ቡርኪና ፋሶ ከፈረንሳይ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋረጠች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የቡርኪና ፋሶ ወታደራዊ ጁንታ ከፈረንሳይ ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማቋረጡን አስታወቀ።

ፈረንሳይ ከቡርኪና ፋሶ ብሔራዊ ፍላጎቶች ጋር የሚጻረሩ እንቅስቃሴዎችን አካሂዳለች ሲልም ወንጅሏል።

ካፕቴን ኢብራሒም ትራኦሬ ሥልጣን ከያዙ አንስቶ በቡርኪና ፋሶ እና በቀድሞ ቅኝ ገዢዋ ፈረንሳይ መካከል ያለው ግንኙነት ሻክሯል።

ኢብራሒም ትራኦሬ በአውሮፓውያኑ 2022 በመፈንቅለ መንግሥት መንበረ ሥልጣኑን ከተቆጣጠሩ ወዲህ ፀረ ምዕራባውያን አጀንዳ ማራመድ ቀጥለዋል።

የኮምንኬሽን ሚኒስትር ፒንግዌንዴ ጊልበርት ኦዬድራጎ እንደተናገሩት ፈረንሳይ በአገራቸው ላይ "ግድየለሽ ንቅናቄ" እያደረገች ሲሆን፤ "ኒዮ ኮሎኒያል ፍላጎቶችንም" እያራመደች ትገኛለች።

የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ውሳኔውን "ፀበኛ እና መሠረት አልባ" ሲል ተችቷል።

በተጨማሪም "የቡርኪና ፋሶ መንግሥት እየሄደበት ያለውን አሳሳቢ መንገድ ያሳያል" ብሏል።

ፈረንሳይ በቡርኪና ፋሶ ያሉ ዜጎቿ "ከፍተኛ ጥንቃቄ" እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ ሰጥታለች።

ኢብራሒም ትራኦሬ ሥልጣን እንደያዙ የፈረንሳይ ወታደሮችን ከአገራቸው አባርረዋል።

ፈረንሳይ "ስውር አጀንዳ" አላት ብለው የከሰሱት መሪው ፊታቸውን ወደ ቻይና እና ሩሲያ አዙረዋል።

ቡርኪና ፋሶ በቅርቡ ያወጣችው መግለጫ በሁለቱ አገራት መካከል መከባበር እንደሌለ ይጠቁማል።

ፈረንሳይ ቡርኪና ፋሶን በዓለም አቀፍ መድረክ "የማግለል አላማ እንዳላት" እና "አዋኪ ቡድኖችን እንደምትደግፍ" የአገሪቱ መንግሥት ገልጿል።

"ግንኙነታችንን ለማቋረጥ የወሰነው ከተቋማት ጋር ነው። የፈረንሳይ እና ቡርኪና ፋሶ ሕዝብን ታሪካዊ፣ ሰብአዊ፣ ባህላዊ እና ማኅበራዊ ግንኙነትን ጥያቄ ውስጥ የሚከት አይደለም" ሲልም ባወጣው መግለጫ አቋሙን አንጸባርቋል።

ወታደራዊው ጁንታ በ2024 ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እንደሚመልስ ቃል ቢገባም በያዝነው ዓመት ጥር ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በይፋ አክስሟል።

ቡርኪና ፋሶ እና ወታደራዊ መንግሥት ያላቸው ጎረቤቶቿ ማሊ እና ኒጀር ከምዕራብ አፍሪካው ቀጣናዊ የትስስር መድረክ ራሳቸውን ያገለሉት አምና ነበር።

ከ2023 ጀምሮ ፈረንሳይ በቡርኪና ፋሶ አምባሳደር የላትም።

ከሁለት ዓመት በፊት ሦስት የፈረንሳይ ዲፕሎማቶች "የዓመፅ ድርጊት በመፈጸም" ተከስሰው ከቡርኪና ፋሶ መባረራቸው ይታወሳል።