የአሜሪካ የኤርትራን ማዕቀቦች ማንሳት፡ ቀይ ባሕር የሸፈነው የሰብአዊ መብት ጥያቄ?

ሕገ መንግሥት እና ምክር ቤት አልባዋ፣ ምርጫ የማይካሄድባት፣ ነጻ መገናኛ ብዙኃን የከሰሙባት፣ ገለልተኛ የፍትሕ ሥርዓትም ያልገነባችው ኤርትራ በዓለማችን አምባገነን አገራት ዝርዝር ውስጥ በግንባር ቀደምነት ከሚጠቀሱ አንዷ ሆና ቀጥላለች።
ከአሜሪካ በተጨማሪ የመንግሥታቱ ድርጅት እና የአውሮፓ ኅብረት የተለያዩ ማዕቀቦችን ጥለውባትም ቆይተዋል።
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም በብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ ንግግር በሚያደርጉባቸው አጋጣሚዎች ምዕራባውያንን በተለይም አሜሪካን አጥብቀው ይተቻሉ።
አሜሪካ "ለሰብአዊ መብት እና ዴሞክራሲ መከበር" በሚል የጣለቻቸውን ማዕቀቦች ልታነሳ እንደሆነ ተዘግቧል።
ሮይተርስ ባለፈው ሳምንት ያስነበበው ዘገባ፤ አሜሪካ ከኤርትራ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት "ለማሻሻል እንደምትፈልግ" ይጠቁማል። ኤርትራም ይሄንን እንደምትደግፍ በይፋ አስታውቃለች።
አሜሪካ ማዕቀቦችን ከማንሳቷ ጀርባ ያለው ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ምክንያት ምንድን ነው? ኤርትራ ላይ የሚቀርቡ የሰብአዊ መብት ጥሰት ክሶችን በተመለከተ ተጠያቂነት እና ፍትሕ ሳይሰፍን ማዕቀቦችን ማንሳትስ ምን ያስከትላል? የሚሉት ጥያቄዎች ተነስተዋል።
የአብዛኞቹ ጥያቄዎች መነሻ ለምን አሁን ላይ ማዕቀቦችን ማንሳት አስፈለገ? የሚለው ሲሆን፤ በተያያዥም የኤርትራ እና አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሻሻል ለኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ምን ማለት ነው? የሚለውን ማንሳት ይቻላል።
ለምን አሁን ማዕቀቦችን ማንሳት አስፈለገ?
አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት በወራት ውስጥ ዓለምን እያመሰቃቀለ ነው። የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት የነዳጅ እና ሸቀጦች አቅርቦትን ጨምሮ ያልነካው ዘርፍ የለም።
ኢራን በኤደን ባሕረ ሰላጤ እና በቀይ ባሕር መካከል የሚገኘው የባብ-ኤል መንደብ ወሽመጥን ለመዝጋት መዛቷ ደግሞ ቀውሱን ያባብሳል።
በሌላ በኩል የኢራን ደጋፊ የሆኑት የየመን ሁቲ አማጺያን ለቀይ ባሕር ስጋት ሆነዋል። በባብ-ኤል መንዳብ አቅራቢያ መርከቦች ላይ በሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ሚሳዔሎች ጥቃቶች ፈጽመዋል።
በዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ ውስጥ አሜሪካ በቀይ ባሕር ላይ ኤርትራን "ስትራቴጂያዊ አጋር" ማድረግ እንደምትፈልግ የቀጣናው ፖለቲካ ተንታኞች ተናግረዋል።
ከሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የሚነሳው ጥያቄ ደግሞ ጂኦ-ፖለቲካዊ ፍላጎት የሰብአዊ መብት ጥያቄን ይበልጣል? የሚለው ነው።
ጂኦ-ፖለቲካዊ ፍላጎት የሰብአዊ መብት ጥያቄን ይበልጣል?
በዩናይትድ ኪንግደም የሚኖሩት ኤርትራዊት የሰብአዊ መብት ተሟጋች እና የሂውማን ራይትስ ኮንሰርን ኤርትራ ዳይሬክተር ኤልሳ ጭሮም "የሰብአዊ መብት ሁኔታ ሳይሻሻል ግንኙነትን ማደስ፤ ጂኦ-ፖለቲካዊ ፍላጎት ከፍትሕ እና ከሰብአዊ ክብር ይበልጣል የሚል አደገኛ መልዕክት ያስተላልፋል" ይላሉ።
የዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሂውማን ራይትስ ዋች የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር ላቲሻ ባዲር በበኩላቸው፤ "የሰብአዊ መብት ጥሰትን ችላ ያለ የሰጥቶ መቀበል ዲፕሎማሲ ለዓመታት የተፈጸሙ ሰፊ ጥሰቶች ያለ ቅጣት መታለፍን የሚያሰርጽ ነው" ብለዋል።
ከአራት ዓመታት በፊት በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ሥር የአሜሪካ ግምጃ ቤት በኤርትራ ላይ ማዕቀቦች ሲጥል በትግራይ ጦርነት ከተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ጋር በተገናኘ ነው።
ማዕቀቡ "ለቀውሱ እና ግጭቱ አስተዋጽኦ ያደረጉ ኤርትራውያንን" የሚመለከት እንደሆነ ተገልጿል። እነዚህ አካላት "የኢትዮጵያን መረጋጋት እና ሉዓላዊነት በማወክም" ተከስሰዋል።
በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 2021 የአሜሪካ መንግሥት በኤርትራ ገዢ ፓርቲ ሕዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲ እና ለፍትሕ (ሕግዴፍ) እንዲሁም ከፓርቲው ጋር ትስስር ባላቸው ሕድሪ ትረስት እና ሬድ ሲ ትሬዲንግ ኮርፖሬሽን ላይ ማዕቀብ ጥሏል።
የኤርትራ ገዢ ፓርቲ የምጣኔ ሃብት አማካሪ ሐጎስ ገብረሕይወት ወልደኪዳን፣ የኤርትራ ብሔራዊ ደኅንነት ኃላፊ ብርጋዴር ጄነራል አብርሃ ካሳ ነማርያም እና የኤርትራ ጦር ኃይል ኤታማዦር ሹም ጄነራል ፊልጶስ ወልደዮሐንስ ላይም ዕቀባ ተጥሏል።
የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ጦርነት "በዝርፊያ፣ በወሲባዊ ጥቃት፣ ንጹኃንን በመግደል እና ሰብአዊ እርዳታን በማስተጓጎል" ተከስሰዋል።
የአሜሪካ መንግሥት የኤርትራ ኃይሎች እንዲሁም ገዢው ፓርቲው እና ባለሥልጣኖች "በጭፍጨፋ፣ በዘረፋ፣ በወሲባዊ ጥቃት እና የተኩስ አቁምን በማደናቀፍ" ተጠያቂ አድርጓል።
በኤርትራ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ላይ የሚደርሰው እንግልት፣ የነጻ መገናኛ ብዙኃን አፈና፣ የተለያዩ ሃይማኖቶች ተከታዮች የሚገጥማቸው ጫና እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የሁለቱን አገራት ግንኙነት እንዳሻከሩት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በድረ ገጹ አስፍሯል።
የኤርትራ መንግሥት የሚቀርቡበት የሰብአዊ መብት ጥሰት ላይ ማሻሻል ሳያደርግ ማዕቀቦቹን ማንሳትን የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች አጥብቀው ኮንነዋል።
የሰብአዊ መብት ተሟጋቿ ኤልሳ፤ ኤርትራ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን የማንሳት ጉዳይ በአገሪቱ ያለውን የሰብአዊ መብት አያያዝ የዘነጋ መሆን እንደሌለበት ያሳስባሉ።
በኤርትራ ባለው ሁኔታ፣ በትግራይ ጦርነት እንዲሁም በቀጠናዊ ግጭቶች እና የደኅንነት ስጋቶች ምክንያት የተጣሉ ማዕቀቦችን ማንሳት "ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከሰብአዊ መብት እና ከተጠያቂነት በላይ ደኅንነት እና ወታደራዊ ትብብርን እንደሚያስቀድም" ያሳያል ይላሉ። ።
አፈና፣ አስገዳጅ ብሔራዊ ውትድርና፣ የዘፈቀደ እገታ፣ ስቅይት፣ የግዳጅ መሰወር፣ የንግግር ነጻነት መገደብ እና የሃይማኖት ነጻነት ማጣትን በተመለከተ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ለዓመታት ንቅናቄ አድርገዋል።
አሁን ላይ በኢራን ጦርነት ምክንያት የቀይ ባሕር አካባቢ በጣም ወሳኝ እየሆነ መምጣቱ የኤርትራን ስትራቴጂያዊ ተፈላጊነት ማጉላቱን ኤልሳ ይስማሙበታል። ሆኖም ከኤርትራ ጋር ንግግር ሲደረግ "በግልጽ የሰብአዊ መብት ጉዳይ መነሳት" እንዳለበት ያሳስባሉ።
"ማዕቀብ ብቻውን ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ አያመጣም" የሚሉት ኤልሳ፤ "ትርጉም ያለው ፖለቲካዊ ለውጥ ካልመጣ፣ ሕግ መንግሥታዊ አስተዳደር ካልተዘረጋ፣ ተጠያቂነት ካልሰፈነ እና ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ከሌሉ ለውጥ አይመጣም" ይላሉ።
የሂውማን ራይትስ ዋች የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር ላቲሻ ባዲር ባለፈው ሳምንት ያወጡት መግለጫም ተመሳሳይ ይዘት አለው።
"በኤርትራም በኢትዮጵያ በትግራይ ክልልም ለከፍተኛ ጥሰቶች ተጠያቂነት እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች ክብር ሳይኖር ማዕቀቦችን አሁን ላይ ማንሳት፤ ለወደፊት ስቅይት እና ብዝበዛ መፈጸም ተቀባይነት እንዳለው ድርጊት እንዲቆጠር የሚያደርግ ነው" ብለዋል።
ላቲሻ ከጠቀሷቸው ነጥቦች አንዱ በኤርትራ መዋቅራዊ ለውጥ እንዲመጣ የጠየቁት 11 የመንግሥት ባለሥልጣናት እና 10 ጋዜጠኞች ከታሰሩ ዘንድሮ 25ኛ ዓመት መሙላቱ ነው።
በሌላ በኩል ኤርትራውያን ወታደሮች በትግራይ ጦርነት ወቅት ከፈጸሙት "ጭፍጨፋ፣ መጠነ ሰፊ ወሲባዊ ጥቃት፣ አፈና እና ምዝበራ" በተጨማሪ "አሁንም ድረስ በሰፈሩባቸው የትግራይ አካባቢዎች ጥቃት ይፈጽማሉ" ብለዋል።
ኤርትራ "ለጥቃቶች ተጠያቂነት ሳታሰፍን፣ ከዚህ ቀደም ከነበረው እና አሁንም ካለው የብዝበዛ አካሄድ መውጣቷን በግልጽ ሳይታይ አሜሪካ ማዕቀቦችን ለማንሳት ማሰብ የለባትም" ሲሉም አሳስበዋል።
ኤርትራ ምን አለች?
ኤርትራ፤ አሜሪካ ማዕቀቦችን ለማንሳት ማሰቧን "በበጎ እንደምትመለከተው" ገልጻለች።
ባለፈው ሳምንት የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ "ፍትሕ፣ ሕጋዊት እና ፍትሐዊነት እንዲሰፍን፤ የተሳሳተ ፖሊሲን የማስተካከል ሒደትን እንደግፋለን" ብሏል።
የቀድሞዎቹ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ባራክ ኦባማ እና ጆ ባይደን የጣሏቸውን ማዕቀቦች "ሕገ ወጥ እና የአንድ ወገን" ሲል አጣጥሏል።
ይህ የኤርትራ መንግሥት አቋም ከዚህ ቀደም ሲያራምድ ከነበረው አሜሪካን የሚኮንን ዕይታ የተለየ ነው።
አሜሪካ የኤርትራን ማዕቀቦች አንስታ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማደስ ማቀዷን በተመለከተ ከኢትዮጵያ በኩል እስካሁን በይፋ የተሰጠ አስተያየት የለም።
የቀይ ባሕር ጉዳይ
አሜሪካ ማዕቀቦችን ለማንሳት ማቀዷን "ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ወደ ጦርነት እንዳትገባ መልዕክት ለማስተላለፍ ያለመ ነው" በሚል የገለጹት ተንታኞች አሉ።
ሮይተርስ እንደዘገበው፤ አሜሪካ በኤርትራ ላይ የጣለቻቸውን ማዕቀቦች የምታነሳ ከሆነ፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት ልትወስድ የምትችለውን የትኛውንም ዓይነት የኃይል እርምጃ እንደማትደግፍ መልዕክት የሚያስተላልፍ መሆኑን በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ዲፕሎማታችን ተናግረዋል።
ለአሥርታት በጠላትነት ሲተያዩ የቆዩት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ግንኙነታቸው ከፍተኛ ለውጥ ቢያሳይም፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር ይገባኛል ጥያቄ በማንሳቷ የሁለቱ አገራት ውጥረት ተባብሷል። ውጥረቱ የጦርነት ስጋትን እስከማጫርም ደርሷል።
ሮይተርስ በዘገባው የጠቀሰው የአሜሪካ መንግሥት ውስጣዊ ሰንድ "የባሕር በርን በኃይል ለማግኘት የሚደረግን የትኛውንም ዓይነት ሙከራ እንደምንቃወም ለኢትዮጵያ በተደጋጋሚ አሳውቀናል" ይላል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ እና ኤርትራ አንዳቸው በሌላኛቸው ውስጣዊ ጉዳይ ላይ ያላቸው "አለመረጋጋትን በሚፈጥር ተሳትፎ" የተነሳ ማሳሰቢያ እንደተሰጣቸው ተገልጿል።
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የፖሊሲ ጥናት ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ሙከረም ሚፍታህ እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የባሕር በር ጥያቄን ለመመለስ "ሌላ አማራጭ ካገኘ" ወደ ጦርነት የመግባት ዕድል አይኖርም።
ማዕቀቦች ተነስተው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከተፈጠረ በንግድ እንዲሁም በሰላም እና ደኅንነት ጉዳዩች በትብብር መሥራት ይከተላል።
አሜሪካ እና ሌሎችም ወዳጆቿ የሆኑ አገራት ወታደራዊ መቀመጫ የሚያገኙበት እንዲሁም የቀጣናውን የንግድ እንቅስቃሴ ሰላም እና ደኅንነት የሚያረጋግጡበት እንደሚሆን ያስረዳሉ።
ኢትዮጵያ፤ እስራኤል የአገርነት ዕውቅና ከሰጠቻት ሶማሊላንድ ጋር እንዲሁም የአሜሪካ አጋር ከሆነችው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር የቅርብ ትስስር አላት።
ስለዚህም አሜሪካ ከኤርትራ ጋር ያለኝን ግንኙነት "ማደስ እፈልጋለሁ" ስትል ከአሜሪካ ወዳጅ አገሮች ጋር አብሮ መሥራትን እንደሚያካትት ዶ/ር ሙከረም ይናገራሉ።
"የኢትዮጵያን ከኤርትራ ጋር ጦርነት ውስጥ መግባት አይፈልጉም" የሚሉት ባለሙያው፤ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መታደሱ "ጦርነት ውስጥ የመግባት ዕድሉን ሙሉ በሙሉ ይዘጋዋል" ይላሉ።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የአሜሪካ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እንዲሁም የእስራኤል ድጋፍ የሚኖረው ከሆነ ከጦርነት ውጭ የሆኑ አማራጮች እንደሚተገበሩ ያክላሉ።
የአሜሪካ ፍላጎት ምንድን ነው?
ዶ/ር ሙከረም እንደሚናገሩት፤ የአሜሪካ መንግሥት ዋነኛ ጥያቄ ዴሞክራሲም ሰብአዊ መብትም አይደለም።
"የእነሱን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማስከበር እንጂ የአንድ መንግሥት የዴሞክራሲ ሥርዓት እና ሰብአዊ መብት ማክበር፤ የተቃዋሚዎች በነጻነት መንቀሳስ፣ የንግግር ነጻነት ሁለተኛ ጉዳይ ነው።"
ኢራን ሆርሙዝ ወሽመጥን መያዟ የበርካታ አገራት የነዳጅ አቅርቦትን አናግቷል። ጉዳዩ የብሔራዊ ደኅንነት ጥያቄ እንዲሆንም አድርጓል።
በተጨማሪም ሁቲዎች በቀይ ባሕር ምዕራባዊ አቅጣጫ የፈጠሩት ስጋት አሜሪካ "በሁለቱም አቅጣጫ ላለመታፈን ቢያንስ አንደኛውን መውጫ እንድትቆጣጠር" የሚገፋ መሆኑን ባለሙያው ይናገራሉ።
የማዕቀቦች መነሳት ምን ያስከትላል?
ኤርትራ እና አሜሪካ አብረው መሥራት ከጀመሩ "ለአምባገነን መንግሥት ሕጋዊ መልክ እና ቅቡልነት የሚሰጠው ይሆናል" በማለትም ዶ/ር ሙከረም ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።
በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙት የምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ተንታኝ አብዱራህማን ሰዒድም ተመሳሳይ አስተያየት አላቸው።
የማዕቀብ መነሳት እና ከአሜሪካ ጋር ትብብር ማድረግ "ለኢሳያስ ሕጋዊነት ይሰጣቸዋል" በማለት ይገልጹታል።
የትግራይ ጦርነትን ጨምሮ አል-ሻባብን ከመደገፍ ጋር በተያያዘ እና በሌሎችም ቀጣናዊ ጉዳዮች የተጣሉት ማዕቀቦች በኤርትራ መንግሥት ላይ ጫና አሳድረዋል ብለው አያምኑም።
ኤርትራ የጦር መሣሪያ እንዳታስገባ ማዕቀብ ቢጣልም "በቂ መሣሪያ ስላላት" እንዲሁም "በትግራይ ጦርነት ወቅት ከኢትዮጵያ መሣሪያ በመውሰዳቸው" እምብዛም ውጤታማ አለመሆኑን ይጠቅሳሉ።
በሌላ በኩል የኤርትራ መንግሥት በኢ-መደበኛ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ በመሠማራቱ ምጣኔ ሃብታዊ ማዕቀቦች ግባቸውን እንዳልመቱ ያክላሉ።
በቀጣይም የአሜሪካ ማዕቀቦችን ማንሳት በኤርትራ አምባገነናኢዊ አካሄድ ላይ ብዙም ለውጥ ያመጣል ብለው አይጠብቁም።
"ኢሳያስ በ80 ዓመታቸው ለውጥ አያመጡም. . . ኢሳያስ እና ግብረ አበሮቻቸው እንዳሻቸው ለማድረግ ፍጹም የሆነ ሥልጣን አላቸው። ለሕግም ለሕግ ተቋማትም የማይገዛ ሥርዓት ነው።"
አሜሪካም ከኤርትራ ጋር በሚኖራት ግንኙነት ጥቅሟን ከማስጠበቅ በዘለለ የሰብአዊ መብት እና ዴሞክራሲ ጉዳይ ብዙም ግድ የሚሰጣት አይሆንም።
የፖሊሲ ጥናት ባለሙያው ዶ/ር ሙከረም "አሜሪካ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሟን ለማስከበር ከሰውም፣ ከመልዓክም፣ ከሰይጣንም ጋር ለመሥራት ዝግጁ ናት" በማለት ይገልጹታል።














