የአሜሪካ ምክር ቤት ትራምፕ በኢራን ጦርነት ላይ ያላቸውን ሥልጣን የሚገድብ ውሳኔ አሳለፈ

በዋሽንግተን የሚገኘው የአሜሪካ ካፒቶል ሕንፃ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ላይ ተጨማሪ ጥቃት እንዳይፈፅሙ የሚያደርግ ውሳኔ አሳለፈ።

ውሳኔውን ያሳለፉት 215 ለ 208 በሆነ ድምጽ ሲሆን አራት ሪፐብሊካኖች ባለፈው የካቲት ወር ላይ የጀመረውን ጦርነት በመቃወም ዲሞክራቶችን ተቀላቅለዋል።

ይህ በኮንግረሱ ፈቃድ አልተሰጠውም በሚል ትችት ሲቀርብበት የነበረውን የትራምፕን ሥልጣን ለመገደብ በምክር ቤቱ የተደረገ አራተኛው ሙከራ ነው።

አሁንም ግን ምክር ቤቱ ያሳለፈው ውሳኔ ሪፐብሊካኖች በሚቆጣጠሩት የአሜሪካ ሴኔት ይሁንታን ማግኘት አለበት።

ሴኔቱ ሊያፀድቀው ቢችልም እንኳን ውሳኔው በኢራን ላይ እየተወሰደ ያለውን ወታደራዊ እርምጃ ያስቆማል ተብሎ አይታሰብም።

ሴኔቱ ቀደም ብሎ ካደረጋቸው ያልተሳኩ ሰባት ሙከራዎች በኋላ ግንቦት ወር ላይ ተመሳሳይ የውሳኔ ሃሳብ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ሙሉ ድምጽ ማግኘት አልቻለም።

ረቡዕ ዕለት የምክር ቤቱ አባላት የሰጡት ድምጽ በትራምፕ ሪፐብሊካን ፓርቲ ውስጥ መከፋፋል እንዳለ ያሳየ ነበር።

የሪፐብሊካን ተወካይ የሆኑት ቶማስ ማሴ፣ ብሪያን ፊትዝፓትሪክ፣ ቶም ባሬት እና ዋረን ዴቪድሰን ረቡዕ ዕለት የተላለፈውን ውሳኔ እና ዲሞክራቶች ያቀረቡትን ሃሳብ ተቀላቅለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ድምፅ የሰጡት ዲሞክራቱ ጃረድ ጎልደን ኦፍ ሜን አሁንም ድጋፋቸውን አሳይተዋል።

በሚችጋን የሪፐብሊካን ተወካይ የሆኑት ባሬት " ኮንግረንሱ ብቻውን ጦርነት አውጇል። ይህ ልንጠብቀው የሚገባ ጉዳይ ነው" ብለዋል። ከትራምፕ ስለሚመጣባቸው አፀፋ ያሳስባቸው እንደሆነ ተጠየቁት የምክር ቤት አባሉ " ትክክል ነው ብዬ ለማስበው ነገር ነው ድምጽ የሰጠሁት። የሚመጣውን ለመቀበል ፈቃደኛ ነኝ" ሲሉም ምላሽ ሰጥተዋል።

በምክር ቤቱ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴን የሚመሩት ዲሞክራቱ ግሪጎሪ ሚክስ በበኩላቸው የድምጽ አሰጣጡን " ገለልተኛ የሆነ እና ትራምፕ በኢራን ላይ እያካሄዱት ያለውን ሕገወጥ እና ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል ጦርነት የሚቃወም እንዲሁም ጦርነቱን ለአንደኛ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም የተወሰደ የመጀመሪያው እርምጃ ነው" ብለዋል።

አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የካቲት መገበዳጃ ላይ ነበር ጥቃት የከፈቱት።

ኢራንም በእስራኤል እና በባሕረ ሰላጤው በሚገኙ የአሜሪካ አጋር አገራት ላይ ጥቃት በመፈፀም እና የዓለም አብዛኛው ነዳጅ መተላለፊያ የሆነውን የሆርሙዝ ወሽመጥን በመዝጋት ምላሽ ሰጥታለች።

ሚያዚያ ወር ላይ አሜሪካ ወደ ኢራን የሚሄዱ እና ከኢራን የሚነሱ መርከቦች እንዳይንቀሳቀሱ እገዳ እንደምትጥል አስታውቃ ነበር።

በዚያው ወር ሁለቱ አገራት የተኩስ አቁም ለማድረግ የመጀመሪያ ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር።

ስምምነት ላይ ቢደርሱም አሜሪካ ከሰሞኑ በኢራን ላይ ጥቃት ፈፅማለች። ቴህራንም በምላሹ የአሜሪካ አጋር በሆነችው በኩዌት ላይ ጥቃት በመፈፀም አጸፋ ሰጥታለች።

የአሜሪካ ምክር ቤት ድምጽ ከመስጠቱ ቀደም ብሎም ትራምፕ ጦርነቱን ለማስቆም የሚደረገው ድርድር " በጥሩ ሁኔታ" እየሄደ እንደሆነ እና በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ተናግረዋል።

ፕሬዚደንቱ ጨምረውም አብዛኞቹ የአስተዳደራቸው አባላት " ሁሉም ሰው ሳያልቅ" ግጭቱን በቅርቡ ለማቆም ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።