በፈረንሳይ የተከተሰውን ከፍተኛ ሙቀት ተከትሎ ፓሪስ ውስጥ የመጠጥ ሽያጭ ላይ ዕገዳ ተጣለ
የፈረንሳይ ባለሥልጣናት በአገሪቱ በተከሰተው ከፍተኛ ሙቀት ምክንያት በሆስፒታሎች ውስጥ የሚፈጠረውን ጫና ለመቀን ሲሉ በዋና ከተማዋ ፓሪስ ውስጥ የአልኮል መጠጥ አጠቃቀም እና ሽያጭ ላይ ዕገዳ ጣሉ።
የፓሪስ ከተማ ነዋሪዎች ከረቡዕ ከሰዓት እስከ ቅዳሜ ጠዋት ድረስ በሕዝብ ቦታዎች አልኮል እንዳይጠጡ ተከልክለዋል። ይህ ዕግድ ቅዳሜ እና እሁድ በተመሳሳይ ሰዓትም ተግባራዊ እንደሚሆን ተገልጿል።
ከአርብ እስከ እሁድ ባሉት ዕገዳ በተጣለባቸው ሰዓታት ውስጥ መጠጥ ገዝቶ መንቀሳቀስም ተከልክሏል። ፈቃድ ያላቸው ባሮች እና ሬስቱራንቶች ግን ከዚህ ዕገዳ ውጪ ናቸው ተብሏል።
ስፔን፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይን ያስጨነቀው የሙቀት ማዕበል ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ እየዞረ መሆኑ ተነግሯል። ጀርመን እና ቼክ ሪፐብሊክ እጅግ ከባድ ሁኔታ ሊገጥማቸው እንደሚችል የአየር ትንበያ ባለሙያዎች አስጠንቅቀዋል።
ፈረንሳይ ውስጥ የሆስፒታሎችን ዝግጁነት ለማጠናከር እና ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን ለመጠበቅ ሲባል የጤና ስጋት ምጣኔው ወደ ከፍተኛ ደረጃ ከፍ መደረጉን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሴባስቲያን ሌኮርኑ ተናግረዋል።
ረቡዕ በፈረንሳይ ለተከታታይ ሁለተኛ ቀን ከፍተኛ ሙቀት የተመዘገበበት ዕለት ሆኗል። የሙቀት ክብረ ወሰኑም መሰበር ቀጥሏል። ረዕቡ ምሽት አማካይ የሙቀት መጠኑ ቢያንስ 22 ሴሊሺዬስ እንደደረሰ ተመዝግቧል።
በአገሪቱ ታሪክ ከፍተኛ የሆነ የሙቀት መጠን ከተመዘገበ በኋላ የፈረንሳይ ባለሥልጣናት ሕዝቡ ልማዱን እንዲያስተካክል አሳስበዋል። ወጣቶች እና አረጋውያን ተጋላጭ እንደሆኑም ተገልጿል።