በ20 ዓመታቸው ከአንድ ሰው ከተለገሰ የወንድ ዘር ፍሬ እንደተወለዱ ያወቁት 'እህትማማቾች'

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

ናታሻ፣ ጄማ እና ሄለን አባታቸውን በእርግጠኝነት እንሚያወቁ አምነው ነበር ያደጉት።

ከአሥርት ዓመታት በኋላ የዘረ መል (ዲኤንኤ) ምርመራ ሲያደርጉ ነው ከአንድ ለጋሽ ከተገኘ የወንድ ዘር ፍሬ እንደተፀነሱ ያወቁት።

በአውሮፓውያኑ 1991 በዩናይትድ ኪንግደም የዘር ልገሳ ሕግ ከመውጠቱ በፊት ነበር የተፀነሱት። ወቅቱም በተለገሱ የወንድ ዘር ፍሬዎች የሚወለዱ ልጆች የተበራከተበት በመሆኑ የዚያ ትውልዶች አካል መሆናቸውን ይናገራሉ።

ራሳቸውንም "ከአንድ የዘር ፍሬ የተገኙ እህትማማቾች" ብለው ይጠራሉ። እና አዲስ ያገኙትን የእህትማማችነት ግንኙነት በጋራ እየቃኙ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ሲገናኙ የነበረውን ቅፅበት ሲገልፁ "ልክ አንደ አስማት ነበር። አስማታዊ ስሜት ተሰማን። የደስታ እንባ ነበር" ይላሉ።

ጄማ እና ሄለን በርክሻየር ከሚባል ቦታ ነው አብረው ያደጉት። ያሳዳጋቸው አባታቸው ወላጅ አባታቸው እንደሆነ ነበር የሚያምኑት።

በ20ዎቹ ዕድሜ እያሉ ነበር በወንድ ዘር ፍሬ ልገሳ እንደተወለዱ ያወቁት።ነገር ግን ከአንድ ለጋሽ እንደተወለዱ አያውቁም ነበር። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በጊዜው የነበራው የመረጃ አያያዝ ውስን ስለነበረ ነው።

የ36 ዓመቷ ጄማ "በጊዜው የወንድ ዘር ፍሬ ልገሳ የተስፋፋ ነበር። እናም በርካታ ወላጆች ልጆቹን እንደ ራሳቸው አድርገው እንዲያሳድጉ ተነግሯቸዋል። ላለመናገር ቅድመ ሁኔታዎች ነበር" ትላለች።

የዩናይትድ ኪንግደም የውልደት ተቆጣጣሪ የሆነው ባለሥልጣን በአውሮፓውያኑ ነሐሴ 1991 ተመሥርቶ የቁጥጥር ሥርዓትን ይፋ አድርጓል።

የዘረ መል ምርመራው አንድ ወላጅ አባት እንዳላቸው ብቻ ሳይሆን ከሌሎች እህቶቻቸው ጋርም አስተዋውቋቸዋል።

"በአካሌ ላይ ለውጥ እንዳለ ተሰማኝ። ራሴን እንዳላወቅኩ ተሰማኝ። እና የሠራኋትን አያንዳንዷን ቅንጣት ነገር መጠየቅ ጀመርኩ፤ ምን አልባት ዘሬ ሊሆን ይችላል ብዬ ገመትኩ" ትላለች ጄማ።

በሀምሻየር ለምትኖረው የ35 ዓመቷ ሄለን መጀመሪያ የተሰማት ድንጋጤ ቀለል ሲልላት ዜናው እውነትን ይዞላት መጣ።

"እንግዳ የሆነ የመረጋጋት ስሜት ላዬ ላይ ወረደ። በሕይወቴ የሆኑ ጉዳዮችን መለስ ብዬ አየሁ እና በድንገት ትርጉም ሰጡኝ።"

ጄማ እና ሄለን ከዚህ በኋላ ከተመሳሳይ የወንድ የዘር ፍሬ ለጋሽ የተወለዱ ሁለት እህቶችን አግኝተዋል። ከእነዚህም ውስጥ ኢሴክስ የምትኖረው የ36 ዓመቷ ናታሻ ጎልድስቲን-ኦፓሲያክ አንዷ ናት።

በዘር ፍሬ ልገሳ እንደተወለደች በ21 ዓመቷ አውቃለች። ይሁን እንጂ የዘረ መል ምርመራ ያደረገችው በ31 ዓመቷ ነበር።

"ግማሽ ማንነቴ ከምን እንደተሠራ ለማወቅ በመጓጓቴ ምክንያት ነው ያደረኩት። እህቶች አገኛለሁ ብዬ በፍፁም አላሰብኩም ነበር" ትላለች።

"በመጨረሻም ዘመዶች እንዳገኘሽ የሚገልፅ ኢሜል አንድ ቀን ይደርስሻል። ልክ እንደ ፍቅረኛ አገናኝ መተግበሪያ አጋር አግኝተሻል ይላል፤ ይኸው እህቶችሽ።"

ሄለን እና ጄማ ለናታሻ መልዕክት ልከው ከአንድ ወር በኋላ ለመገናኝ ተስማሙ።

"ልክ እንደ ማግኔት አንድ ላይ እንደተሳሳብን ሁሌ እናወራለን" ትላለች ጄማ።

"ከናታሻ ጋር ቁጭ እንዳልን በደቂቃ ውስጥ የምናወራበት መንገድ አንድ ዓይነት እንደሆነ አወቅን። በጉዳዮች ላይ ተመሳሳይ እይታ አለን፤ በጣም አንግዳ ነው፤ ነገር ግን አስማተኛ ነው።"

ከዚህ በፊት አንዳንድ ቦታዎች ላይ ለመገናኘት ተቃርበው እንደነበርም አወቁ።

ጄማ እና ናታሻ ከ15 ዓመት በፊት ሊድስ ዩኒቨርስቲ እያሉ አንድ የመኖሪያ ሕንፃ ውስጥ ነበሩ።

"ልጆች እያለን እንዳንገናኝ መደረጉ በጣም ያሳዝናል። የጋራ ልደቶችን አብረን ማክበር እንችል ነበር። በጣም ብዙ ነገሮችን ማጣታችንን ስናስብ በጣም ያሳዝናል" ትላለች ጄማ።

ሦስቱም ለአብነት ያህል በተሰጥኦ ተመሳሳይ ባህሪ አላቸው። ጄማ የሥዕል፣ ሄለን የሙዚቃ፣ ናታሻ ደግሞ የዳንስ ሥልጠና ተከታትለዋል። በሕይወታቸው በሆነ ጊዜ መምህር ወይም ሌክቸረር ሆነዋል።

"የጥበብ ተሰጥኦ ባለው ቤተሰብ ውስጥ አላደኩም። ነገር ግን ከጥበባዊ ሰዎች እንደመጣሁ አቅኩ። ሁሉም ነገር ተስተካከለ፤ የራስሽ ዋጋ መስመሩ እንደተገጣጠመ ይሰማሻል" ትላለች ጄማ።

ሁሉም ሦስት እህትማማቾች የመጡበትን ማወቃቸው ማንነታቸው ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ይናገራሉ።

ጄማ እና ሄለንን ያሳደገው አባት የዌልስ ዜጋ ነው። እናም ጥንዶቹ ዌልስን በመጎብኘት የዌልስን የራግቢ ቡድን በመደገፍ አድገዋል።

"ዌልሳዊ መሆናችን የዕድገታችን አስፈላጊ አካል ነው። በጣም ጠንካራ በሆነ የኩራት ስሜት ነው ያደግነው" ትላለች ጄማ።

በተመሳሳይ ሁኔታ ወላጅ አባታቸው የዌልስ ዘር እንዳለው የዘረ መል ምርመራው አሳይቷል።

"እንደ ዕድል ሆኖ ምንም አልተለወጠም። ፈረንሳያዊ ወይም ሌላ መሆናችንን ብናውቅ ኖሮ ምን ልናስብ እንደምንችል አላውቅም። መሠረቴ የዌልስ ማኅበረሰብ አካል እንዳልሆነ ማወቅ አሳዛኝ ስሜት ነበር የሚሆነው።"

ናታሻ ስታድግ ዌልሳዊ እንደሆነች አታስብም ነበር። ነገር ግን ግንኙነቶች ነበሯት።

"በልጅነቴ. . . በሰሜናዊ ዌልስ አካባቢዎች ጊዜ አሳልፊያለሁ። ስለዚህ በእንግዳ መልኩም ቢሆን ከዌልስ ጋር በጣም እንደተሳሰርኩ ይሰማኛል።

"የዘር ፍሬውን የለገው ሰው ከዚህ አካባቢ መሆኑን ማወቄ በጣም አስደሰተኝ።"

ሄለን በበኩሏ "ማን እንደሆንሽ ስታውቂ፤ ይህን በማድረጋችን በጣም ዕድለኞች ነን። እፎይታ ይሰጣል" ትላለች።

እህትማማቾቹ ወላጅ አባታቸው ማን እንደሆነ አውቀዋል። ለማግኘት የላኩት መልዕክት "በደግነት እና በአዎንታዊ" እንደተቀበለው ተናግረዋል።

የዩኬ የወሊድ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ከአውሮፓውኑ 1991 ወዲህ ፈቃድ በተሰጣቸው ክሊኒኮች ከ85 ሺህ በላይ ሰዎች በወንድ የዘር ፍሬ ልገሳ እንደተወለዱ ተናግሯል።

በ2005 በተደረገ የሕግ ለውጥ ማንነት ሳይታወቅ የወንድ ዘር ፍሬ፣ የሴት እንቁላል እና ሽሎችን መለገስ ክልክል ነው።

ይህም ማለት በዘር ፍሬ፣ በእንቁላል እና በሽል ልገሳ የተፀነሰ አንድ ልጅ 18 ዓመት ሲሞላው የለጋሾችን ማንነት ማወቅ እና መገናኘት ይችላል።

ከአንድ የዘር ፍሬ የተገኙት ሦስቱም "እህትማማቾች" በመሆናቸው እንደማይለያዩ ይናገራሉ። በዚህ ስያሜያቸውም በጋራ ፖድካስት ጀምረዋል።

"ሦስታችንም ብቸኝነት ተሰምቶን ነበር። ይህንንም ያወቅነው ስናወራበት ነው፤ መልስ ማግኘት እና እንድንተዋወቅ አድርጎናል" ትላለች ናታሻ።

"ይህን ፖድካስት በመጀመራችን የእህትማማች ፍቅራችንን ገንብተናል።"

"ብዙ የምናወራው ነገር አለን፤ 30 የአበባ ዓመታት" ስትል ጀማ ከሄለን ጋር የበለጠ እንድትቀራረብ እንዳደረጋት ታክላለች።

ሦስቱ እህቶች በተለገሰ የዘር ፍሬ ስለሚፈጠር ፅንስ ግንዛቤ ማስጨበጥ ይፈልጋሉ። ናታሻ ሁኔታውን "የዝምታው ፕሮጄክት" ትለዋለች።

ለሰዎች በዘር ፍሬ ልገሳ እንደተወለደች ስትነግር "ግርታ እና ምን ማለት እንደሆነ እውነተኛ አረዳድ" እንደሌላቸው መገንዘብ ችላለች።

አሁን የተሻለ ቁጥጥር ቢኖርም በተለገሰ የወንድ የዘር ፍሬ የተፀነሱ ልጆችን በተመለከተ ምንም ዓይነት ጥበቃ የለም ትላለች።

እህታማማቾቹ ምን ያህል ሌሎች ወንድሞች እና አህቶች እንዳሏቸው አያውቁም። አንድ ለጋሽ ለ10 ቤተሰቦች የሚለው ገደብ እነርሱ ሲወለዱ አልነበረም።

በቅርቡ ቢቢሲ ዌልስ ባደረገው ምርመራ ቁጥጥር የሌለበት የወንድ ዘር ፍሬ ልገሳ በማኅበራዊ የትስስር ገፆች እና መተግበሪያዎች እንደተስፋፋ አጋልጧል።

"የወሊድ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣኑ በእንዲህ ዓይነት መንገድ የተወለዱ ልጆች ለጋሾቻቸው እነማን እንደሆኑ ለማወቅ በሚያደርግ ቁጥጥር ላይ በደንብ እየሠራ ነው" ትላለች ጄማ።

"ሕጎቹ በጣም ተሻሽለዋል። እንደ ፌስቡክ የዘር ፍሬ የመሰሉ አዝማሚያዎች መስፋፋት ይህን ሁሉ ሥራ ወደ ኋላ መመለሱ ያሳዝናል።

"ምንም ሕግ ባልነበረበት ዘመን ነው እኛ የተወለድነው። አሁንም ከዚህ የተለየ አይደለም። በለጋሽ የዘር ፍሬ ለተወለዱ ድምፅ መሆን ከቻልን፤ አንዳንድ ወላጆች ምሥጢር እንዲያደርጉት ወይም ጥያቄ እንዳይጠይቁ በድጋሚ እንዲያስቡ ያደርጋል ብዬ አስባለለሁ።"

ሄለን በዘር ፍሬ ለጋሾች የተወለዱ ልጆች "በዚህ ጊዜ ድምፅ አልባ" እንደሆኑ እና እርሷ እና እህቶቿ "ላለው ሁኔታ ድምፅ" እንደሚሆኑ ተስፋ አላት።