በሆርሙዝ የጭነት መርከብ ላይ ጥቃት በመድረሱ ተመድ ባሕርተኞችን ለማስወጣት የያዘውን እቅድ ገታ
በወሳኙ የባሕር መተላለፊያ ሆርሙዝ በኩል ስታልፍ በነበረ አንድ የጭነት መርከብ ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ፤ የተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የማሪታይም ድርጅት በወሽመጡ ማለፊያ አጥተው የቆዩ ከ11,000 በላይ ባሕርተኞችን ለማስወጣት የያዘውን እቅድ በጊዜያዊነት አቆመ።
ከዚህ ጥቃት አስቀድሞ በርካታ ጀልባዎች ማለፋቸውን የገለጹት የተቋሙ ዋና ኃላፊ አርሴኒዮ ዶሚንጌዝ፤ ሌሎች ጉዞዎችን ለማድረግ ግን በቅድሚያ “አስፈላጊው የደኅንነት ማረጋገጫ” መኖሩ ሊረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የብሪታንያ የባህር ላይ የደህንነት ተቋም ትናንት ሐሙስ ባወጣው መረጃ፤ በኦማን ከሚገኘው የዳሂት ወደብ በስተደቡብ ምስራቅ 7.5 ኖቲካል ማይል ርቀት ላይ አንዲት መርከብ “ምንነቱ ባልታወቀ ተተኳሽ” መመታቷን አስታውቋል። በዚህ ጥቃት በሰዎች ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ አልተገለጸም።
ቫንጋርድ የተባለው የማሪታይም የስጋት አስተዳደር ተቋም ደግሞ ‘ኤቨር ላቭሊ’ የተባለችው ይህቺ በሲንጋፖር ባንዲራ የምትንቀሳቀስ መርከብ ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላም ጉዞዋን መቀጠሏን አስታውቋል።
የአሜሪካ ባለስልጣናት፤ ኢራን መርከቧ ላይ ጥቃት ፈጽማለች ማለታቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስተዳደር ያቋቋመችው መስሪያ ቤት በበከሉ ከተቀመጡት መስመሮች ውጭ የሚጓዙ መርከቦች ደኅንነቱ የተጠበቀ ጉዞ የማድረግ ማረጋገጫ እንደማይኖራቸው አስጠንቅቋል።
የፋርስ ባሕረ ሰላጤ ወሽመጥ ባለስልጣን በኤክስ ገጹ ባሰፈረው ጽሑፍ፤ "ከተፈቀዱት መንገዶች ውጭ በመጠቀም ምክንያት ለሚፈጠር ማንኛውም መዘዝ ኃላፊነቱ የመርከቡ ባለቤት፣ ኦፕሬተር እና ዋና ኃላፊ ይሆናል" ብሏል።
አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር እያደረጉ ባለው ጦርነት የተነሳ ከየካቲት አንስቶ በመቶዎች የሚቆጠሩ መርከቦች እና በሺህዎች የሚቆጠሩ ባሕርተኞች በፋርስ ባሕረ ሰላጤ መውጫ አጥተው ቆመዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ማክሰኞ ዕለት እነዚህን መርከበኞች የማስወጣት እቅዱን ይፋ ያደረገው የሆርሙዝ ወሽመጥ በድጋሚ መከፈቱን ተከትሎ ነበር።
ኢራን፣ ኦማን፣ አሜሪካ እና ሌሎች የባሕር ዳርቻው አገራት እንዲሁም የማሪታይም ኢንዱስትሪው የዚህ “ግዙፍ ኦፕሬሽን” ተባባሪዎች እንደሆኑ የተቋሙ ኃላፊ ዶሚኒጌዝ ገልጸው ነበር።
አሁን የጭነት መርከቧ ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ ባወጡት መግለጫ ግን፤ “የተቀናጀ አካሄድ እና የጉዞ ደኅንነትን ለማረጋገጥ ሲባል ተጨማሪ ግልጽነት እስከሚኖር ድረስ የማስወጣት እቅዱ በጊዜያዊነት ይቆማል" ብለዋል።