የተመድ የአቶሚክ ኃላፊ ለኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም “እጅግ ጠንካራ” የማረጋገጫ ስርዓት ያስፈልጋል አሉ
የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኤነርጂ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ከመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ማብቃት በኋላ ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ እንዳይኖራት ለማረጋገጥ እንዲቻል “እጅግ ጠንካራ” የማረጋገጫ ስርዓት መዘርጋት እንዳለበት ተናገሩ።
ጃፓን ውስጥ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ራፋኤል ግሮሲ፤ አሜሪካ እና ኢራን የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት የሚመሩት ተቋም ወደ የቴህራን የኒውክሌር ጣቢያዎች እንዲገባ ይፈቅዳል የሚል አቋማቸውን በድጋሚ ገልጸዋል።
ይህንን አቋም ውድቅ ያደረገችው ኢራን፤ ከአሜሪካ ጋር የመጨረሻ ስምምነት እስከሚደረስ እና ማዕቀቦች እስከሚነሱ ድረስ ተቆጣጣሪዎች ወደ ቁልፍ የኒውክሌር ጣቢያዎች እንዲገቡ እንደማትፈቅድ ገልጻለች።
ዋና ዳይሬክተሩ ግሮሲ ጃፓን ውስጥ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ይህ ስምምነት ነው፤ ስምምነቱን ለማስፈጸም ደግሞ የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኤነርጂ ተቋም ሊፈቀድለት እና ምርመራ ሊያካሄድ ይገባል። በቅርቡ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።
ግሮሲ፤ በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት “ዓላማው ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ ወደማምረት እንደማትሻገር ማረጋገጥ ይመስለኛል። የኢራን መንግሥት ይህ ዓላማ እንደሌለው በግልጽ አስታውቋል” ሲሉም ተናግረዋል።
አክለውም ግን “እርግጥ ነው ዓላማን መግለጽ ብቻውን በቂ አይደለም። ተግባራዊ ሊሆን በሚችል መልኩ በተቻለ ፍጥነት እጅግ ጠንካራ የማረጋገጫ ስርዓት መዘርጋት ያስፈልገናል” ብለዋል።
ኢራን ለአሁኑ የዋና ዳይሬክተሩ አስተያየት ምላሽ አልሰጠችም። ከዚህ ቀደም ግን የኒውክሌር ጉዳይ በሁለት ወራት ውስጥ ይደረሳል ተብሎ የሚጠበቀው የመጨረሻ ስምምነት እስከሚፈረም ድረስ እንደሚዘገይ ገልጻለች።