ፒት ሄግሴት አውሮፓ የአደገኛ ርዕዮተ ዓለሞች “ወረራ” ተጋርጦባታል በማለት የስደተኛ ፖሊሲን ተቹ

የአሜሪካው መከላከያ ሚኒስትር በፈረንሳይ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት መታሰቢያ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር የአውሮፓ አገራትን የስደተኞች ፖሊሲ ነቀፉ። ሚኒስትሩ በንግግራቸው አንዳንድ የአውሮፓ አገራት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች እንዲገቡ መፍቀዳቸውን ተችተው “ወረራ” ሲሉ ጠርተውታል። “የሚያሳዝነው፣ ዛሬ፣ የአውሮፓ የባሕር ዳርቻዎች በተለያዩ አደገኛ ርዕዮተ ዓለሞች ተወርሯል” ብለዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ፔንታጎን የእስራኤል ስለላ እንደሚያሳስበው ተገለጸ

    ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ፔንታጎን እስራኤል ከፍተኛ ልዑኮችን ጨምሮ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን መሰለሏን በመጥቀስ “አሳሳቢ” መሆኑን ገለጸ።

    ሁለቱ አገራት ኢራን ላይ በጥምረት ጦርነት ቢከፍቱም በኋላ ላይ በሊባኖስ የተነሳ በመካከላቸው ውጥረት ሰፍኗል።

    ለኤንቢሲ መረጃውን ያቀበሉ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ፔንታጎን እስራኤል ከፍተኛ የአገሪቱን ባለሥልጣናት በቀጣናው ግጭት ዙሪያ የሚያደረጉትን ክርክሮችን ለማወቅ በሚል ትሰልላለች ብሎ እንደሚያምን ተናግረዋል።

    እንደ ዘገባው ከሆነ የፔንታጎን የመከላከያ ደህንነት ኤጀንሲ እስራኤል በቅርብ ሳምንታት ያደረገችውን ስለላዎች በሚመለከት ደረጃውን “አሳሳቢ” ወደሚል ከፍ ማድረጉን በውስጥ የተለዋወጧቸው መልዕክቶች ላይ አስፍሯል።

    አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ፔንታጎን የእስራኤልን ስለላ በሚመለከት ባለ ሰባት ገጽ ሪፖርት ማዘጋጀቱን እና አሳሳቢ ያላቸውን ክስተቶች ዘርዝሯል ብለዋል።

    ባለሥልጣናቱ የደህንነት መረጃዎችን የማሰባሰብ ደረጃው በሁለት ወዳጅ አገራት መካከል ከሚጠበቀው ያለፈ መሆኑን ጠቅሰዋል።

    ነገር ግን አንድ የተናጠል ክስተት የስጋት ደረጃውን ከፍ ያድርገው ወይም ተከታታይ እርምጃዎች ግልጽ አላደረጉም።

    እስራኤል የአሜሪካን ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ መሰለሏን ኒውዮርክ ታይምስ ቅዳሜ ዕለት የአገሪቱን ባለሥልጣናት ጠቅሶ ዘግቧል።

    ዊትኮፍ ከኢራን ጋር በሚካሄደው፣ እስራኤል ከሐማስ ጋር እንደሁም ዩክሬን እና ሩሲያ ጋር በምታደርጋቸው ድርድሮች ላይ ይሳተፋሉ።

    የመገናኛ ብዙኃኑ የደህንነት ሪፖርቶችን በመጥቀስ የአሜሪካ ባለሥልጣናት እስራኤል በከፍተኛ የመከላከያ ባለሥልጣናት በተለይ ኢልብሪጅ ኮልቢ እና ምክትላቸው ማይክል ፒ ዲሞኖ ላይ የምታካሄደውን ስለላ ማጠናከሯ እንዳሳሰባቸው ዘግበዋል።

    ስለላው እስራኤል የኮሙኑኬሽን መስመራቸውን መጥለፍ ወይንም በአሜሪካ የፖሊሲ ውይይት ላይ በተለይ ከኢራን ጋር በሚደረገው ድርድር መረጃዎችን መሰብሰብ እንደሚሆን ተናግረዋል።

    ታይምስ የጠቀሳቸው አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን ትራምፕ ባለፈው ዓመት ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ እስራኤል በአሜሪካ ባለስልጣናት ላይ የምታደርገው የተጠናከረ ስለላ “ያልተጠበቀ ነው” ብለዋል።

    ኒውዮርክ ታይምስም ሆነ ኤንቢሲ ከፔንታጎን ምላሽ ለማግኘት ያደረጉት ጥረት አለመሳካቱን ጠቅሰዋል።

  2. የዩኬ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጄዲ ቫንስ “የስደተኞች ወረራ” በሚል የሰጡት አስተያየት “ስህተት” እንደሆነ እንደነገሯቸው ገለፁ

    የዩናይትድ ኪንግደም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትት ዴቪድ ላሚ የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ፤ ሄነሪ ኖዋክ በተባለው ታዳጊ ግድያ ዙሪያ የሰጡት አስተያየት “ስህተት” እንደሆነ ነግሬያቸዋለሁ አሉ።

    ቫንስ የ18 ዓመቱ ብሪታኒያዊ ተማሪ ግድያ በ“ጅምላ ስደተኞች ወረራ” እንደተፈፀመ እና “ብቸኛው ምላሽ” “እውነተኛ ቁጣ” ነው ብለዋል።

    ዴቪድ ላሚ ለቢቢሲ ከጄዲ ቫንስ ጋር መነጋገራቸውን እና ለምክትል ፕሬዝዳንቱ ግድያው “ከጅምላ ስደት ጋር ምንም የሚያገናኘ የለም” ብለው እንደነገሯቸው ገልፀዋል።

    ተማሪውን በመግደል የተጠረጠረው ቪክረም ዲውጋ የዘረኝነት ጥቃት እንደደረሰበት እና ራሱን የመከላከል እርምጃ እንደወሰደ ተናግሯል።

    የብሪታኒያ ዜግነት ያለው ተጠርጣሪው የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበታል።

    ግድያዎ በተለይም በፖሊስ ጥበቃ እና የድምጽ አልባ መሣሪያ ሕግ ዙሪያ ከባድ ክርክር ያስነሳ ሲሆን፤ የተቃውሞ ሰልፎችን ቀስቅሷል።

    አርብ ዕለት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ በኤክስ ገፃቸው ላይ “አሳዛኝ” በማለት ታዳጊው ለስደተኞች ባይሆን ኖሮ በሕይወት ይቆይ ነበር ብለዋል።

    ምክትል ፕሬዝዳንቱ አውሮፓዊያን በስደተኞች ወረራ ጉዳይ ጠንከር ያለ እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው አመልክተዋል።

    ላሚ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ይህን የቫንስ አስተያየት በተመለከተ መነጋገራቸውን ገልፀዋል።

  3. የፓኪስታን አገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ለጠቅላይ መሪው ሞጅታባ ኻሜኒ የተላከ መልዕክት ይዘው ቴህራን ገቡ

    የኢራኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከፓኪስታኑ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሞህሲን ናቅቪ ጋር በቴህራን ተገናኝተው ተወያዩ።

    የፓኪስታኑ ከፍተኛ ባለሥልጣን ቴህራን የደረሱት ቅዳሜ ምሽት መሆኑ ተዘግቧል።

    እንደ ኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ከሆነ የፓኪስታን አገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ቴህራን የመጡት ከፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ለጠቅላይ መሪው ሞጅታባ ኻሜኒ የተላከ “መልዕክት” ለማድረስ ነው።

    የፓኪስታን ሚኒስትር ቴህራን የደረሱት በኢራን እና በአሜሪካ መካከል የሚካሄደው የሰላም ድርድር በተስተጓጎለበት ወቅት ነው።

    እንደ ታስኒም የዜና ወኪል ዘገባ ናቅቪ በርካታ የኢራን ባለሥልጣናትን አግኝተው ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    የፓኪስታን ምንጮች ለዓለም አቀፍ የዜና ወኪሎች ከሚኒስትሩ ጉዞ አስቀድሞ በቴህራን እና ዋሺንግተን መካከል ስላለ “አዲስ የሰላም ዕቅድ” ይወያያሉ ሲሉ ተናግረው ነበር።

    ምንጮቹ አክለውም አዲሱ ዕቅድ በሁለቱ አገራት መካከል የተስተጓጎለውን ድርድር ለማስቀጠል እና በሁለቱ ተደራዳሪ ወገኖች መካከል መግባባት እንዲፈጠር ለማድረግ መፍትሄ ያስቀምጣል ተብሏል።

    በኢራን እና አሜሪካ መካከል ጦርነት የካቲት 21 2018 ዓ.ም. ከተቀሰቀሰ ወዲህ ፓኪስታን አደራዳሪ በመሆን እየሰራች ነው።

  4. ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ፕሮግራሟ “በፍጹም ለድርድር” እንደማይቀርብ አስታወቀች

    የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ሰሜን ኮሪያን ከመጎብኘታቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ፒዮንግያንግ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ከማምረት ወደኋላ እንደማትል አስታወቀች።

    የሰሜን ኮሪያው መሪ እህት ኪም ዮ ጆንግ እሁድ ዕለት ለታተመው የአገሪቱ ጋዜጣ፣ ጎዶንግ ሲንሙን “በኒውክሌር ኃይል ላይ ያለን አቋም ፈጽሞ ለድርድር የማይቀርብ ነው” ብለዋል።

    ጆንግ በሰሜን ኮሪያ እንደ ቁልፍ የኮሙኑኬሽን እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ይታያሉ።

    አክለውም “አገራችን ራሷን ለመከላከል የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ፕሮግራሟን ለማጠናከር የወሰነችው ውሳኔ የመጨረሻ እና የማይቀለበስ ነው" ብለዋል።

    ሰሜን ኮሪያ የመጀመርያ የኒውክሌር ሙከራዋን ይፋ ያደረገችው እአአ በ2006 ሲሆን በ2023 ደግሞ በሕገ መንግሥቷ ላይ ራሷን እንደ ኒውኬሌር ኃያላን አገር አስቀምጣለች።

    በዚህ ሳምንት መጀመርያ ላይ ዩራኒየምን ጦር መሣሪያ ለማምረት በሚያስችል ደረጃ የሚያብላላ አዲስ ተቋም ይፋ አድርጋለች።

    ኪም ስፍራውን የጎበኙ ሲሆን የአገሪቱን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ብዛትት “በከፍተኛ ሁኔታ” የሚጨምር እንደሚሆን ተናግረዋል።

    ተንታኞች አዲሱ የኒውክሌር ተቋም ኪም እና ዢ በሚኖራቸው ድርድር ላይ አቅም ይፈጥራል ሲሉ ተናግረዋል።

    ኪም ሌላ የጦር መሣሪያ ማምረቻ ጎብኝተው የአገሪቱ የሚሳዔል ማምረት አቅም በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በእጥፍ እንዲያድግ ማዘዛቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

  5. ስታርመር ፓርቲያቸው የመሪዎች ምርጫ ለማድረግ ከወሰነ ተፎካካሪ ሆነው እንደሚቀርቡ ለደጋፊዎቻቸው ገለጹ

    የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ፓርቲያቸው ዳግም የመሪዎች ምርጫ የሚያደርግ ከሆነ ተፎካካሪ ሆነው እንደሚቀርቡ ለደጋፊዎቻቸው ገለጹ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና አጋሮቻቸው የመሪዎች ምርጫ የሚካሄድ ከሆነ ተፎካካሪ ሆነው እንደሚቀርቡ እየተናገሩ ቢሆንም ሌሎች ግን ምን ማድረግ እንዳለባቸው ለመወሰን አሁንም ገና ነው ሲሉ ጥርጣሬያቸውን ይገልጻሉ።

    የማንችስተር ከንቲባ የሆኑት አንዲ በርንሃም የመሪዎች ምርጫ የሚካሄድ ከሆነ ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።

    ሰር ኪር ስታርመር ግን የትኛውም የመሪዎች ምርጫ ቢካሄድ ተፎካካሪ ሆነው እንደሚቀርቡ ለደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሪዎች ምርጫ ዳግም የሚካሄድ ከሆነ አገሪቱን ወደ ቀውስ ውስጥ ይከታታል ብለው እንደሚያምኑ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

    ከሁለት ዓመት በፊት በከፍተኛ አብላጫ ድምጽ መመረጣቸውን በመግለጽም የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለመወጣት እየሰሩ መሆኑን ይናገራሉ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣናቸው እንዲለቅቁ ከሌሎች ጋር በመሆን እየጠየቁ የሚገኙት የጤና ሚኒስትሩ እና የማንችስተር ከንቲባ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ሌበር ፓርቲ ዳግም የመሪዎች ምርጫ ሊያካሄድ ይችላል የሚሉ አሉባልታዎች በመናፈስ ላይ ናቸው።

    በቀጣይ መሪ ላይ የሚኖረውን ሁኔታ ለመወሰን የሚቻለው እአአ በሰኔ 18 ከሚካሄደው የማሟያ ምርጫ በኋላ ነው። በዚህ ምርጫ የማንችስተሩ ከንቲባ አንዲ በርንሃም ሌበር ፓርቲን ለመምራት መወዳደር የሚፈልጉ ከሆነ ማሸነፍ ይኖርባቸዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ዳግም ለመፎካከር የሚወስኑ ከሆነ በሌበር አመራሮች መካከል ከፍተኛ ፉክክር ይፈጠራል።

    ባለፈው ወር በተካሄደው ምርጫ ሌበር ፓርቲ በከፍተኛ ሁኔታ ከተሸነፈ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣን እንዲነሱ የሚጠይቁ ፖለቲከኞች በርትተዋል።

  6. የአሜሪካው መከላከያ ሚኒስትር የአውሮፓ አገራትን በስደተኞች ጉዳይ ተቹ

    የአሜሪካው መከላከያ ሚኒስትር በፈረንሳይ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት መታሰቢያ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር የአውሮፓ አገራትን የስደተኞች ፖሊሲ ነቀፉ።

    ሚኒስትሩ በንግግራቸው አንዳንድ የአውሮፓ አገራት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች እንዲገቡ መፍቀዳቸውን ተችተው “ወረራ” ሲሉ ጠርተውታል።

    ሄግሴት ንግግር ያደረጉት ናዚዎች በርካታ የአውሮፓ አገራትን ከወረሩ በኋላ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተፋፍሞ እአአ በ1944 የኅብረቱ ኃይሎች ሰሜናዊ የፈረንሳይ የባሕር ዳርቻ የሆነችውን ኖርማንዲን የተቆጣጠሩበትን 82ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ላይ ነው።

    “የሚያሳዝነው፣ ዛሬ፣ የአውሮፓ የባሕር ዳርቻዎች በተለያዩ አደገኛ ርዕዮተ ዓለሞች ተወርሯል” ብለዋል።

    “የስፔን፣ ጣሊያን፣ ግሪክ እና ቡልጋሪያ የባሕር ዳርቻዎች ጀልባዎች እና ሰዎች ይመጣሉ። የአውሮፓ አገራት ለዚህ ወረራ የሆነ ነገር የሚያደርጉት መቼ ነው?”

    ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአውሮፓ ስደተኝነት ዋና የፖለቲካ አጀንዳ ሲሆን ጠንካራ የኢሚግሬሽን ፖሊሲ እንዲኖር የሚጠይቁ ፓርቲዎች ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኙ መምጣታቸውን የሕዝብ አስተያየት መሰብሰቢያዎች ያሳያሉ።

    ከፍተኛ የትራምፕ አስተዳዳር አባላት የአውሮፓ የስደተኞች ፖሊሲን ሲተቹ ሄግሴት የመጀመርያው አይደሉም።

    አርብ ዕለት የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ የ18 ዓመቱ ብሪታኒያዊ ተማሪ፣ ሄንሪ ኖዋክ ባለፈው ዓመት በሳውዝሃምፕተን በስለት ተወግቶ መሞቱን በማንሳት በቀጥታ የሚያያዘው ካለው “ከፍተኛ የስደተኞች ወረራ” ጋር ነው ካሉ በኋላ “ብቸኛው ምላሽ” ሊሆን የሚችለው “ተቀባይነት ያለው ቁጣ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

    የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የምክትል ፕሬዚዳንቱን ንግግር “ሰዎች በዲሞክሪያሲያችን ጣልቃ እየገቡ ነው” ሲል ተችቷል። አክሎም የኖዋክ ቤተሰብ “የልጃቸው ሞት ተጨማሪ መከፋፈል እንዲፈጠር ምክንያት አንዲሆን እንደማይፈልጉ ተናግረዋል”

    ሄንሪ ኖዋክን ወግቶ የገደለው ቪክረም ዲግዋ የተወለደው ብሪታኒያ ውስጥ መሆኑን አቃቤ ሕግ አረጋግጧል።

    በፈረንሳይ የሁለተኛው ዓለም ጦርነት መታሰቢያን አስመልክተው ንግግር ያደረጉት ፒት ሄግሴት አንዳንድ የአውሮፓ አገራት በከፍተኛ መስዋዕትነት የተገኘ ነጻነታቸውን “ተመቻችተው” በመቀመጥ “ነጻነት በነጻ እንደማይገኝ” ረስተውታል ብለዋል።

    “እዚህ ተዋግተው የወደቁት አርበኞች የአውሮፓን ነጻነት አስመልሰዋል” ያሉት ሄግሴት “ያ ነጻነት በቀጣይ አመራሮች እና የጦር ተዋጊዎች ካልተጠበቀ የተዋደቁለት ዓላማ ጊዜያዊ ይሆናል።”

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ዓመት በተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ ላይ የአውሮፓን የስደተኞች ፖሊሲን ተችተው አገራቱ “ቁጥጥር በሌለው ፍልሰት” የተነሳ “ወደ ሲኦል እየሄዱ ነው” ብለው ነበር።

  7. ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥን “ለነዳጅ እና ጋዝ ላኪዎች ሙሉ በሙሉ ለመዝጋት” ዛተች

    በኢራን እና በአሜሪካ መካከል የተኩስ ልውውጥ መደረጉን ተከትሎ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የሆርሙዝ ወሽመጥን “ለነዳጅ እና ጋዝ ላኪዎች ሙሉ በሙሉ ለመዝጋት” ዛተ።

    በባሕረ ሰላጤው አካባቢ ሁለቱ አገራት የተኩስ ልውውጥ ካደረጉ በኋላ እስላማዊ አብዮታዊ ዘቡ በሰጠው ማስጠንቀቂያ የሆርሙዝ ወሽመጥ ለነዳጅ እና ለጋዝ ላኪዎች ሙሉ በሙሉ ቢዘጋ “ኃላፊነቱን የምትወስደው አሜሪካ ናት” ብሏል።

    አሜሪካ “እኩይ ድርጊቷን ከቀጠለች” ለሚወስደው እርምጃ ኃላፊነቱን እንደምትወስድም አስታውቋል።

    የአሜሪካ ጦር ኢራን ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ የተኮሰቻቸውን አራት ድሮኖች መትቶ መጣሉን አስታውቋል።

    የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ፤ ጎሩክ እና ቃሽም በተባሉ ደሴቶች ላይ የኢራን የባሕር ዳርቻ ጥበቃ ማዕከላት ላይ ጥቃት መፈጸሙን ገልጿል።

    ኢራንም በአጸፋው በኩዌት የሚገኙ ሁለት የአሜሪካ ጦር መቀመጫዎች ላይ ባለስቲክ ሚሳዔል ተኩሳለች። በባሕሬን በሚገኘው የአሜሪካ ጦር ሰፈር ላይም ጥቃት ማድረሷ ተገልጿል።

    የባሕሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢራን ያደረሰችውን ጥቃት “በጽኑ” እንደሚያወግዝ አስታውቋል። በባሕሬን እንዲሁም በኩዌት ላይ የደረሰውን ጥቃት “ግልጽ ጸብ አጫሪነት” ብሎታል።

  8. ሩሲያ በዩክሬን የድሮን ጥቃት እንደተፈጸመባት ገለጸች

    ዩክሬን በሩሲያዋ ሴንት ፒተርስበርግ ከተማ ዙሪያ “ያልተጠበቀ ጥቃት” እንደፈጸመች ሞስኮ ገለጸች።

    ከተማዋ የምታስተናግደው ዓመታዊ የምጣኔ ሃብት ጉባኤ የመጨረሻው ቀን ላይ ጥቃቱ መፈጸሙን ሩሲያ አስታውቃለች።

    በሴንት ፒተርስበርግ ዙሪያ ከ140 በላይ ድሮኖች ተመትተው እንደወደቁ ከንቲባ አሌክሳንደር ድሮዝዶኮ ተናግረዋል።

    ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነዋሪዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።

    የሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም ከቮሎድሚር ዜሌንስኪ ጋር የመገናኘታቸው ጥቅም እንደማይታያቸው ገልጸዋል።

    ባለፈው ሳምንት የዩክሬኑ ፕሬዚደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ሁለቱ መሪዎች ፊት ለፊት ተገናኝተው እንዲመክሩ መጠየቃቸው ይታወሳል።

    ዜሌንስኪ ጦራቸው የሩሲያን ባሕር ኃይል ዒላማ እንዳደረገ እና ጥቃቱን የፈጸሙት ሞስኮ ላደረሰችው ጉዳት የአጸፋ ምላሽ ለመስጠት እንደሆነ ተናግረዋል።

    “የአገራችን ድሮኖች በሴንት ፒተርስበርግ 1,000 ኪሎሜትር ርቀት ሸፍነው የጠላት ባሕር ኃይልን ዒላማ አድርገዋል” ብለዋል።

  9. ባሕሬን ከኢራን የተሰነዘረባትን ጥቃት አወገዘች

    የባሕሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢራን ያደረሰችውን ጥቃት “በጽኑ” እንደሚያወግዝ አስታወቀ።

    በባሕሬን እንዲሁም በኩዌት ላይ የደረሰውን ጥቃት “ግልጽ ጸብ አጫሪነት” እንዲሁም “የሁለት አገራትን ሉዓላዊነት መጣስ” ሲል ኮንኗል።

    የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ፤ ጎሩክ እና ቃሽም በተባሉ ደሴቶች ላይ የኢራን የባሕር ዳርቻ ጥበቃ ማዕከላት ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በአጸፋው በኩዌት የሚገኙ ሁለት የአሜሪካ ጦር መቀመጫዎች ላይ ባለስቲክ ሚሳዔል እንደተኮሰ እና በባሕሬን በሚገኘው የአሜሪካ ጦር ሰፈር ላይም ጥቃት እንዳደረሰ አስታውቋል።

    የአሜሪካ ጦር የኢራንን አራት ድሮኖች መትቶ ከጣለ በኋላ ቴህራን ወደ ኩዌት እና ባሕሬን ሰባት ሚሳዔሎችን ማስወንጨፏን ገልጿል።

    ስድስቱን ሚሳዔሎች ማክሸፍ እንደተቻለ እና ሰባተኛው ዒላማውን እንዳልመታም አስታውቋል።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ባወጣው መግለጫ “በሕገ ወጥ መንገድ የአሜሪካን መመሪያ ተቀብለው በሆርሙዝ ወሽመጥ ሊያልፉ ሲሞክሩ አስቁመናል” ብሏል።

  10. የሰባት ወር ፍልስጤማዊ ጨቅላ በእስራኤል ጥቃት መገደሉ ተገለጸ

    በይዞታ ሥር ባለችው ዌስት ባንክ የሰባት ወር ፍልስጤማዊ ጨቅላ በእስራኤል ጥቃት መገደሉን የፍልስጤም የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

    በሄብሮን ከተማ፣ ታል ሩሚዳ አካባቢ ሳም ፋሐድ አቡ ሐኪል የተባለው ጨቅላ ወላጆችም ከእስራኤል በተተኮሰ ጥይት ጉዳት ደርሶባቸዋል።

    የእስራኤል መከላከያ ኃይል አርብ ዕለት ወታደሮቹ “ወደ እነሱ እየገሰገሰ የሚሄድ መኪና እንደተመለከቱ” ገልጾ ከወታደሮቹ አንደኛው “አንድ ጥይት ወደ ተሽከርካሪው በመተኮስ ምላሽ መስጠቱን” ገልጿል።

    “በዚህም ምክንያት ሦስት ፍልስጤማውያን ተጎድተው ወደ ሕክምና ተወስደዋል። ክስተቱ ላይ ምርመራ እየተደረገ ነው። የማይመለከታቸው ሰዎች በመጎዳታቸው ጥልቅ ሐዘን ተሰምቶናል” ሲልም ጦሩ አስታውቋል።

    ቤተሰቡ የእስራኤልን ወታደራዊ ተሽከርካሪ ከሩቅ ሲመለከት መኪናውን ማቆሙን የጨቅላው አያት መናገራቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    ከዚያም ወደ መኪናቸው ሲተኮስ ማስጠንቀቂያ እንደመሰላቸው አያትየው ተናግረዋል።

    “አንድ ጥይት የልጅ ልጄን መታው። ጥይቱ ጭንቅላቱን ሲመታው የልጄን ጉንጭም ጭሯት አልፏል” ብለዋል።

  11. አሜሪካ ለኢራን ብሔራዊ ቡድን ቪዛ መስጠቷን አስታወቀች

    ለዓለም ዋንጫ ላለፈው የኢራን ብሔራዊ ቡድን አሜሪካ ቪዛ መስጠቷን አስታወቀች።

    የኢራን የመጀመሪያ ጨዋታ ከኒው ዚላንድ ጋር በሎስ አንጀለስ ከተማ የሚካሄድ ይሆናል።

    የአሜሪካ ባለሥልጣናት “ለስፖርተኞቹ እንዲሁም ድጋፍ ለሚሰጧቸው የቡድን አባላት ቪዛ ሰጥተናል” ብለዋል።

    “የኢራን ብሔራዊ ቡድን ሥርዓቱን በመበዝበር አሸባሪዎችን ወደ አሜሪካ እንዲያስገባ አንፈቅድም” በማለትም አክለዋል።

    የኢራን እግር ኳስ ፌደሬሽን ስለ ቪዛው መሰጠት እስካሁን በይፋ ያለው ነገር የለም።

    በዓለም ዋንጫ ታሪክ አስተናጋጅ አገር ጦርነት ውስጥ የገባችበትን አገር ብሔራዊ ቡድን ስትቀበል የመጀመሪያው ይሆናል።

  12. አሜሪካ እና ኢራን በባሕረ ሰላጤው አካባቢ የተኩስ ልውውጥ አደረጉ

    የአሜሪካ ጦር ኢራን ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ የተኮሰቻቸውን አራት ድሮኖች መትቶ መጣሉን አስታወቀ።

    “አንድ ጊዜ ብቻ ጥቃት የሚያደርሱት ድሮኖች በባሕር እንቅስቃሴ ላይ አደጋ ጥለዋል” ሲል ጦሩ ገልጿል።

    የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ፤ ጎሩክ እና ቃሽም በተባሉ ደሴቶች ላይ የኢራን የባሕር ዳርቻ ጥበቃ ማዕከላት ላይ ጥቃት መፈጸሙን ጠቅሷል።

    ኢራንም በአጸፋው በኩዌት የሚገኙ ሁለት የአሜሪካ ጦር መቀመጫዎች ላይ ባለስቲክ ሚሳዔል ተኩሳለች። በባሕሬን በሚገኘው የአሜሪካ ጦር ሰፈር ላይም ጥቃት ማድረሷን የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ እንዳለው ከባሕረ ሰላጤው አገራት ላይ ኢራን ከተኮሰቻቸው ሰባት ሚሳዔሎች ስድስቱ ዒላማቸውን ሳይመቱ ማክሸፍ ተችሏል።

    በተደጋጋሚ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት የኢራን እና የአሜሪካ የተኩስ አቁም ስምምነት አደጋ ውስጥ ወድቋል።

    ከቀናት በፊትም ተመሳሳይ የተኩስ ልውውጥ ተደርጎ እንደነበር ይታወሳል።

    ኢራን በኩዌት ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በፈጸመችው የድሮን ጥቃት አንድ ሰው ሲገደል፤ 60 ሰዎች ቆስለዋል።

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በአውሮፕላን ማረፊያው ጥቃት መፈጸሙን አስተባብሏል። ጉዳት የደረሰው በተሳሳተ የአሜሪካ ሚሳዔል አምካኝ ምክንያት መሆኑንም ገልጿል።

  13. በሞቃዲሾ ለሁለት ቀናት የቆየው ግጭት ጋብ ማለቱ ተዘገበ

    የመንግሥት ወደታሮች እና የተቃዋሚ ፖለቲከኞች ደጋፊ ሚሊሻዎች ሞቃዲሾ ውስጥ ለሁለት ቀናት ከተጋጩ በኋላ የሶማሊያ የፀጥታ ኃይሎች ችግሩን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን የአገሪቱ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ገለጸ።

    "የተቃዋሚ ቡድን ሚሊሻዎች ትጥቅ ፈትተው ከነበሩባቸው ቦታዎች እንዲወጡ ተደርገዋል።” ያለው ሚኒስቴሩ ግጭቱን ፈርተው የሸሹ ነዋሪዎች ወደ መደበኛ ኑሯቸው ተመልሰዋል ብሏል።

    ነገር ግን ነዋሪዎች ሚሊሻዎች ትጥቃቸውን አለመፍታታቸውን እና ግጭቱም የቆመው በጎሳ መሪዎች በተደረገ የሽምግልና ጥረት መሆኑን ለሮይተርስ ተናግረዋል።

    ግጭቱ የተቀሰቀሰው የሥልጣን ጊዜያቸው ካበቃ በኋላ ቦታቸውን ያላስረከቡትን ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድን የሚቃወም ሰልፍ ለማካሄድ የተያዘው ዕቅድ ከመተግበሩ በፊት ነው።

    ባለፈው መጋቢት ወር የአገሪቱ ፓርላማ የፕሬዝዳንቱን የሥልጣን ቆይታ በአንድ ዓመት የሚያራዝመውን ሕገ-መንግሥታዊ ለውጥ በመደገፍ የምርጫ ጊዜውን በአንድ ዓመት ገፍቶታል።

    ሐሙስ ዕለት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሻሪፍ ሼክ አህመድ የመንግሥት ኃይሎች ቤታቸውን ዒላማ ማድረጋቸውን እና መንግሥት “በሕገ- ወጥነት ሕገ መንግሥቱን አሻሽሏል” ሲሉ ከስሰዋል።

    የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሐሳን አሊ ካሂር በተመሳሳይ የመንግሥት ወታደሮች ፀረ ታንክ መሳሪያ እና ድሮኖችን ጨምሮ ከባድ መሳሪያዎችን ሕዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች ላይ ተጠቅመዋል ሲሉ ክስ አሰምተዋል።

    የማስታወቂያ ሚኒስቴር ግን ሁለቱን የቀድሞ ባለሥልጣናት ታጣቂዎቻቸውን ወደ መኖሪያ አካባቢዎች በማሰማራት እና ፖሊሶችን እንዲያጠቁ በማድረግ የሰላማዊውን ሕዝብ ሕይወት ለአደጋ አጋልጠዋል ሲል ወቅሷል።

    የተባበሩት መንግሥታት፣ የአፍሪካ ኅብረት እና የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ማኅበር በግጭቱ ውስጥ የሚሳተፉ ወገኖች አለመግባባታቸውን በንግግር እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል።

  14. በመካከለኛው ምሥራቅ የሚካሄደው ጦርነት ሚሊዮኖችን ለረሃብ አደጋ ማጋለጡ ተነገረ

    በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ ያለው ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተጨማሪ ሰዎችን ለረሃብ አደጋ እንዳጋለጠ የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ገለጸ።

    ድርጅቱ እንዳለው እየጨመረ ያለው የነዳጅ እና የትራንስፖርት ዋጋ በአንድ በኩል ምግብን ውድ ሲያደርግ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የገንዘብ እጥረት ድርጅቱ የሚያቀርበውን የምግብ እርዳታ እንዲቀንስ አስገድዶታል።

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ውስጥ ቀጣናዊ ጦርነት ከመቀስቀሱ በተጨማሪ ወደ ሊባኖስ ተስፋፍቶ ሆርሙዝ ወሽመጥን ጨምሮ በወሳኝ የባሕር ማጓጓዣ መስመሮች በመዘጋታቸው እንቅስቃሴ ላይ መስተጓጎል ፈጥሯል።

    ይህ ሁኔታም የጭነት መርከቦች የጉዞ መስመሮቻቸውን እንዲቀይሩ በማድረግ የዓለም አቀፍ የነዳጅ እና የጋዝ አቅርቦት ሰንሰለትን አደናቅፏል።

    በአፍጋኒስታን፣ በሶማሊያ እና በሲሪ ላንካ ያሉ ቤተሰቦች ክፉኛ ከተጎዱት መካከል ሲሆኑ፣ በነዳጅ እና በምግብ ዋጋ መናር እንዲሁም በገቢ ማሽቆልቆል እና በንግድ እንቅስቃሴ መቋረጥ ምክንያት ከፍተኛ ጫና እየደረሰባቸው መሆኑ ተገልጿል።

    የዓለም ምግብ ፕሮግራም እንደሚለው ባለንበት የአውሮፓውያን ዓመት 6.5 ሶማሊያውያን ወይም አንድ ሦስተኛ የሚሆነው የአገሪቱ ሕዝብ ከባድ የረሃብ አደጋ ይገጥመዋል።

    በአፍጋኒስታን ደግሞ 17.4 ሚሊዮን ሕዝብ የምግብ እጥረት ችግር ገጥሞታል።

    መስተጓጎሉ የሚቀጥል ከሆነ ሁኔታው ወደ ከፋ ደረጃ ከፍ በማለት በሶማሊያ እና በአፍጋኒስታን ተጨማሪ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ከባድ የምግብ እጥረት እና ረሃብ እንደሚያጋጥማቸው ድርጅቱ አስጠንቅቋል።

    ሁለቱም አገራት ከውጭ በሚገቡ የኃይል አቅርቦት እና የምግብ ምርት ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ጥገኛ ናቸው።

  15. የሰሀራ በረሃን ሲያቋርጡ ከነበሩ ተጓዦች መካከል ቢያንስ 50 ሰዎች በውሃ ጥም ሞቱ

    በሰሀራ በረሃ ውስጥ እየተጓዙ ሳሉ መኪናቸው የተበላሸባቸው ቢያንስ 50 ሰዎች በውሃ ጥም መሞታቸው ተዘገበ።

    ተጓዦቹ በማሊ የሙስሊሞች ፌስቲቫል ላይ ታድመው እየተመለሱ ነበር።

    መንገደኞቹ በኒጀር እና በአልጄሪያ መካከል ከምትገኘው ቁልፍ ሥፍራ አሳማካ በ80 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ሳሉ ውሃ እንዳለቀባቸው ተገልጿል።

    የአግዴዝ አገረ ገዢ ባወጡት መግለጫ “በጣም ሞቃታማ በሆነው ቦታ መንቀሳቀስ የማይችሉበት ሁኔታ ገጠማቸው። የሚያስፈልጋቸውን ግብዓት ስላላገኙ በሕይወት መቆየት ከባድ ነው” ብለዋል።

    አብረው በመጓዝ ላይ ከነበሩት መካከል ሁለቱ ብቻ ተርፈዋል።

    መኪናቸው ከማሊዋ ቴለሀንደክ ከተማ ከተነሳ በኋላ መንገዱን እንደሳተ ተገልጿል።

    ለቀናት ያህል አሽከርካሪው እና ተሳፋሪዎች መኪናውን ለመጠገን ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም።

    “መኪናውን መሥራት አልቻሉም፤ ውሃም አልቆባቸው ነበር። በከባድ ሙቀት ውስጥ ታፍነው ነበር። መኪናው አጠገብ ብዙ አስከሬኖች ተገኝተዋል” ይላል መግለጫው።

    ሟቾቹ በጅምላ መቃብር ውስጥ ተቀብረዋል።

    መኪናው ከተበላሸበት ሥፍራ በቅርብ ርቀትም ሌላ 60 ሰዎች የጫነ ተሽከርካሪ ብልሽት ገጥሞት ተገኝቷል። ተሳፋሪዎች መኪናውን ለመሥራት ለሦስት ቀናት ሞክረው አልተሳካላቸውም።

  16. ኢራን ከአሜሪካ ጋር መግባባት እንደተደረሰ የታገደባት ግማሽ ሀብቷ እንዲለቀቅ ጠየቀች

    ኢራን ከአሜሪካ ጋር ያደረገችው ድርድር መግባባት ላይ ሲደርስ በመጀመሪያው ደረጃ ላይ ከታገደባት ሀብት ግማሽ ያህሉ እንዲለቀቅ መጠየቋ ተነገረ።

    የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካዜም ጋሪባባዲ እና የአገራቸው ተደራዳሪ ቡድን አባላት እንዳሉት ከአሜሪካ ጋር “የመግባቢያ ስምምነት እንደተፈረመ ወዲያውኑ ከታገደባት 50 በመቶው ሀብት እንዲለቀቅላት የኢራን እስላማዊ ረፐብሊክ ጠይቃለች” ሲሉ የአገራቸውን ፍላጎት ማቅረባቸውን አመለክተዋል።

    መጀመሪያ ግማሹ ሀብት ከተለቀቀ በኋላ “ቀሪው በተወሰነ ጊዜው ውስጥ፤ በእኛ ግምት ከአንድ ወይም ከሁለት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ እንዲለቀቅ” እንደሚፈልጉ መጠየቃቸውን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መህር ለተባለው የኢራን ዜና አገልግሎት ተናግረዋል።

    ባለሥልጣኑ ጨምረውም የታገደውን የኢራን ሀብት ማስለቀቅ ከአሜሪካ ጋር በሚደረገው ድርድር ላይ ወሳኝ እና ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ “ምን ያህሉ ገንዘብ መጀመሪያ ላይ እንደሚለቀቅ እና ቀሪው በምን ያህል ጊዜ እንደሚለቀቅ በድርድር የሚወሰን ነው” ብለዋል።

    አሜሪካ ግን ሊደረስ በሚችለው ስምምነት የመጀመሪያ ደረጃ ላይ ምንም ዓይነት ገንዘብ ለኢራን እንደማይለቀቅ ከዚህ ቀደም አስታውቃለች።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም "ከኢራን ጋር ስምምነት የሚደረስ ከሆነ፣ ባራክ ኦባማ እንዳደረገው የኒውክሌር ስምምነት ተፈርሞ ለኢራን ክምር ገንዘብ የሚያስገኝ ሳይሆን ጥሩ ስምምነት ነው የሚሆነው” በማለት ኢራን የታገደባትን ሀብቷን በምትፈልገው መጠን የማግኘት ፍላጎቷን ጥያቄ ውስጥ አስገብተውታል።

  17. ሄዝቦላህ የተኩስ አቁሙን አልቀበልም ማለቱን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ጨመረ

    ሊባኖስ እና እስራኤል የደረሱበትን የሰላም ስምምነት ሄዝቦላህ እንደማይቀበል ማስታወቁን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አሳየ።

    የዛሬው የዋጋ ንረት የታየው የኦማን ነዳጅ መጫኛ አካባቢ ፍንዳታ በመነሳቱ የነዳጅ ጭነት ከመቋረጡ ጋር በተያያዘም ጭምር ነው።

    እስራኤል እና ሊባኖስ ከዚህ ቀደም የደረሱበትን የተኩስ አቁም ስምምነት እንደሚያድሱ ከማስታወቃቸው በተጨማሪ በሊባኖስ ውስጥ የሄዝቦላህ እንቅስቃሴ የሚገደብበት የደኅንነት ቀጣና ለመፍጠርም ተስማምተዋል።

    ሄዝቦላህ ግን ስምምነቱን “ለሊባኖስ አሳፋሪ እና እርባና ቢስ” በሚል እንደማይቀበለው አስታውቋል።

    የሄዝቦላህ መሪ “ሄዝቦላህ ተኩስ አቁሞ ተዋጊዎቹን ከደቡብ ሊባኖስ የሚያስወጣበት ስምምነት የመሸነፍ ያህል ነው፤ የእስራኤልንም ዓላማ ያሳካል” ማለታቸውም ተዘግቧል።

  18. እስራኤል ጋዛ ውስጥ በርካታ የሐማስ የደኅንነት ባለሥልጣናትን መግደሏን አስታወቀች

    የእስራኤል ጦር ሠራዊት እና የአገር ውስጥ ደኅንነት ተቋም የሆነው ሺን ቤት በጋዛ ሰርጥ ውስጥ ሌሊቱን በተካሄዱ ዘመቻዎች የሐማስ “ጠቅላላ የደኅንነት አገልግሎት” የሚባለው ኃይል በርካታ ከፍተኛ አመራሮች መገደላቸውን አስታወቁ።

    “የጋዛ ጠቅላላ ደኅንነት አገልግሎት” የሚባለው ኃይል በሐማስ ውስጥ ያለ ምሥጢራዊ ቡድን ሲሆን ኃላፊነቱም የሐማስን መሪዎች መጠበቅ እና ድጋፍ መስጠት መሆኑን እስራኤል ገልጻለች።

    የዚህ ኃይል ዋነኛ ኃላፊነቶች በሐማስ መሪዎች መካከል ግንኙነት እና ቅንጅት እንዲኖር ማድረግ፣ ጥበቃ ማድረግ እና ደኅንነቱ ወደተጠበቀ ቦታ ማጓጓዝ፣ መረጃ ማሰባሰብ እንዲሁም የሐማስ መሪዎች ለሚሰጡት ውሳኔ የደኅንነት መረጃ መስጠትም ይካተቱበታል።

    ከእስራኤል ጦር እና ከደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ሺን ቤት የወጣው መግለጫ እንዳመለከተው የጠቅላላ ደኅንነት ቡድኑ ምክትል አዛዥ የሆነው ሐሳን ራባህ ሐሳን ላባዳ በተፈጸሙት ጥቃቶች ተገድሏል።

    በተጨማሪም አሲም አሚን ሻላሽ ሻቢር፣ አብዱላህ አታ ዩኒስ አቡ ኩሉብ እና ሞሐማድ ኖማን ዛኪ አቡ ማርቅ በጥቃቶቹ ተገድለዋል ከተባሉት የቡድኑ ባለሥልጣናት መካከል መሆናቸው ተገልጿል።

    ከዚህ በፊት በተካሄደው ጦርነት ወቅት እና ከዚያም በኋላ በርካታ ከፍተኛ አመራሮቹ በእስራኤል ኢላማ ተደርገው የተገደሉበት ሐማስ አሁን የእስራኤል ጦር እና የደኅንነት ተቋም ከፍተኛ አመራሮቹን ስለመግደላቸው ስላወጡት መግለጫ እስካሁን ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ አልሰጠም።

  19. ሄዝቦላህ የእስራኤል እና ሊባኖስን የተኩስ አቁም ስምምነት እንደማይቀበል አስታወቀ

    በአሜሪካ አሸማጋይነት ሊባኖስ እና እስራኤል የደረሱበትን የተኩስ አቁም ስምምነት እንደማይቀበል ሄዝቦላህ አስታወቀ።

    ሄዝቦላህ ባወጣው ጠንካራ ይዘት ያለው መግለጫ ላይ መሪው ናይም ቃሲም “ድርድሮች ለሊባኖስ አሳፋሪ እና ውጤት አልባ ሆነዋል” ብለዋል።

    ስምምነቱን “በሊባኖች ሕዝብ ስም” እንደማይቀበለውም ታጣቂ ቡድኑ አስታውቋል።

    እስራኤል እና ሊባኖስ ከዚህ ቀደም የደረሱበትን የተኩስ አቁም ስምምነት እንደሚያድሱ አስታውቀዋል። በሊባኖስ ውስጥ የሄዝቦላህ እንቅስቃሴ የሚገደብበት የደኅንነት ቀጣና ለመፍጠርም ተስማምተዋል።

    የእስራኤል እና ሊባኖስ ስምምነት ሄዝቦላህ እስራኤል ላይ ጥቃት እንዳይፈጽም የሚያግድ ነው።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሄዝቦላህ እና ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር መወያየታቸውን ጠቅሰው፤ የተወሰነ መሻሻል መስተዋሉን አስታውቀዋል።

    “ሊባኖስ ሰላም ብታገኝ መልካም ነው። ለዓመታት ጥቃት ሲደርስባት ነበር። ጥቃቱ ቢገታ ጥሩ ይሆናል” ሲሉም ተናግረዋል።

    ትራምፕ ይህንን ከማለታቸው በፊት በውይይቱ ያልተሳተፉ የሄዝቦላህ መሪ “ሄዝቦላህ ተኩስ አቁሞ ተዋጊዎቹን ከደቡብ ሊባኖስ የሚያስወጣበት ስምምነት የመሸነፍ ያህል ነው፤ የእስራኤልንም ዓላማ ያሳካል” ብለዋል።

    የሄዝቦላህ ጠንካራ ይዞታ በሆነው የቤሩት ደቡባዊ ክፍል የተስተዋለውም ተመሳሳይ ስሜት ነው።

    ቢቢሲ ካነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች አንዱ የሆነው ሳሚ “ይሄ የሰላም ስምምነት ሳይሆን መረታት ነው” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

  20. ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን ላይ ጦርነት የማካሄድ ሥልጣናቸው በምክር ቤት በመገደቡ ቁጣቸውን ገለጹ

    የአሜሪካ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በኢራን ላይ ጦርነት የማካሄድ ሥልጣናቸውን የሚገድብ ውሳኔ በማሳለፉቸው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የምክር ቤቱን አባላት አጥብቀው ተቹ።

    ፕሬዝዳንቱ ከኢራን ጋር የሚደረገውን ጦርነት ለማብቃት የሚያስችለው ድርድር “ከመጨረሻ ደረጃ” ላይ በደረሰበት ጊዜ የአሜሪካ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጦርነት በማካሄድ ሥልጣናቸው ላይ ገደብ መጣሉን “አገር ወዳድነት አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በትሩዝ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ውሳኔውን በተመለከተ ባሰፈሩት ጽሁፍ ተቀናቃኞቸቻውን ዲሞክራቶች እና እነሱን ደግፈው ድምጽ የሰጡ የፓርቲያቸው ሪፐብሊካን የምክር ቤት አባላትን ወቅሰዋል።

    ". . .ከኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ጋር የሚደረገውን ጦርነት ለማብቃት በመጨረሻው ድርድር መካከል ላይ እያለሁ አራት የሪፐብሊካን እና ሁሉም የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላት የምክር ቤት እንደራሴዎች ጦርነት የማካሄድ ሥልጣኔን የሚገድብ ትርጉም የለሽ ውሳኔ አሳልፈዋል” ብለዋል።

    "ድርድሩ ከምን ደረጃ ላይ እንዳለ እያወቁ እንዴት እንዲህ ያለ ከአርበኝነት የራቀ ውሳኔ ይሰጣሉ?” ሲሉ በተወካዮች ምክር ቤት አባላቱ ውሳኔ ደስተኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።

    ከዚህ ቀደም ብዙም ባልታየ ሁኔታ የአሜሪካ ምር ቤት ረቡዕ ዕለት የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላት ያቀረቡትን ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን ላይ የሚያካሂዱትን ጦርነት የሚገድብ የውሳኔ ሀሳብ በመደገፍ ድምጽ ሰጥተዋል።

    ይህ ውሳኔ በምክር ቤቱ ውስጥ ካሉ ዲሞክራቶች የ211 አባላት ድጋፍ ያገኘ ሲሆን፣ አራት የትራምፕ ፓርቲ አባላትም ደፈግወውት በ215 ለ208 በሆነ የድምጽ ብልጫ ነው ተቀባይነት ያገኘው።

    የኢራን ጦርነት ከተጀመረ በኋላ የትራምፕን ጦርነት የማካሄድ ሥልጣን ለመገደብ በተደጋጋሚ ድምጽ ቢሰጥም ተቀባይነት ሳያገን ቀርቶ ነበር። አሁን ግን አብዛኞቹ ሪፐብሊካኖች ውሳኔውን ቢቃወሙትም በአብላጭ ድምጽ አልፏል።