ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዩኤኢ ወደ ሱዳን ለሚጓዙ ቅጥረኛ ወታደሮች መተላለፊያ ናት ሲል ሂውማን ራይትስ ዎች ከሰሰ
የኮሎምቢያ ቅጥረኛ ወታደሮች በዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስ መቀመጫውን ባደረገ ኩባንያ ተቀጥረው በኤምሬት ወታደራዊ ጣቢያዎች በኩል ተሸጋግረው በሱዳን ውስጥ ግፍ እና አሰቃቂ ወንጀሎች የፈፀመውን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ለመደገፍ ተሰማርተዋል ሲል ሂውማን ራይትስ ዎች አስታወቀ።
'ሂውማን ራይትስ ዎች' ዩኤኢ በሱዳን ጦርነት የጦር ወንጀሎችን ፈፅሟል ተብሎ የሚከሰሰውን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) እየደገፈች ለመሆኑ የሚያመለክት ተጨማሪ ማስረጃ አግኝቷል።
ዩኤኢ ግን በግዛቷ ላይ የውጭ ተዋጊዎችን በመቅጠር እና ሥልጠና በመስጠት የሚነሱባትን ክሶችን አስተባብላለች።
"ዩኤኢ ግዛቷን ሱዳንን ጨምሮ ለየትኛውም ግጭት የውጭ ተዋጊዎችን ለመቅጠር፣ ሥልጠና ለመስጠት፣ በገንዘብ ለመደገፍ ወይም ለመሸጋገሪያነት እንዲጠቀሙ አትፈቅድም" ሲል የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተናግሯል።
የሂውማን ራይትስ ዎች ምርመራ እ.አ.አ ከመጋቢት እስከ መስከረም 2025 ድረስ ከኮሎምቢያ ቅጥረኛ ወታደሮች ጋር ቃለ ምልልስ በማድረግ እና በማኅበራዊ የትስስር ገፆች ላይ የተለጠፉ ምሥሎችን በመተንተን ቁልፍ ቦታዎች እና መሣሪያዎችን በመለየት ትንተናውን አካትቷል።
የሱዳን ጦርነት የተቀሰቀሰው በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እና በሱዳን ጦር መካከል ውጥረቱ ካገረሸ በኋላ በሚያዚያ አጋማሽ 2023 ነው።
ከዚህን ጊዜ ጀምሮ ከ150 ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል ተብሎ የሚገመት ሲሆን፤ ከ12.9 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ደግሞ ተፈናቅለዋል።
የሂውማን ራይትስ ዎች ሪፖርት ባለፈው ወር 'ኮንፍሊክት ኢንሳይትስ ግሩፕ' የተባለ ድርጅት ባወጣው የደኅንነት ትንተና በሱዳን ምዕራባዊ ክልል ዳርፉር የኮሎምቢያ ቅጥረኛ ወታደሮች ተሳትፎን ይፋ ካደረገ በኋላ የተከተለ ነው።
የኮሎምቢያ ፕሬዝዳንት ጉስታቮ ፔትሮ ባለፈው ዓመት እነዚህን ቅጥረኛ ወታደሮች "የሞት ጥላ" ብለው የጠሯቸው ሲሆን፤ ቅጥራቸውንም "ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር" ብለው ገልፀውታል።
ሂውማን ራይትስ ዋች በሪፖርቱ ወታደሮቹ ወደ ዳርፉር ከመጓዛቸው በፊት የዩኤኢ፣ ሊቢያ፣ ቻድ እና ሶማሊያ አውሮፕላን ማረፊያዎችን ተጠቅመዋል ብሏል።
አንድ ቅጥኛ ወታደር ለመብት ድርጅቱ "ፓስፖርታችን ላይ ማኅተም አልመቱም" በማለት በዩኤኢ ዋና ከተማ አቡ ዳቢ ያደረገውን ጉዞ አብራርቷል።
"ገባ ብለውን ወጣን፤ ወደ ወታደራዊ ጣቢያ የሚወስደን አውቶብስ እየጠበቀን ነበር።"
የመብት ድርጅቱ ምርመራ እጅግ የተወሳሰበ የኮሎምቢያ እና የኤምሬትስ ኩባንያዎች መረብ እንዳለ ይጠቁማል። ኩባንያዎቹ ለቀድሞ የኮሎምቢያ ሠራዊት አባላት "በአፍሪካ የድሮን ሥራ" የሚል ማስታወቂያ አውጥተው ነበር።
ሂውማን ራይትስ ዎች አቡ ዳቢ መቀመጫውን ያደረገ ኩባንያ ወደ ሱዳን የተጓዙትን ወታደሮች የመለመለው "ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ስልታዊ እና ቴክኒካዊ ድጋፍ ለማቅረብ፣ የእግረኛ ወታደሮች፣ የመሣሪያ ባለሙያ፣ የድሮን አብራሪ፣ የተሽከርካሪ ባለሙያዎች እና አሰልጣኞች ለማቅረብ" እንደሆነ ገልጿል።
እንደ መብት ቡድኑ ከሆነ ቅጥረ ወታደሮቹ እጅግ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ወደተፈፀሙበት የጦር ግንባር ከመዝመታቸው በፊት በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ የጦር ጣቢያዎች ሰልጥነዋል።