሙሉ ለሙሉ አደገኛ” መሆኑን ካሳወቀ በኋላ ነው።

    የብሪታኒያ የባሕር ላይ ጉዞ ደኅንነት ተቋም ሐሙስ ዕለት እንዳለው መርከቡ ከኦማን ወደብ ደቡብ ምሥራቅ ላይ “ምንነቱ ባልታወቀ ተወንጫፊ” መመታቱን እና በሰው ላይ ጉዳት አለመድረሱን አስታውቋል።

    ኢራን በመርከቡ ላይ ጥቃቱን መፈጸሟን የአሜሪካ ባለሥልጣናት መናገራቸውን የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

  3. የተመድ የአቶሚክ ኃላፊ ለኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም “እጅግ ጠንካራ” የማረጋገጫ ስርዓት ያስፈልጋል አሉ

    የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኤነርጂ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኤነርጂ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ከመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ማብቃት በኋላ ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ እንዳይኖራት ለማረጋገጥ እንዲቻል “እጅግ ጠንካራ” የማረጋገጫ ስርዓት መዘርጋት እንዳለበት ተናገሩ።

    ጃፓን ውስጥ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ራፋኤል ግሮሲ፤ አሜሪካ እና ኢራን የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት የሚመሩት ተቋም ወደ የቴህራን የኒውክሌር ጣቢያዎች እንዲገባ ይፈቅዳል የሚል አቋማቸውን በድጋሚ ገልጸዋል።

    ይህንን አቋም ውድቅ ያደረገችው ኢራን፤ ከአሜሪካ ጋር የመጨረሻ ስምምነት እስከሚደረስ እና ማዕቀቦች እስከሚነሱ ድረስ ተቆጣጣሪዎች ወደ ቁልፍ የኒውክሌር ጣቢያዎች እንዲገቡ እንደማትፈቅድ ገልጻለች።

    ዋና ዳይሬክተሩ ግሮሲ ጃፓን ውስጥ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ይህ ስምምነት ነው፤ ስምምነቱን ለማስፈጸም ደግሞ የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኤነርጂ ተቋም ሊፈቀድለት እና ምርመራ ሊያካሄድ ይገባል። በቅርቡ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

    ግሮሲ፤ በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት “ዓላማው ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ ወደማምረት እንደማትሻገር ማረጋገጥ ይመስለኛል። የኢራን መንግሥት ይህ ዓላማ እንደሌለው በግልጽ አስታውቋል” ሲሉም ተናግረዋል።

    አክለውም ግን “እርግጥ ነው ዓላማን መግለጽ ብቻውን በቂ አይደለም። ተግባራዊ ሊሆን በሚችል መልኩ በተቻለ ፍጥነት እጅግ ጠንካራ የማረጋገጫ ስርዓት መዘርጋት ያስፈልገናል” ብለዋል።

    ኢራን ለአሁኑ የዋና ዳይሬክተሩ አስተያየት ምላሽ አልሰጠችም። ከዚህ ቀደም ግን የኒውክሌር ጉዳይ በሁለት ወራት ውስጥ ይደረሳል ተብሎ የሚጠበቀው የመጨረሻ ስምምነት እስከሚፈረም ድረስ እንደሚዘገይ ገልጻለች።

  4. በፈረንሳይ የተከተሰውን ከፍተኛ ሙቀት ተከትሎ ፓሪስ ውስጥ የመጠጥ ሽያጭ ላይ ዕገዳ ተጣለ

    ፊቷ ላይ በረዶ የምታደርግ እና ሌላ ሴት ተቀምጠው

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የፈረንሳይ ባለሥልጣናት በአገሪቱ በተከሰተው ከፍተኛ ሙቀት ምክንያት በሆስፒታሎች ውስጥ የሚፈጠረውን ጫና ለመቀን ሲሉ በዋና ከተማዋ ፓሪስ ውስጥ የአልኮል መጠጥ አጠቃቀም እና ሽያጭ ላይ ዕገዳ ጣሉ።

    የፓሪስ ከተማ ነዋሪዎች ከረቡዕ ከሰዓት እስከ ቅዳሜ ጠዋት ድረስ በሕዝብ ቦታዎች አልኮል እንዳይጠጡ ተከልክለዋል። ይህ ዕግድ ቅዳሜ እና እሁድ በተመሳሳይ ሰዓትም ተግባራዊ እንደሚሆን ተገልጿል።

    ከአርብ እስከ እሁድ ባሉት ዕገዳ በተጣለባቸው ሰዓታት ውስጥ መጠጥ ገዝቶ መንቀሳቀስም ተከልክሏል። ፈቃድ ያላቸው ባሮች እና ሬስቱራንቶች ግን ከዚህ ዕገዳ ውጪ ናቸው ተብሏል።

    ስፔን፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይን ያስጨነቀው የሙቀት ማዕበል ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ እየዞረ መሆኑ ተነግሯል። ጀርመን እና ቼክ ሪፐብሊክ እጅግ ከባድ ሁኔታ ሊገጥማቸው እንደሚችል የአየር ትንበያ ባለሙያዎች አስጠንቅቀዋል።

    ፈረንሳይ ውስጥ የሆስፒታሎችን ዝግጁነት ለማጠናከር እና ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን ለመጠበቅ ሲባል የጤና ስጋት ምጣኔው ወደ ከፍተኛ ደረጃ ከፍ መደረጉን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሴባስቲያን ሌኮርኑ ተናግረዋል።

    ረቡዕ በፈረንሳይ ለተከታታይ ሁለተኛ ቀን ከፍተኛ ሙቀት የተመዘገበበት ዕለት ሆኗል። የሙቀት ክብረ ወሰኑም መሰበር ቀጥሏል። ረዕቡ ምሽት አማካይ የሙቀት መጠኑ ቢያንስ 22 ሴሊሺዬስ እንደደረሰ ተመዝግቧል።

    በአገሪቱ ታሪክ ከፍተኛ የሆነ የሙቀት መጠን ከተመዘገበ በኋላ የፈረንሳይ ባለሥልጣናት ሕዝቡ ልማዱን እንዲያስተካክል አሳስበዋል። ወጣቶች እና አረጋውያን ተጋላጭ እንደሆኑም ተገልጿል።

  5. በሆርሙዝ የጭነት መርከብ ላይ ጥቃት በመድረሱ ተመድ ባሕርተኞችን ለማስወጣት የያዘውን እቅድ ገታ

    በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚጓዙ መርከቦች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በወሳኙ የባሕር መተላለፊያ ሆርሙዝ በኩል ስታልፍ በነበረ አንድ የጭነት መርከብ ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ፤ የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የማሪታይም ድርጅት በወሽመጡ ማለፊያ አጥተው የቆዩ ከ11,000 በላይ ባሕርተኞችን ለማስወጣት የያዘውን እቅድ በጊዜያዊነት አቆመ።

    ከዚህ ጥቃት አስቀድሞ በርካታ ጀልባዎች ማለፋቸውን የገለጹት የተቋሙ ዋና ኃላፊ አርሴኒዮ ዶሚንጌዝ፤ ሌሎች ጉዞዎችን ለማድረግ ግን በቅድሚያ “አስፈላጊው የደኅንነት ማረጋገጫ” መኖሩ ሊረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል።

    የብሪታንያ የባህር ላይ የደህንነት ተቋም ትናንት ሐሙስ ባወጣው መረጃ፤ በኦማን ከሚገኘው የዳሂት ወደብ በስተደቡብ ምስራቅ 7.5 ኖቲካል ማይል ርቀት ላይ አንዲት መርከብ “ምንነቱ ባልታወቀ ተተኳሽ” መመታቷን አስታውቋል። በዚህ ጥቃት በሰዎች ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ አልተገለጸም።

    ቫንጋርድ የተባለው የማሪታይም የስጋት አስተዳደር ተቋም ደግሞ ‘ኤቨር ላቭሊ’ የተባለችው ይህቺ በሲንጋፖር ባንዲራ የምትንቀሳቀስ መርከብ ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላም ጉዞዋን መቀጠሏን አስታውቋል።

    የአሜሪካ ባለስልጣናት፤ ኢራን መርከቧ ላይ ጥቃት ፈጽማለች ማለታቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስተዳደር ያቋቋመችው መስሪያ ቤት በበከሉ ከተቀመጡት መስመሮች ውጭ የሚጓዙ መርከቦች ደኅንነቱ የተጠበቀ ጉዞ የማድረግ ማረጋገጫ እንደማይኖራቸው አስጠንቅቋል።

    የፋርስ ባሕረ ሰላጤ ወሽመጥ ባለስልጣን በኤክስ ገጹ ባሰፈረው ጽሑፍ፤ "ከተፈቀዱት መንገዶች ውጭ በመጠቀም ምክንያት ለሚፈጠር ማንኛውም መዘዝ ኃላፊነቱ የመርከቡ ባለቤት፣ ኦፕሬተር እና ዋና ኃላፊ ይሆናል" ብሏል።

    አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር እያደረጉ ባለው ጦርነት የተነሳ ከየካቲት አንስቶ በመቶዎች የሚቆጠሩ መርከቦች እና በሺህዎች የሚቆጠሩ ባሕርተኞች በፋርስ ባሕረ ሰላጤ መውጫ አጥተው ቆመዋል።

    የተባበሩት መንግሥታት ማክሰኞ ዕለት እነዚህን መርከበኞች የማስወጣት እቅዱን ይፋ ያደረገው የሆርሙዝ ወሽመጥ በድጋሚ መከፈቱን ተከትሎ ነበር።

    ኢራን፣ ኦማን፣ አሜሪካ እና ሌሎች የባሕር ዳርቻው አገራት እንዲሁም የማሪታይም ኢንዱስትሪው የዚህ “ግዙፍ ኦፕሬሽን” ተባባሪዎች እንደሆኑ የተቋሙ ኃላፊ ዶሚኒጌዝ ገልጸው ነበር።

    አሁን የጭነት መርከቧ ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ ባወጡት መግለጫ ግን፤ “የተቀናጀ አካሄድ እና የጉዞ ደኅንነትን ለማረጋገጥ ሲባል ተጨማሪ ግልጽነት እስከሚኖር ድረስ የማስወጣት እቅዱ በጊዜያዊነት ይቆማል" ብለዋል።

  6. ኢራን በሆርሙዝ የሚያልፉ መርከቦችን ለማስከፈል ያላት ፍላጎት አደገኛ መሆኑን አሜሪካ አስጠነቀቀች

    በሆርሙዝ ላይ መርከቦች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦችን ለማስከፈል ያላት ፍላጎት ወደ ሌሎች የባሕር ላይ መተላለፊያዎች በመስፋፋት “ከባድ ቀውስ” ይፈጥራል ሲሉ አስጠነቀቁ።

    “የዓለም አቀፍ የባሕር መተላለፊያዎች የትኛውም አገር ንብረት አይደሉም። ይህም የዓለማችን መሠረታዊ መርኅ ሲሆን፣ ከዚያ ውጪ ቢሆን ኖሮ ግን ዓለማችን ሙሉ ለሙሉ በቀውስ ትታመስ ነበር” ሲሉ ባህሬን ውስጥ እየተካሄደ ባለው የባሕረ ሰላጤው አገራት የትብብር ምክር ቤት ስብሰባ ላይ መናገቸራውን ኤኤፍፒ ዘግቧል።

    “አገራት በአቅራቢያቸው ያሉ ዓለም አቀፍ የባሕር ላይ መተላለፊያዎችን በመቆጣጠር ገንዘብ ማስከፈል እንደሚችሉ ከተቀበልን፣ ይህ እንደ ወረርሽኝ በመላው ዓለም ይስፋፋል” በማለት ሩቢዮ አስጠንቅቀዋል።

    አሜሪካ እና አስራኤል በኢራን ላይ ጦርነት መክፈታቸውን ተከትሎ ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ከመዝጋቷ ባሻገር መተላለፊያውን በመቆጣጠር መርከቦች ክፍያ እንዲፈጽሙ የሚያስገድድ ሕግ አዘጋጅታለች።

    ነገር ግን ጦርነቱን ባስቆመው ከአሜሪካ ጋር በተደረሰው የመግባቢያ ሰነድ ላይ ሆርሙዝ ያለክፍያ ለሁሉም መርከቦች ክፍት እንደሚሆን ከስምምነት ቢደረስም ኢራን ግን ወሽመጡን ለመቆጣጠር የሚያስችላትን እርምጃ እየወሰደች ነው።

  7. በ3 ቀናት 57 የጭነት መርከቦች ከሆርሙዝ መውጣታቸውን ተመድ አስታወቀ

    ነዳጅ ጫኝ መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የተባበሩት መንግሥታት የባሕር ትራንስፖርት ድርጅት መረጃ በሆርሙዝ መዘጋት ምክንያት መውጫ አጥተው ከቆዩ መርከቦች መካከል ባለፉት ሦስት ቀናት 57 መርከቦች እና 1,100 ሠራተኞቻቸው ማለፋቸውን አስታወቀ።

    ከሆርሙዝ መከፈት በኋላ ለወራት የቆሙ በርካታ መርከቦች እና ከ11 ሺህ በላይ ሠራተኞቻቸው ከአካባቢው መውጣት ከጀመሩበት ካለፈው ሰኞ ወዲህ ምን ያህል መርከቦች መንቀሳቀሳቸውን ድርጅቱ መረጃ ሲያጋራ የመጀመሪያው ነው።

    ዓለም አቀፉ የባሕር ትራንስፖርት ድርጅት መርከቦችን እና ሠራተኞቸቻውን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል እንዲያልፉ የማድረጉ ሥራ በአሜሪካ እና በአካባቢው አገራት ቅንጅት የሚካሄድ መሆኑን ገልጿል።

    ድርጅቱ ባሠራጨው መረጃ ዛሬ ሐሙስ ጠዋት ላይ 12 መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ማለፋቸውን፣ ትናንት ረቡዕ 32፣ ማክሰኞ ደግሞ 13 መርከቦች ከባሕረ ሰላጤው አካባቢ ውጥተዋል።

    ከእነዚህ መርከቦች መካከል የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ንብረት የሆነችው ኤምቪ ጊቤ መርከብ ከወራት ቆይታ በኋላ ሐሙስ ዕለት ከሆርሙዝ ወሽመጥ መውጣቷን ድርጅቱ አስታውቋል።

  8. የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እናት አረፉ

    ወ/ሮ አዳነሽ በርሄ
    የምስሉ መግለጫ, ወ/ሮ አዳነሽ በርሄ

    የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እናት ወ/ሮ አዳነሽ በርሄ በ97 ዓመታቸው ማረፋቸውን የአገሪቱ ማስታወቂያ ሚኒስቴር አስታወቀ።

    ከኤርትራ ነጻነት አንስቶ ከ35 ዓመታት በላይ በብቸኝነት ኤርትራን እየመሩ ያሉት የ80 ዓመቱ አዛውንት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ እናት ያረፉት ሰኞ ዕለት ነበር።

    ትናንት ረቡዕ ሰኔ 17/2018 ዓ. ም. አሥመራ አቅራቢያ በሚገኘው የትውልድ ስፍራቸው በተፈጸመው ቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ፕሬዝዳንት ኢሳያስን ጨምሮ ቤተሰቦች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ከፍተኛ ባለሥልጣናት መገኘታቸውን የማስታወቂያ ሚኒስቴሩ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ አመለክቷል።

    የፕሬዝዳንት ኢሳያስ እና ወ/ሮ አዳነሽ በርሄ ከአቶ አፈወርቂ አብርሃ ጋር በትዳር በቆዩባቸው ጊዜያት 14 ልጆችን ያፈሩ ሲሆን፣ ዘጠኙ ለነጻነት በተካሄደው እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳተፊ እንደነበሩ ይነገራል።

    ወ/ሮ አዳነሽ በኤርትራ ውስጥ ጦርነቱ በሚካሄድበት ወቅት ወደ አሜሪካ ሄደው የኖሩ ሲሆን፣ ኤርትራ ነጻ አገር ስትሆን ተመልሰው እስከ ኅልፈታቸው ድረስ በኤርትራ ኖረዋል።

  9. የነዳጅ ዋጋ ከኢራን ጦርነት ወዲህ ባልታየ መጠን ቀነሰ

    ነዳጅ የሚቀዳ ግለሰብ

    የፎቶው ባለመብት, The Dallas Morning News via Getty Images

    መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል መጓጓዝ መቀጠላቸውን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ከኢራን ጦርነት ወዲህ ባልታየ መጠን ቀነሰ።

    የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በበርሜል ወደ 72.48 ዶላር ወርዷል። ይህም አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ ጥቃት ከሰነዘሩበት ቀን በፊት የነበረው ዋጋ ነው።

    ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን በመዝጋቷ ባለፉት ወራት የነዳጅ ዋጋ አሻቅቦ ነበር።

    ኢራን እና አሜሪካ የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረሙበት ዕለት አንስቶ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ እያሽቆለቆለ መጥቷል።

    የቴህራን እና ዋሽንግተን ልዑካን በስዊትዘርላንድ ውይይት ካደረጉ በኋላ አሜሪካ የኢራን የነዳጅ የወጪ ንግድ ላይ ጥላ የነበረውን ማዕቀብ አላልታለች።

    ስምምነት ከተፈራሙ በኋላ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚተላለፉ መርከቦች ቁጥር ጨምሯል።

    ድፍድር ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ እንዲሁም ማዳበሪያ እና ሌሎችም ሸቀጦች የጫኑ መርከቦች እየተላለፉ ይገኛሉ።

  10. ፊሊፒንስ በትምህርት ቤት ተኩስ በመክፈት የተጠረጠረ ታዳጊ ሲጫወት የነበረውን ጌም አገደች

    ‘ጎርቦክስ’ የተባለው ጌም

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በፊሊፒንስ ባልተለመደ ሁኔታ ትምህርት ቤት ውስጥ ተኩስ በመክፈት የተጠረጠረ ታዳጊ ሲጫወት የነበረው ‘ጎርቦክስ’ የተባለው ጌም ላይ ጊዜያዊ እገዳ ተጣለ።

    ያለፈው ሰኞ በተከፈተው ተኩስ ሦስት ተማሪዎች ሲገደሉ 20 የሚደርሱ ቆስለዋል።

    ተጠርጣሪዎቹ የ15 እና 14 ዓመት ታዳጊዎች ሲሆኑ፤ ሽጉጥ ይዘው ወደ ክፍል መግባታቸው ተዘግቧል።

    የ14 ዓመቱ ተጠርጣሪ ‘ጎርቦክስ’ የተባለውን ጌም ይጫወት እንደነበር ተገልጿል።

    ጉግል ፕለይ ላይ ጌሙ የተገለጸው “ተጫዋቾች ያሻቸውን ነገር ማውደም ይችላሉ። በመሣሪያ ወይም በፈንጂ በጭካኔ የተሞካ ፍልሚያ ያደርጋሉ” በሚል ነው።

    የፊሊፒንስ የሳይበር ደኅንነት ተቋም “የበይነ መረብ ገጹ ለአሰቃቂው ክስተት አስተዋጽኦ አድርጎ ሊሆን ይችላል” ብሏል።

    ጌሙ በጊዜያዊነት መታገዱ “ለተጠርጣሪዎቹ ድርጊት ምን ያህል ሚና እንደነበረው ለመመርመር እንደሚረዳም” ተገልጿል።

    ቢቢሲ ጌሙን ከሚያመርተው የጀርመኑ ኤፍቱጌምስ ኩባንያ አስተያየት ጠይቋል። በነውጠኛ ባህሪ እና በቪድዮ ጌም መካከል ትስስር መኖሩን የሚያረጋግጡ ሳይንሳዊ ምርምሮች የሉም።

  11. በኢራን ጦርነት ኔቶ "ተጠያቂ እንዲደረግ" የቴህራን ባለሥልጣን ጠየቁ

    ኢስማኤል ባጋይ

    የፎቶው ባለመብት, LightRocket via Getty

    የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ዋና ጸሐፊ የሰጡትን አስተያየት ተከትሎ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ “ኔቶ ተጠያቂ መደረግ አለበት” አሉ።

    ዋና ጸሐፊው ማርክ ሩተ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ “ኔቶ፤ የተባበሩት መንግሥታት አባል በሆነች አገር ላይ በተፈጸመ ሕገ ወጥ ጦርነት መሳተፉን በግልጽ አምነዋል” ሲሉ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

    “ይህም ዓለም አቀፍ ሕግን እንዲሁም የተመድን ስምምነት የሚጥስ” እንደሆነ አክለዋል።

    ኔቶ እና አባል አገራቱ “ተጠያቂ መደረግ አለባቸው” ሲሉም ኢስማኤል ባጋይ አሳስበዋል።

    ማርክ ሩተ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኔቶ በበቂ ሁኔታ አሜሪካን አልደገፈም ሲሉ ላቀረቡት ክስ ምላሽ ሰጥተዋል።

    ማርክ ለትራምፕ በሰጡት ምላሽ “አውሮፓ የአሜሪካ ኃያልነት መሳያ ነው” ብለዋል።

    ጣሊያን እና ሮማኒያን በዋናነት ጠቅሰው በኢራን ጦርነት አሜሪካን መደገፋቸውን ተናግረዋል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ይሄንን ንግግር መነሻ አድርገው “በኢራናውያን ላይ መጠነ ሰፊ ወንጀል ሲፈጸም ለምን እንዳገዙ ለሕዝባቸው እና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማስረዳት አለባቸው” ብለዋል።

    በቴህራን፣ ሚንዳብ፣ ላማርድ፣ ኢስፋሀን፣ ሳንዳጅ፣ ሀሜንዳን እና ሌሎችም የኢራን ከተሞች የተፈጠረውን በመጥቀስም ኔቶ ኃላፊነት እንዲወስድ አሳስበዋል።

    ከኔቶ ዋና ጸሐፊ አስተያየት በኋላ የጣሊያን መከላከያ ሚኒስቴር “የተዛባ ምሥል የሚሰጥ” ንግግር ነው ብለዋል።

    ጣሊያን የሰጠችው “የቴክኒክ፣ ሎጅስቲክ እና ወታደራዊ ያልሆነ ድጋፍ” እንደሆነም ተናግረዋል።

    ከአሜሪካ ጋር ካላቸው የትብብር ማዕቀፍ ውጭ የሆነ ጥያቄ ቀርቦ ከሆነ “ጣሊያን ፈቃዷን እንዳልሰጠች” አክለዋል።

    የአሜሪካ ጦር የጣሊያንን ወታደራዊ ሰፈሮች እንዲጠቀም እንዳልፈቀዱም ጠቅሰዋል።

  12. ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ለሚያልፉ መርከቦች ማሳሰቢያ አወጣች

    መርከቦች በሆርሙዝ ላይ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦች ሁሉ ለደኅንነታቸው ሲባል መጠቀም ያለባቸው በኢራን በተፈቀዱ ቦታዎች በኩል እንደሆነ እና እንቅስቃሴያቸውንም ቀድመው ማሳወቅ እንዳለባቸው የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ አስታወቀ።

    ዘቡ ይህንን መግለጫ ያወጣው በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ አዲስ የመርከቦች መተላለፊያ መስመር መከፈቱን የሚያመለክቱ ዘገባዎች መውጣታቸውን ተከትሎ ነው።

    ለወራት መተለላፊያ አጥተው ለቆዩት መርከቦች ተከፈተ የተባለው መስመር “ተቀባይነት የሌለው ሙሉ ለሙሉ ለመርከቦቹ አደገኛ ነው” በማለት አስጠንቅቋል።

    የኢራን አብዮታዊ ዘብ ባወጣው መግለጫ “በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ለማለፍ የተፈቀደበት መስመር በኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ የተገለጸው ብቻ ነው” መሆኑን በመግለጽ መርከቦች “ቻናል 16 በተባለው መስመር በኩል” ብቻ እና ከኢራን ጦር ኃይል ጋር በመነጋገር መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

    ረቡዕ ዕለት የሆርሙዝ ወሽመጥ ተጎራባች የሆነችው ኦማን ለረጅም ጊዜ መውጫ አጥተው የቆዩ መርከቦችን እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍ አዲስ የባሕር መስመር መክፈቷን አሳውቃ የነበረ ቢሆንም፣ የኢራን አብዮታዊ ዘብ ግን በመግለጫው ስለኦማን አዲስ የባሕር ላይ መስመር በቀጥታ ያለው ነገር የለም።

  13. የተመድ የአቶሚክ ኤነርጂ ኃላፊ በስምምነቱ መሠረት ተቆጣጣሪዎች የኢራንን የኒውክሌር ጣቢያዎች ይጎበኛሉ አሉ

    የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኤነርጂ ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኤነርጂ ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ

    የዓለም አቀፉ የኒውክሌር ተቋም ኃላፊ፤ አሜሪካ እና ኢራን በደረሱት የመጀመሪያ ደረጃ የሰላም ስምምነት መሠረት ተቆጣጣሪዎች በቴህራን የኒውክሌር ጣቢያዎች ተገኝተው ምርመራ እንደሚያደርጉ ተናገሩ።

    የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኤነርጂ ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ግሮሲ ጃፓን ውስጥ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ “በእርግጥም ምርመራ ይካሄዳል” ብለዋል። የሚካሄድበትን “መንገድ፣ ቀን፣ ሂደት፣ ቦታ [በተመለከተ] እንሰራለን፤ በጣም በቅርቡ” ሲሉም አክለዋል።

    የኢራንን እጅግ የበለጸገ ዩራኒየም የመበረዝ ተግባር በዓለም አቀፉ የኒውክሌር ተቋም ቁጥጥር እንደሚካሄድ ባለፈው ሳምንት የተፈረመው ስምምነት ላይ “በግልጽ” እንደሰፈረም ገልጸዋል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ግን ጉዳት የደረሰባቸው የአገሪቱ የኒውክሌር ተቋማት እና የኒውክሌር ቁሶችን የተመለከተ ሥራ ሊከናወን የሚችለው ከአሜሪካ ጋር በሚደረስ የመጨረሻ ስምምነት ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ እንደሚሆን ተናግረዋል።

    የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኤነርጂ ዋና ዳይሬክተር ይህንን አስተያየት የሰጡት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ስለ ስምምነቱ ለመወያየት የባሕረ ሰላጤው አገራትን እየጎበኙ ባለበት ወቅት ነው።

    አሜሪካ እና ኢራን የተፈራረሙት የመጀመሪያ ስምምነት፤ ቴህራን በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚደረግ የመርከቦች ጉዞን እንደምትፈቅድ፤ ዋሽንግተን ደግሞ በኢራን ወደቦች ላይ የጣለችውን የጉዞ እገዳ እንደምታነሳ ያትታል።

    ባለፉት ቀናት የተመድ የኒውክሌር ተቆጣጣሪዎች ወደ ቴህራን የመግባታቸው ጉዳይ ላይ አሜሪካ እና ኢራን የተቃረነ አስተያየት ሰጥተዋል።

    የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ በስዊትዘርላንድ ከኢራን ዋና ተደራዳሪ ጋር ካደረጉት ንግግር በኋላ ቴህራን “የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኤነርጂ ተቆጣጣሪዎች ወደ አገሪቱ እንዲመለሱ ለመጋበዝ ተስማምታለች” ሲሉ ተደምጠዋል።

    በቀጣዩ ቀን አስተያየት የሰጡት የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ግን በጉዳዩ ላይ የተደረገ “ምንም ዝርዝር ውይይት” እንደሌለ ተናግረዋል።

    ኢራን፤ የተቋሙ ተቆጣጣሪዎች ባለፈው ዓመት ከእስራኤል ጋር በተደረገው የ12 ቀናት ጦርነት ድብደባ ወደተፈጸመባቸው የኒውክሌር ተቋማት እንዲሄዱ የማድረግ እቅድ እንደሌላትም ገልጸዋል።

  14. የአሜሪካ እና ኢራን ቴክኒካዊ ንግግር በሚቀጥለው ሳምንት ድጋሚ እንደሚጀመር ተገለጸ

    የሚጨባበጡ ሰዎች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካ እና ኢራን ቴክኒካዊ ንግግር በሚቀጥለው ሳምንት በድጋሚ እንደሚጀመር የአሸማጋይዋ ፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

    “ምናልባት ማክሰኞ” ዕለት ይጀመራል የተባለው ቀጣዩ ቴክኒካዊ ንግግር የሚካሄድበት ቦታ ግን ይፋ አልተደረገም።

    ስዊትዘርላድ ውስጥ የተካሄደው የሁለቱ አገራት የመጀመሪያው ዙር ንግግር እሁድ ዕለት ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ አገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ስዊዘርላንድን ለቅቀው ሄደዋል።

    የቴክኒካል ልዑካኖቻቸው ግን ሰኞ ዕለትም ንግግር ማድረግ ቀጥለው ነበር።

    ማክሰኞ ዕለት የኢራን የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ካዜም ኸሪባባዲ የመጀመሪያው ዙር የቴክኒካል ንግግር መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

    ተደራዳሪዎቹ “የማዕቀብ መነሳት”፣ “የኒውክሌር ጉዳይ”፣ “የኢኮኖሚ መልሶ ግንባታ እና ልማት” እንዲሁም “የቁጥጥር እና ትግበራ” ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ አራት ቡድኖችን ማቋቋማቸውንም ገልጸዋል።

    እነዚህ የስራ ቡድኖች አሜሪካ እና ኢራን የፈረሙትን የመግባቢያ ስምምነት ቴክኒካዊ ዝርዝር ጉዳዮች አፈጻጸምን የመከታተል ኃላፊነት ይኖራቸዋል።

  15. ፈረንሳይ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢቦላ የተያዘ ሰው መገኘቱን አረጋገጠች

    የሕክምና ጓንት ያደረገ የጤና ባለሙያ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ የሰብአዊ ረድኤት ተልዕኮ ላይ ሲሳተፍ ቆይቶ የተመለሰ አንድ ዶክተር ላይ የኢቦላ ቫይረስ መገኘቱን የፈረንሳይ መንግሥት አስታወቀ። የሕክምና ባለሙያው ፈረንሳይ ውስጥ በኢቦላ መያዙ የተረጋገጠ የመጀመሪያው ሰው ሆኗል።

    የፈረንሳይ ጤና ሚኒስቴር ዛሬ ረቡዕ ባወጣው መግለጫ፤ ዶክተሩ "ወዲያውኑ ወደ ልዩ የህክምና ተቋም መግባቱን" እና አሁን በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።

    ዴሞክራቲክ ኮንጎ የኢቦላ ወረርሽኝ መከሰቱን ይፋ ያደረገችው ባለፈው ወር ቢሆንም፤ ባለሙያዎች በሽታው መከሰቱ ከመታወጁ ሳምንታት አስቀድሞ ሲሰራጭ እንደነበረ ያምናሉ።

    በማዕከላዊ አፍሪካዊቷ አገር ውስጥ በተከሰተው በሽታ ምክንያት ከ260 በላይ ሰዎች እንደሞቱ ተረጋግጧል። አንድ ሺህ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ተይዘዋል።

    ባለፈው ወር ዴሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ በበሽታው የተያዘ ሰው ጀርመን ውስጥ ሕክምና ሲያገኝ የነበረ ቢሆንም በአውሮፓው የኢቦላ መገኘቱ ሲረጋገጠ የአሁኑ የመጀመሪያው ነው።

    የኮንጎ ጎረቤት የሆነችው ዩጋንዳም በኢቦላ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን አረጋግጣለች። የዓለም ጤና ድርጅት ዩጋንዳ ውስጥ 20 ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን እና ሁለት ሰዎች መሞታቸውን እንደተረጋገጠ ገልጿል።

    የፈረንሳይ ጤና ሚኒስቴር በዛሬው መግለጫው በሕዝቡ ውስጥ በሽታው የመሠራጨቱ የስጋት መጠን “እጅግ ዝቅተኛ” መሆን በአጽንኦት አንስቷል።

    ባለሥልጣናት ከዶክተሩ ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች ለመለየት እየሰሩ መሆኑንም አክሏል።

    የጤና ባለሙያዎች ከሰውነት በሚወጡ ፈሳሾች ለሚተላለፈው ኢቦላ የበለጠ ተጋላጭነት አላቸው።

    አሁን የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ ቡንዲቡግዮ በተባለው የቫይረሱ ዝርያ የመጣ ሲሆን ይህ ዝርያ እስካሁን ክትባት አልተገኘለትም።

  16. ጊቤ የተባለችው የኢትዮጵያ መርከብ ከሆርሙዝ ወሽመጥ ወጥታ ወደ ጂቡቲ ጉዞ ጀመረች

    ጊቤ መርከብ እና ሠራተኞቿ

    የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Shipping and Logistics

    በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል መተላለፊያ አጥታ የነበረችው ጊቤ የተባለችው የኢትዮጵያ መርከብ ጉዞ መጀመሯ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አስታወቀ።

    ባለፈው የካቲት ወር መጨረሻ ላይ በባሕረ ሰላጤው ጦርነት ሲጀመር ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ለወራት ዘግታው ቆይታለች።

    ወሽመጡ በቀን አስከ 140 ግዙፍ የጭነት መርከቦች የሚተላለፉበት ወሳኝ መስመር ነበር።

    መተላለፊያው በመዘጋቱ የኢትዮጵያን ጨምሮ 1,150 የጭነት መርከቦች እና ከ20 ሺህ በላይ የመርከቦቹ ሠራtኞች ለወራት ቆመው ለመጠበቅ ተገደዋል።

    ሁሉም መርከቦቹ በአጠቃላይ 125 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ጭነት ይዘው ነበር የቆሙት።

    በጦርነቱ ወቅት ለማለፍ የሞከሩ 32 የጭነት መርከቦች በሚሳዔል ወይም በድሮን ተመትተዋል። በዚህም ከመርከቦቹ ሠራተኞች 10 ሰዎች መሞታቸው እና ሌሎች በርካታ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ተረጋግጧል።

    ኢራን እና አሜሪካ ጦርነቱን ለማቆም ከተስማሙ በኋላ ሆርሙዝ እንደገና ክፍት ተደርጓል። ለወራት መተላለፊያ አጥተው ከነጭነታቸው የቆሙት መርከቦች አሁን ወደየመዳረሻቸው ጉዞ ጀምረዋል።

    ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያዋ መርከብ 'ኤምቪ ጊቤ' ጉዞ መጀመሯን የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አስታውቋል።

    የኢትዮጵያ መርከብ በኦማን ገልፍ በኩል ወደ ጂቡቲ በመጓዝ ላይ መሆኗ ተገልጿል። እሁድ ሰኔ 21 ምሽት 2:00 ሰዓት ጂቡቲ ወደብ እንደምትደርስም እየተጠበቀ ነው።

  17. በኬንያ ታዳጊዎች ከሞቱበት የእሳት አደጋ ጋር በተያያዘ ተማሪዎች ሊከሰሱ ነው

    ክስ የሚመሠረትባቸው ተማሪዎች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ባለፈው ወር በኬንያ ትምህርት ቤት ከተነሳው እና ታዳጊዎች ከሞቱበት የእሳት አደጋ ጋር በተያያዘ ተማሪዎች ላይ ክስ ለመመሥረት እየተዘጋጀ መሆኑን የአገሪቱ ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ።

    ከ15 እስከ 18 ዓመት የሚሆናቸው አስራ ስድስት ተማሪዎች በእሳት አደጋው ምክንያት መሞታቸው ይታወሳል። ሌሎች ብዙ ተማሪዎች ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። ዐቃቤ ሕግ እንዳለው በርካታ ተማሪዎች በግድያ ወንጀል ይከሰሳሉ።

    ከመዲናዋ ናይሮቢ በ120 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ጊልጊል ከተማ በሚገኝ የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ በተማሪዎች መኝታ ክፍል እሳት መነሳቱ ሕዝቡን አስቆጥቷል።

    ስምንት ተማሪዎች በእሳት አደጋው እጃቸው አለበት በሚል በፖሊስ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

    ተማሪዎቹ ፍራሽ በማቃጠል እሳቱ እንዲስፋፋ ማድረጋቸው ተገልጿል።

    እሳቱ 135 ተደራራቢ አልጋዎች ባሉበት መኝታ ክፍል የመጀመሪያ ሕንጻ ላይ ነበር የተነሳው። የድንገተኛ ጊዜ በር ለመክፈት ያልቻሉት በሕንጻው የሚኖሩት 202 ተማሪዎች በአንድ አቅጣጫ ብቻ በሚገኝ በር ለመውጣት ተገድደዋል።

    ፖሊስ እንዳለው በተማሪዎች እና በሠራተኞች ላይ ምርመራ ከተደረገ፣ የደኅንነት ካሜራ ተንቀሳቃሽ ምሥል ከተፈተሸ እና የፎረንሲክ ምርመራ ከተደረገ በኋላ ስምንት ተማሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

    ተማሪዎቹ በግድያ ወንጀል ተከስሰው ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡም ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል።

  18. የሊባኖስን ጦርነት ማስቆም የኢራንን ጦርነት የማስቆም ያህል ዋጋ እንዳለው የቴህራን ባለሥልጣን ተናገሩ

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ መሐመድ ባጋር ጋባሊፍ

    የፎቶው ባለመብት, Tasnim News Agency via Reuters

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ መሐመድ ባጋር ጋባሊፍ “በሊባኖስ ያለውን ጦርነት ማስቆም የኢራንን ጦርነት የማስቆም ያህል ዋጋ አለው” ሲሉ ተናገሩ።

    በአዘርባጃን፣ ባኩ እየተካሄደ ባለው የእስላዊ ትብብር ተቋማት የምክር ቤት ኅብረት ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር “ለእኛ የሊባኖስ የተኩስ አቁም የኢራን የተኩስ አቁም ያህል ዋጋ አለው። በተጨማሪም በሊባኖስ ያለውን ጦርነት ማስቆም የኢራንን ጦርነት የማስቆም ያህል ዋጋ አለው” ብለዋል።

    ኢራን እና አሜሪካ የፈረሙት የመግባቢያ ሰነድ ሊባኖስን ጨምሮ በሁሉም ግንባሮች ውጊያ ማቆምን ያካትታል።

    ዋነኛው ተደራዳሪ የሆኑት የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ መሐመድ ባጋር ጋባሊፍ “የኢስላማባድ ስምምነት የአሜሪካን ሽንፈት አውጇል” ብለዋል።

    የጦርነቱ ዓላማ “በቀጣናው ስትራቴጂያዊ የአሰላለፍ ለውጥ ለማምጣት እና ይህንንም በነጻ አገር ላይ መጫን” እንደሆነም ተናግረዋል።

    ከቀጣናው “የውጭ ኃይሎችን ማስወጣት ስትራቴጂያዊ ድል ነው” ሲሉም አክለዋል።

    ኢራን እርስ በርስ በመከባበር እና ጣልቃ ባለመግባት መርህ ከሙስሊም አገራት ጋር ለመተባበር ዝግጁ መሆኗንም ገልጸዋል።

  19. አሜሪካ እና እስራኤል ደቡብ ሊባኖስን ለአገሪቱ ጦር የማስረከብ ዕቅድ ማውጣታቸው ተዘገበ

    ትራምፕ እና ኔታንያሁ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አሜሪካ ድጋፏን በሰጠችው ዕቅድ መሠረት እስራኤል እና ሊባኖስ፤ የደቡብ ሊባኖስ አስተዳደርን ለአገሪቱ ጦር ለማስረከብ ማሰባቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገበ።

    ሮይተርስ ከፍተኛ የእስራኤል ባለሥልጣናት የሆኑ ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ በዚህ ዕቅድ ውስጥ የሚካተቱ የሊባኖስ ኃይሎች ከአሜሪካ ሥልጠና ይሰጣቸዋል።

    ከሄዝቦላህ ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው ለማረጋገጥም የደኅንነት ማጣራት ይደረጋል።

    የዜና ወኪሉ የጠቀሳቸው ምንጮች እንዳሉት፤ በደቡብ ሊባኖስ ያሉ አካባቢዎች ለአገሪቱ ጦር ተላልፈው እስከሚሰጡ ድረስ እስራኤል ቀጣናውን እየተቆጣጠረች ትቆያለች።

    አሜሪካ እና እስራኤል በይፋ አስተያየታቸውን አልሰጡም። እስራኤል እና ሊባኖስ ዛሬ ረቡዕ በዋሽንግተን ውይይት እያደረጉ ይገኛሉ።

  20. ተመድ ከሆርሙዝ ወሽመጥ 11 ሺህ መርከበኞችን እንደሚያስወጣ አስታወቀ

    የሆርሙዝ ወሽመጥ

    የፎቶው ባለመብት, Atta Kenare / Getty Images

    የተባበሩት መንግሥታት ማሪታይም ባለሥልጣን በኢራን ጦርነት ሳቢያ በሆርሙዝ ወሽመጥ የቀሩ 11 ሺህ መርከበኞችን እንደሚያስወጣ አስታወቀ።

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ በከፈቱት ጦርነት ሳቢያ መርከበኞቹ ከባሕረ ሰላጤው አካባቢ ለመውጣት ሳይችሉ ቆይተዋል።

    የተመድ ማሪታይም ባለሥልጣን (አይኤምኦ) ዋና ጸሐፊ አርሴኒዮ ዶሚኒገዝ እንደተናገሩት ከኢራን፣ አሜሪካ፣ ኦማን እና ሌሎችም የባሕረ ሰላጤው አገራት እንዲሁም የማሪታይም ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር “መጠነ ሰፊ ኦፕሬሽን” ይካሄዳል።

    “ደኅንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ማስወጣት የምንችልበት መንገድ ዘርግተናል” ብለዋል።

    አሜሪካ እና ኢራን የመግባቢያ ሰነድ ላይ ፊርማቸውን ቢያኖሩም ዝርዝሩን በተመለከተ የሚቃረኑ መረጃዎች እያወጡ ይገኛሉ።

    በመግባቢያ ሰነዱ መሠረት ዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ በኢራን ፍተሻ ማድረግ እንደሚችል ዋሽንግተን ብትገልጽም፤ ቴህራን አስተባብላለች።

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦችን ምንም ዓይነት ክፍያ መጠየቅ እንደማትችል ገልጸዋል።

    ሚኒስትሩ እንደተናገሩት ክፍያ መጠየቅ የኢራን እና አሜሪካን ስምምነት የሚጥስ እና ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር የሚቃረን ነው።

    ኢራን በበኩሏ ከኦማን ጋራ ባወጣችው መግለጫ የሆርሙዝ ወሽመጥ የሚገኝበትወሳኝ የባሕር መተላለፊያላይ ሉዓላዊ መብት ያላቸው ሁለቱ አገራት መሆናቸውን አስታውቃለች።

    አገራቱ ጥምር ኮሚቴ አቋቁመው የሆርሙዝ ወሽመጥ አስተዳደር እና መርከቦች ለመተላለፍ የሚፈጽሙትን ክፍያ ጉዳይ በጋራ እንደሚመለከቱም ገልጸዋል።

    የሆርሙዝ ወሽመጥ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters