ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዋስ ከተለቀቁ "ፅምዶን ሊቀላቀሉ ይችላሉ" በሚል ፖሊስ ይግባኝ በማቅረቡ የኢሕአፓ ፖለቲከኞች እና ጠበቃ አበራ ሳይፈቱ ቀሩ
ባለፈው ሳምንት ፍርድ ቤት ከእስር በዋስ እንዲለቀቁ የወሰነላቸው ፖለቲከኞች እና የሕግ ባለሙያ ፖሊስ ይግባኝ በማቅረቡ ምክንያት ሳይፈቱ መቅረታቸውን ጠበቃቸው ለቢቢሲ ተናገሩ።
ተጠርጣሪዎቹ በዋስ የሚፈቱ ከሆነ "ከፅምዶ ቡድን ጋር ተቀላቅለው ሊሰወሩ ይችላሉ" በማለት የስር ፍርድ ቤትን የዋስትና ውሳኔ በመቃወም ፖሊስ ይግባኝ ጠይቋል።
"በሽብር ወንጀል" የተጠረጠሩት የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ፖለቲከኞች አቶ አበበ አካሉ እና አቶ ይሳቅ ወልዳይ እንዲሁም ጠበቃ አበራ ንጉሥ፣ እያንዳንዳቸው በ50 ሺህ ብር ዋስ እንዲፈቱ የፌዴራሉ ፍርድ ቤት ባለፈው ሳምንት ዓርብ ነሐሴ 29/2018 ዓ.ም ነበር የወሰነው።
የተጠርጣሪዎቹ ቤተሰቦች ትላንት ሰኞ ጳጉሜ 2 የዋስትናውን ገንዘብ ቢያስይዙም፣ ፖሊስ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለቱ አለመፈታታቸውን ጠበቃቸው አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የፌዴራል ፖሊስ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ባቀረበው የይግባኝ አቤቱታው፣ ሦስቱ ተጠርጣሪዎች "ጫካ ከሚገኘው ፅምዶ ቡድን ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው" ሲል አመልክቷል።
በመሆኑም በዋስ የሚፈቱ ከሆነ "ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ከፀረ-ሰላም ቡድኑ ጋር ሊቀላቀሉ እንደሚችሉ በቂ ጥርጣሬ አለኝ" ያለው ፖሊስ፣ "በሚፈለጉበት ጊዜ ሊሰወሩብን ይችላሉ" በማለት ተቃውሞውን መግለጹን ጠበቃቸው ገልፀዋል።
የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ እንዲሰጠውም ፖሊስ በማመልከቻው ጠይቋል።
ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢወጡ "ፅምዶን ሊቀላቀሉ ይችላሉ" በሚል በፖሊስ የቀረበው አቤቱታ በስር ፍርድ ቤት ያልተነሳ አዲስ መከራከሪያ እንደሆነ አቶ ሰለሞን አንስተዋል።
በሕጉ መሠረት፣ ፖሊስ ይግባኝ ማቅረብ የሚችለው "በስር ፍርድ ቤት በተከራከረባቸው ነጥቦች ላይ ብቻ እንጂ አዲስ ነገር ማቅረብ አይችልም" የሚሉት ጠበቃው፣ ዛሬ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በነበረው ክርክር ላይ ይግባኙ ውድቅ እንዲደረግ መከራከራቸውን ገልፀዋል።
የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ችሎት፣ ጉዳዩን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለመስከረም 5/2019 ዓ.ም. ቀጠሮ እንደሰጠ ተናግረዋል።
አቶ ሰለሞን እንዳሉት፣ ከተጠርጣሪዎቹ መካከል ሁለቱ አቶ ይሳቅ ወልዳይ እና አቶ አበራ ንጉሥ ከነበሩበት የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ወደ ቦሌ 24 ፖሊስ ጣቢያ ሲዛወሩ አቶ አበበ አካሉ እዚያው በነበሩበት ናቸው።
ሁለቱ ፖለቲከኞች እና የሕግ ባለሞያው አቶ አበራ በቁጥጥር ስር የዋሉት ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም ነው።
ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት "ከፅምዶ ቡድን ጋር ከበድብቅ ግንኙነት በማድረግ" በአዲስ አበባ በሚገኙ የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ተቋማት እና በመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ላይ የሽብር ጥቃት ለመፈፀም በእንቅስቃሴ ላይ እያሉ ነው" ሲል ፖሊስ ወንጅሏል።