የትግራይ ኃይሎች ከፍተኛ አዛዥ ሜጀር ጄነራል ዮሐንስ "እጅ መስጠታቸው" ተነገረ

ሜጀር ጄነራል ዮሐንስ ወልደጊዮርጊስ
የምስሉ መግለጫ, ሜጀር ጄነራል ዮሐንስ ወልደጊዮርጊስ (ጆን መዲድ)
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የቀድሞው የፌደራል መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንን እና የትግራይ ኃይሎች ደቡባዊ ግንባር አዛዥ የሆኑት ሜጀር ጄነራል ዮሐንስ ወልደጊዮርጊስ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና በአጋሩ የትግራይ የሰላም ኃይሎች "መያዛቸውን" ሁለት ለኢትዮጵያ ሠራዊት ቅርብ የሆኑ ምንጮች ለቢቢሲ ትግርኛ አረጋገጡ።

ይሁን እንጂ ይህንን በተመለከተ ከመንግሥት በኩል እስካሁን ይፋዊ መግለጫ አልተሰጠም።

ከህወሓት በኩልም ሆነ ከጄነራሉ ቅርብ ሰዎች የተባለ ነገር የለም። ሆኖም የመንግሥት ደጋፊ የሆኑ አክቲቪስቶች ሜጀር ጄነራል ዮሐንስ "እጅ ሰጥተዋል" የሚል መረጃ በማኅበራዊ ሚዲያ ሲያጋሩ ነው።

"ጆን መዲድ" በሚል ቅጽል ስም የሚታወቁት ሜጀር ጄነራል ዮሐንስ፣ በትግራይ ኃይሎች ወታደራዊ መዋቅር ውስጥ ከሚገኙ ከፍተኛ የጦር አመራሮች መካከል አንዱ ነበሩ።

ምንጮቹ እንደሚሉት፣ ጄነራሉ በሰሜን ትግራይ ማዕከላዊ ዞን ውስጥ በሚገኘው ራማ ወረዳ ከኤርትራ ድንበር አቅራቢያ ሰኞ ዕለት በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና በትግራይ የሰላም ኃይሎች ከተከበቡ በኋላ ነው በቁጥጥር ሥር የዋሉት።

ሜጀር ጄነራል ዮሐንስ በተያዙበት ጊዜ የደኅንነት ጠባቂዎቻቸው፣ የኮሎኔል ማዕረግ ያላቸው ሰባት አዛዦች እና ሌሎች በርካታ መኮንኖች ከእርሳቸው ጋር እንደነበሩ ተነግሯል።

ከምንጮቹ አንዱ ለቢቢሲ እንደገለጸው፣ ሜጀር ጄነራል ዮሐንስ በመከላከያ ሠራዊት ከተያዙ በኋላ ከራማ አካባቢ ተወስደው በአሁኑ ወቅት በዓድዋ ከተማ ይገኛሉ።

ሜጀር ጄነራል ዮሐንስ በቀደሞው የትግራይ ጦርነት ወቅት በተመሠረተው ትግራይ ኃይሎች ውስጥ ማዕከላዊ ዕዝ እና በወታደራዊ ኮማንድ ካውንስል ውስጥ አባል ነበሩ።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጄነራሉ ከ2013 ዓ. ም. ጀምሮ በተካሄደው ጦርነት መጀመሪያ ላይ የህወሓት ኃይሎች ያጋጠማቸውን ውድቀት ተከትሎ የትግራይ ኃይሎችን እንደገና በማደራጀት እና በማሰባሰብ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል ተብለው ከሚታመኑት ወታደራዊ መኮንኖች መካከል አንዱ እንደሆኑ ይታመናል።

በፌዴራል መንግሥት እና በህወሓት መሪዎች መካከል ያለው ፖለቲካዊ አለመግባባት ከመከሰቱ በፊት፣ ሜጀር ጄነራል ዮሐንስ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ውስጥ በከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ ላይ የነበሩ ሲሆን፤ የሠራዊቱ የምዕራብ ዕዝ አዛዥም ነበሩ።

በትግራይ የተካሄደው የሁለት ዓመት ደም አፋሳሽ ጦርነት ካበቃ በኋላ ባለፉት ዓመታት ሜጀር ጄነራል ዮሐንስ ከወታደራዊ ሚናቸው በተጨማሪ በህወሓት ፖለቲካ ውስጥም ጉልህ ሰው ሆነው ታይተዋል።

በህወሓት ውስጥ መከፋፈል ሲፈጠር ከሊቀ መንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ወገን የተሰለፉት ጄነራሉ የቀድሞው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመሩትን አስተዳደር ከተቃወሙ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች መካከል አንዱ ነበሩ።

በህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረው መከፋፈል እየተባባሰ በሄደበት ጊዜም በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ላይ በመቅረብ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው አስተያየቶችን በመስጠት ይታወቃሉ።

ይህ የሜጀር ጄነራል ዮሐንስ "እጅ መስጠት" የተሰማው በትግራይ ውስጥ ያለው ወታደራዊ ሁኔታ በፍጥነት እየተቀየረ ባለበት ወቅት ነው።

መስከረም አጋማሽ ላይ በደቡባዊ ትግራይ፣ በትግራይ ኃይሎች እና በፌደራሉ ሠራዊት መካከል ውጊያ ከተቀሰቀሰ በኋላ የትግራይ ኃይሎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ኤርትራ ድንበር አካባቢዎች እንዲያፈገፍጉ ተደርገዋል ተብሏል።

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና አጋሩ የትግራይ የሰላም ኃይሎች መቀለን ጨምሮ የክልሉን አብዛኛውን ክፍል ተቆጣጥረዋል።