በዓለም ዋንጫ ወቅት ያለው ሙቀት ለተጫዋቾች አደገኛ ሊሆን እንደሚችል ሳይንቲስቶች አስጠነቀቁ

ውሃ የሚጠጣ ኳስ ተጫዋች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ፊፋ በዓለም ዋንጫ ወቅት በከፍተኛ ሙቀት ምክንያት የሚፈጠር ጉዳትን ለመከላከል ያስቀመጣቸው የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎች "በቂ አለመሆናቸውን" ዕውቅ ሳይንቲስቶች አስጠነቀቁ።

ተጫዋቾች ከልክ ባለፈ ወበቅ ምክንያት ለጉዳት እንደሚጋለጡም ሳይንቲስቶቹ አስታውቀዋል።

ዓለም አቀፍ የጤና ባለሙያዎች እና የአየር ንብረት ለውጥ በስፖርት ያለውን ጫና የሚያጠኑ ሳይንቲስቶች ቡድን በጻፈው ግልጽ ደብዳቤ፤ ፊፋ የወሰደው የጥንቃቄ እርምጃ አሁን ካለው ሳይንስ ጋር እንደማይጣጣም ገልጸዋል።

ፊፋ ያስቀመጣቸውን የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎች "ምክንያታዊ አድርጎ ለመውሰድ እንደሚያስቸግር" ሳይንቲስቶቹ ጠቅሰዋል።

ሰውነትን ለማቀዝቀዝ እረፍት መውሰድ እና ከልክ ያለፈ ወበቅ በሚከሰትበት ወቅት ግጥሚያን ማራዘምን ጨምሮ ጠንካራ የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎች መወሰድ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ በሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ከልክ ያለፈ ሙቀት መሰናክል ሊሆኑ እንደሚችሉ ተሰግቷል።

አጥኚዎች እንዳሉት ግጥሚያ ከሚካሄድባቸው 16 ስታድየሞች መካከል በ14ቱ የሙቀት መጠን ከተገመተው በላይ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል።

በደቡብ አሜሪካ እና ሰሜን ሜክሲኮ እኩለ ቀን ላይ ያለው አማካይ የሙቀት መጠን ከ30 ሴንቲግሬድ እስከ 40 ሴንቲግሬድ ይደርሳል ተብሎ ይገመታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሙቀት፣ እርጥበት አዘል አየር፣ በከፍተኛ ፍጥነት የሚጓዝ ንፋስ እና ጠንካራ የፀሐይ ጨረር የዓለም ዋንጫ በሚካሄድባቸው ከተሞች እንደሚከሰቱ ተገልጿል።

እግር ኳስ ተጫዋቾች ከፍተኛ መጠን ባለው ሙቀት ሰውነታቸው ጫና ውስጥ እንደሚወድቅም ሳይንቲስቶቹ አስጠንቅቀዋል።

ፊፋ "የተጫዋቾችን፣ ዳኞችን፣ ደጋፊዎችን፣ ሠራተኞችን እና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪዎችን ጤና እና ደኅንነት ለመጠበቅ ቁርጠኛ ነኝ" ብሏል።

ውድድሩ ሲዘጋጅ ከአየር ንብረት ጋር የተያያዙ ተጋላጭነቶች ከግምት ውስጥ እንደገቡ ፊፋ አስታውቋል።

ፊፋ "የተጫዋቾችን ደኅንነት ለመጠበቅ" ካወጣው መመሪያ መካከል በማንኛውም የአየር ሁኔታ ውስጥ በሁለቱም የግጥሚያ ክፍሎች የሦስት ደቂቃ እረፍት ማድረግ ይጠቀሳል።

የቴክኒክ ድጋፍ ለሚሰጡ ባለሙያዎች የአየር ሁኔታን ያማከለ መቀመጫ እንደሚዘጋጅ ተገልጿል።

ሙቀት እንዲሁም ሙቀት እና እርጥበት ተደባልቀው ሰውነት ላይ የሚደርሰውን ጫና የሚመዝነውን መለኪያ ሥርዓት ፊፋ እንደሚጠቀም አስታውቋል።

ይህ አሠራር 'ወርቃማ መርኅ' ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፤ ሙቀት 28 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ላይ ሲደርስ ለአትሌቶች ጤና አስጊ ነጥብ መሆኑን ያመለክታል።

ፊፋ ባወጣው የአደጋ ጊዜ መመሪያ፤ መለኪያ ሥርዓቱ የሚያሳየው ሙቀት 32 ሴንቲግሬድ ወይም ከዚያ በላይ ከሆነ የግጥሚያው አዘጋጆች "ከወበቅ ጋር የተያያዘ ሕመም እንዳይከሰት የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃ መውሰድ አለባቸው" ይላል።

ከፍተኛ ሙቀት በሚከሰትበት ወቅት ተመልካቾችን ለመጠበቅ እርምጃዎች እንደሚወሰዱም ፊፋ ገልጿል።

የታሸገ ውሃ ይዘው ወደ ስቴድየም እንዲገቡ መፍቀድ አንደኛው መንገድ ነው። ስቴድየሞች ቀዝቃዛ እንዲሆኑ ከማድረግ በተጨማሪ ጥላ ቦታዎች በስፋት እንዲዘጋጁ ተደርጓል።

በስቴድየሞች የውሃ ብናኝ መርጨት፣ ቅዝቃዜ የሚሰጡ አውቶብሶች ማዘጋጀች እና የውሃ ተደራሽነት ማስፋትም ፊፋ የወሰዳቸው ቅድመ ጥንቃቄዎች ናቸው።

የዓለም ዋንጫ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሳይንቲስቶች ስጋት ምንድን ነው?

ለፊፋ የተላከው ደብዳቤ ላይ ፊርማቸውን ያኖሩት የአሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያ እና አውሮፓ ሳይንቲስቶች ናቸው።

ፊፋ ሊቀይራቸው ይገባል ያሏቸውን አሠራሮች እንደሚከተለው በዝርዝር አስቀምጠዋል።

  • ከ28 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ የሆነ ሙቀት ሲከሰት ጨዋታዎችን ማራዘም
  • ሰውነትን ለማቀዝቀዝ የሚወሰደውን እረፍት ቢያንስ ወደ ስድስት ደቂቃ ማራዘም
  • የተጫዋቾችን ሰውነት ለማቀዝቀዝ የተሻሉ ቦታዎች ማዘጋጀች
  • የቅርብ ጊዜ ሳይንስን በተከተለ መንገድ ቅድመ ጥንቃቄን ማሻሻል

ዓለም አቀፍ የተጫዋቾች ማኅበር (ፊፍፕሮ) ያቀረበውን አሠራር ፊፋ መተግበር እንዳለበት ሳይንቲስቶቹ አሳስበዋል።

ደብዳቤውን ያስተባበሩት የኒው ዌዘር ኢንስቲትዩት ኃላፊ አንድሪው ሲምስ "ሰዎች ለከፍተኛ ሙቀት ሲጋለጡ በፍጥነት ብዙ ነገሮች ሊበላሹ ይችላሉ። የተጫዋቾች ደኅንነት ሳይዘገይ በፊት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል" ሲሉ ለቢቢሲ ስፖርት ተናግረዋል።

ፊፋ የተጫዋቾችን "ጤና እና ደኅንነት አደጋ ውስጥ እየከተተ ነው" ብለው እንደሚያምኑም አክለዋል።

ደብዳቤው ላይ የፈረሙት የዩኒቨርስቲ ኦፍ ኮነክቲከት መምህር ፕሮፌሰር ዳግላስ ካሳ እንደገለጹት ፊፋ ያስቀመጠው መመሪያ ደረጃውን የጠበቀ አይደለም።

"በግጥሚያዎች መካከል የሚወሰደው እረፍት ከሦስት ደቂቃ በላይ መራዘም አለበት። ቢያንስ አምስት ደቂቃ መሆን ይገባዋል። ስድስት ደቂቃ ቢሆን ደግሞ የበለጠ ይመረጣል" ሲሉ አስረድተዋል።

ፊፋ የሳይንቲስቶቹን ደብዳቤ ተመርኩዞ መመሪያዎችን የዓለም ዋንጫ ከመጀመሩ በፊት ያሻሽላል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ አክለዋል።

ፊፋ ምን ምላሽ ሰጠ?

በቀጣዩ የዓለም ዋንጫ ከልክ ያለፈ ወበቅ ከፍተኛ ስጋት ደቅኗል። ሙቀት፣ ነጎድጓዳማ ዝናብ እና ሰደድ እሳት የሚፈጥረው የአየር ብክለት በአሜሪካ፣ በካናዳ እና በሜክሲኮ እንደሚከሰቱም ይጠበቃል።

ወርልድ ዌዘር አትሪብዩሽን ባወጣው አዲስ ትንታኔ መሠረት በአውሮፓውያኑ 1994 በዚሁ ቀጣና ከተካሄደው የዓለም ዋንጫ አንጻር በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ተጫዋቾች እና ተመልካቾች ከፍተኛ ሙቀት እና ደረቅ አየር ይገጥማቸዋል።

ከግጥሚያዎቹ ሩብ ያህሉ ከ26 ሴንቲግሬድ በላይ በሆነ ሙቀት ውስጥ እንደሚከናወኑ ሳይንቲስቶች ያምናሉ።

አምስት ጨዋታዎች ደግሞ በ28 ዲግሪሴንቲግሬድ ይካሄዳሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይሄ የሙቀት መጠን ፊፋ ካስቀመጠው 'ወርቃማ መርኅ' አሠራር አንጻር በደረቅ ሙቀት ውስጥ 38 ዲግሪ ሴንቲግሬድ እና እርጥበት አዘል በሆነ ሙቀት ውስጥ 30 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ጋር ይስተካከላሉ።

ይህም ዓለም አቀፍ የተጫዋቾች ማኅበር (ፊፍፕሮ) ለተጫዋቾች አደገኛ ብሎ ያስቀመጠው ነጥብ ነው።

ፊፋ የሳይንቲስቶቹ ደብዳቤ ላይ በቀጥታ አስተያየት ባይሰጥም "በእርከን የተከፋፈለ አደጋ መቀነሻ መንገድ" እንደሚተገብር አስታውቋል።

የፊፋ ቃል አቀባይ እንደተናገሩት በውድድሩ ወቅት ከፍተኛ ሙቀት በሚስተዋልባቸው ከተሞች ከአየር ሁኔታው ጋር ተስማሚ የሆነ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ ናቸው።

የሙቀት መቆጣጠሪያ መሣሪያዎች እና የፊፋን መርህ በመጠቀም ውሳኔዎች እንደሚተገበሩም አክለዋል።

የጨዋታዎች ድልድል የተካሄደው የአየር ሁኔታን ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።

ከፍተኛ ሙቀት በሚኖርባቸው ወቅቶች ጨዋታዎች እንደማይካሄዱም አክለዋል። በእነዚህ ወቅቶች የሚካሄዱ ግጥሚያዎች ጣሪያ ባላቸው ስቴድየሞች ይከናወናሉ።

ፊፋ እንዳለው ያወጣው መርሃ ግብር ጉዞን ለመቀነስ ያለመ እና የእረፍት ቀናትን የሚያራዝም መሆኑን አስታውቋል። ለእያንዳንዱ አካባቢ የሙቀት ሁኔታ ተስማሚ የሆነ የአደጋ ተጋላጭነት ግምገማም ይካሄዳል።

ፊፋ የአየር ሁኔታውን በቀጥታ እየተከታተለ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎችን እንደሚተገብር አስታውቋል።

ውድድሩን ከሚያስተናግዱ አገራት በመተባበር "ደኅንነቱ የተጠበቀ" ውድድር እንደሚያካሂድም አክሏል።