በኦሮሚያ ክልል የቀድሞ ባለቤቱን እና ዳኛን ችሎት ላይ የገደለው ግለሰብ ሆስፒታል ውስጥ ራሱን አጠፋ

የፍትህ ምልክት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ ወልመራ ወረዳ ችሎት ውስጥ አንዲት ዳኛን እና የቀድሞ ባለቤቱን በመግደል የተከሰሰው ግለሰብ ራሱን ማጥፋቱ ተገለጸ።

የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፌስቡክ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ ግለሰቡ ፍርድ ቤት ውስጥ ወንጀሉን በፈጸመበት ወቅት ራሱ ላይም ጉዳት በማድረሱ አዲስ አበባ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሕክምና ሲደረግለት እንደነበር እና አርብ ሰኔ 12/2018 ዓ.ም. ራሱን ማጥፋቱን አስታውቋል።

አቅነው በቀለ የተባለው ግለሰቡ ራሱን ያጠፋው ከሆስፒታሉ ሦስተኛ ፎቅ ላይ በመስኮት ራሱን በመወርወር እንደሆነም የክልሉ ፍርድ ቤት ገልጿል።

የሆለታ ከተማ ዐቃቤ ሕግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጫለሳ በቀለ ግለሰቡ ከነበረበት የሆስፒታል ክፍል ሦስተኛ ፎቅ ላይ እራሱን በመጣል ለኅልፈት መብቃቱን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ግለሰቡ ከፍቺ በኋላ በነበረ የንብረት ክፍፍል ጉዳይ ውሳኔ በተሰጠበት ጊዜ ችሎት ላይ ባለቤቱን እና ዳኛዋን በጥይት በመምታት ካመለጠ በኋላ ራሱ ላይ ጉዳት አድርሷል።

ከወንጀሉ በኋላ ፖሊስ ባደረገው ክትትል ግሰለቡ በቁጥጥር ሥር በዋለበት ጊዜ ከፍተኛ ጉዳት ስለነበረው መጀመሪያ በሆለታ ሆስፒታል ከዚያም ወደ ጳውሎስ ሆስፒታል ለበለጠ ሕክምና ተልኮ ክትትል ሲደረግለት ቆይቷል።

አዲስ አበባ ውስጥ በነበረው የሆስፒታል ቆይታ በፖሊስ ጥበቃ ሥር ሕክምናውን እየተከታተለ ለሳምንታት ከቆየ በኋላ ሰኔ 12 ከቀኑ ሰባት ሰዓት አካባቢ ከነበረበት ሕንጻ መስኮት ራሱን በመጣል ሕይወቱ ማለፉን አቶ ጫለሳ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ግለሰቡ ከሕንጻው ላይ ከወደቀ በኋላ ሕይወቱ ወዲያውኑ ማለፉን እና የአዲስ አበባ እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ እና ዐቃቤ ሕግ በስፍራው ተገኝተው መረጃ መሰብሰባቸውን አስረድተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የተጠርጣሪው ሕይወት የጠፋበት ክስተት ያጋጠመው ግለሰቡ በሆስፒታሉ ተኝቶ የሚደረግለት ሕክምና አብቅቶ በተመላላሽነት እንዲታከም መወሰኑን እና በዚህ ሂደት መካከል እንደሆነም ተናግሯል።

ግለሰቡ ፍርድ ቤት ውስጥ የቀድሞ ባለቤቱን እና ዳኛን ከገደለ በኋላ ባመለጠበት ጊዜ ሆዱ ላይ ራሱን በጥይት በመምታቱ በደረሰበት ጉዳት ነበር ሕክምና ሲከታተል የቆየው።

ግለሰቡ ግንቦት 27/2018 ዓ. ም. ነበር በፍርድ ቤት ክርክር ሲያደርግበት የነበረውን የፍትሐ ብሔር ክስ ውሳኔ በመቃወም ባለቤቱን ወ/ሮ አልማዝ መኮንን እና ዳኛ ወ/ሮ ወርቄ ፉካንሳ በያዘው ሽጉጥ ተኩሶ የገደላቸው።

በወቅቱ የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ጣሰው ለቢቢሲ እንደገለጹት ግለሰቡ ድርጊቱን ከፈጸመ በኋላ ራሱን ለማጥፋት ሙከራ አድርጎ ጉዳት ደርሶበት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሎ ነበር።

በከሳሽ እና ጉዳዩን ሲመለቱ በነበሩት ዳኛ ላይ በተፈጸመው ወንጀል ላይ እንዲሁም ግለሰቡ እንዴት ሽጉጥ ወደ ፍርድ ቤት ይዞ ሊገባ እንደቻለ ፖሊስ ምርመራ እያካሄደ ነበር።

ተጠርጣሪው ግድያውን ከፈጸመ በኋላ በራሱ ላይ ባደረሰው ጉዳት ምክንያት ሆስፒታል ገብቶ ሕክምናውን ሲያጠናቅቅ ፍርድ ቤት ይቀርባል ተብሎም ሲጠበቅ ነበር።

በዚህም መሠረት ግለሰቡ አርብ ሰኔ 12/2018 ዓ.ም. ሕክምናውን ጨርሶ ከሆስፒታሉ ለመውጣት ዝግጅት እያደረገ በነበረበት ወቅት ራሱን ከፎቅ ላይ ወርውሮ ለሞት መብቃቱን የሆለታ ከተማ ፖሊስ መምሪያን ጠቅሶ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አረጋግጧል።

ተከሳሹ ሁለት ሚስቶች የነበሩት ሲሆን ከሁለቱም ጋር ፍቺ ፈጽሞ በንብረት ጉዳይ ክርክር ሲያደርግ ቆይቶ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመቃወም ነበር ባለቤቱን እና ብይን የሰጡትን ዳኛ ፍርድ ቤት ውስጥ ተኩሶ የገደላቸው።

ግለሰቡ ከተፋታት እና ጉዳዩን በፍርድ ቤት ሲታይ ከነበረችው እና ችሎት ውስጥ ከገደላት ሚስቱ ልጆች እንዳሉት ተገልጿል።