ሩቢዮ ከኢራን ጋር የሚደረገው ንግግር የማይሳካ ከሆነ አሜሪካ “ሌላ አማራጭ ትፈልጋለች” አሉ
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ሰኞ ዕለት አገራቸው ከኢራን ጋር ጥሩ ስምምነት ታደርጋለች ወይም “በሌላ መንገድ” ትፈታዋለች ሲሉ ተናገሩ።
በሕንድ የሚገኙት ሩቢዮ ሌሎች “አማራጮችን” ከመፈለግ በፊት ለዲፕሎማሲ ያለውን ዕድል ሁሉ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እሁድ ዕለት ተወካዮቻቸው ከኢራን ጋር ስምምነት ለማድረግ እንዳይጣደፉ አሳስበዋል።
ሩቢዮ “ሆርሙዝን ለመክፈት የሚያስችል ተጨባጭ የሆነ ስምምነት ጠረጴዛው ላይ አለ። ወሽመጡን ክፈቱ፤ ተጨባጭ፣ እውነተኛ በጊዜ የተገደበ ድርድር ወደ ማድረግ ግቡ፤ እናም ተስፋ አለኝ እናሳካዋለን” ብለዋል።
እሁድ ዕለት ፕሬዚዳንት ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ አሜሪካ በኢራን ወደቦች ላይ የጣለችው ዕገዳ “ከስምምነት ላይ እስክንደርስ፣ ስምምነቱ እስኪጸድቅ እና እስኪፈረም ድረስ በሙሉ ኃይል ተግባራዊነቱ ይቀጥላል” ብለዋል።
አክለውም “ሁለቱም አካላት ጊዜ መውሰድ እና የሚገባ ነገር ላይ መድረስ አለባቸው” ሲሉ ጽፈዋል።
የኢራን መንግሥት በትራምፕ ሆነ በሩቢዮ አስተያየቶች ላይ አስተያየቱን አልሰጠም።
ታስኒም የዜና ወኪል ግን አሜሪካ የስምምነቱ ወሳኝ ነጥቦችን እያስተጓጎለች ነው በማለት እንዳይንቀሳቀሱ የታገዱ ፈንዶች እንዲለቀቁ ጠይቋል።
የኢራን ፓርላማ ቃል አቀባይ ኢብራሂም ሬዛይ በበኩላቸው በጦርነቱ ወቅት “ዓይን ላጠፋ ዓይን” የሚል መርህ ሲከተሉ እንደነበር ገልጸው፤ በዲፕሎማሲ አለመግባባት ወቅት ደግሞ “ለተግባር ተግባራዊ ምላሽ መስጠት” የሚል መሆኑን ተናግረዋል።
በኤክስ ገጻቸው ላይ ኢራን በጫናዎች ወይንም ማስፈራሪያዎች አትንበረከክም ያሉት ቃል አቀባዩ፤ አሜሪካ ስምምነት ላይ መድረስ የምትፈልግ ከሆነ መደራደር አለባት ነገር ግን ነዳጅ በ6 ዶላር ማግኘት የምትፈልግ ከሆነ ማስመሰሏን ትቀጥል ሲሉ ጽፈዋል።
በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የሰላም ስምምነት ይፈረማል የሚል ተስፋ እየጨመረ በመምጣቱ ሰኞ ዕለት የዓለም የነዳጅ ዋጋ በ6 በመቶ ገደማ ቀንሷል።