በዓለም ዙሪያ መርዛማ ኬሚካልን የሸጠው ግለሰብ ራስን ለማጥፋት እገዛ ማድረጉን አመነ

ተከሳሹ ኬነት ሎው

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የምስሉ መግለጫ, ኬነት ሎው በኦንታሪዮ ካናዳ ፍርድ ቤት ቀርቧል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በካናዳ አንድ ግለሰብ በኦንላይን መርዛማ ንጥረ ነገሮችን በመሸጥ በቀረቡበት 14 የራስን ማጥፋት እገዛ ክሶች ጥፋተኛ መሆኑን አመነ።

ኬነት ሎው የተባለ የ60 ዓመት ግለሰብ አርብ ዕለት በኦንታሪዮ ፍርድ ቤት የቀረበበትን ክስ ከአቃቤ ሕግ ጋር በገባው ስምምነት መሠረት ጥፋተኝነቱን አምኗል።

በስምምነቱ መሠረት አቃቤ ሕግ አስቀድሞ ያቀረበውን ከባድ የግድያ ክሶች አንስቷል።

የአገሪቱ ባለሥልጣናት እንዳሉት የቀድሞው የምግብ ባለሙያ በመርዝ የተሞሉ 1,200 ያህል ጥቅሎችን ስለ ራስ ማጥፋት በሚወራባቸው የድረ ገፅ መድረኮች ላገኛቸው የ40 አገራት ተጠቃሚዎች ሸጧል።

ክሶቹ ግን በካናዳ የተጎዱ ሰዎችን የሚመለከቱ ቢሆንም፤ የብሪታንያ የተጎጂ ቤተሰቦች የዩናይትድ ኪንግደም ባለሥልጣናት ሎውን ከ79 የብሪታንያውያን ሞት ጋር የተያያዘ ክስ አልመሰረቱም በማለት ክፉኛ ተችተዋል።

ሞቶቹ ኬነት ሎው ለሽያጭ ካቀረባቸው ኬሚካሎች ጋር እንደሚያያዙ ተነግሯል።

ከሎው ተጎጂዎች መካከል አንዱ የኦንታሪዮ ነዋሪ የነበረው የ19 ዓመቱ አሽቲን ፕሮሰር-ብሌክ ሲሆን እ.አ.አ በመጋቢት 2023 ራሱን አጥፍቷል።

እናቱ ኪም ፕሮሰር ለቢቢሲ "እጅግ ደስተኛ እና ሞገስ ያለው ልጅ ነበር። ሁልጊዜም ተሸናፊዎችን ለመከላከል የሚቆም ነበር" ብላለች።

ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ የአዕምሮ ጤናው ያሽቆለቆለው አሽቲን በቶሮንቶ የኮሌጅ ትምህርቱን ከማቋረጡ በፊት ለአንድ ዓመት ያህል ተከታትሎ ነበር።

ከዚያም "መቸገሩን ቀጥሏል" ብላለች እናቱ ራሱን ከማጥፋቱ በፊት የነበረበትን ሁኔታ ስትገልፅ።

"ልጄን ማጣቴ ያስከተለው ሕመም ሰው እስር ቤት ስለገባ አይቀንስም። ሌላ ሰው ሲሰቃይ ማየቴ አያፅናናኝም" ብላለች።

በዩኬ ደግሞ ዴቪድ ፓርፌት የ22 ዓመት ልጁ ቶማስ ከሎው የገዛውን ንጥረ ነገር መጠቀሙን ተናግሯል።

"ቶም ከሕይወት ደስታን የሚያይ ነበር። እጅግ ባልተለመዱ ነገሮች ላይ ቀልድ ያገኝ ነበር፤ ሁልጊዜ ስለ ሳቁ አስባለሁ" ብሏል።

ቶም 50 ፓውንድ ከፍሎ ንጥረ ነገሩን ገዝቶ ነበር የተባለ ሲሆን፤ አስከሬኑ እ.አ.አ በ2021 ሆቴል ውስጥ ተገኝቷል።

ኬነት ሎው ዩኬ፣ ጣሊያን እና አሜሪካን ጨምሮ ከበርካታ አገራት የተውጣጡ 11 የሕግ አስከባሪ ተቋማት ሰፊ ምርመራ ካደረጉ በኋላ ግንቦት 2023 በቁጥጥር ስር ውሏል።

ታይምስ ጋዜጣ ሎው ለወጣቶች መርዝ እየሸጠ እንደነበር ባደረገው ድብቅ ምርመራ ካጋለጠ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነበር በቁጥጥር ስር የዋለው።

ሎው የሚሸጠው ዕፅ "ለመሞት ምርጡ መንገድ" መሆኑን ለመርማሪ ጋዜጠኛው እንዴት መጠቀም እንዳለበት እንዳማከረ ተነግሯል።

የካናዳ መርማሪ ፖሊሶች ኬነት ሎው ሰዎች ሕይወታቸውን ለማጥፋት የሚያግዛቸውን ቁሳቁሶች እና ንጥረ ነገር የሚሸጥበት በርካታ ድረ ገፆች እንደነበሩት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በካናዳ የወንጀል ሕግ ራስን ለማጥፋት እርዳታ የሚቃርቡ ሰዎች ጥፋተኛ ከተባሉ እስከ 14 ዓመት እስር ይጠብቃቸዋል።