ትራምፕ አረብ አገራት ከእስራኤል ጋር እንዲፈራረሙት የሚፈልጉት 'የአብርሃም ስምምነት' ምንድነው?

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር ለሚደረገው የሰላም ስምምነት "ሁሉም አገራት የአብርሃም ስምምነትን በአስቸኳይ እንዲፈርሙ" የሚል ጉዳይን እንደ አንድ ቅድመ ሁኔታ ሊቀመጥ እንደሚችል ጠቁመዋል።

'አብርሃም አኮርድስ' በእስራኤል እና በርካታ አረብ አገራት መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማሻሻል የተደረጉ ስምምነቶች የያዘ ነው። ስምምነቱ የተፈረመው በ2020 በዶናልድ ትራምፕ የመጀመሪያው ሥልጣን ዘመን ነበር።

ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ "ሁሉም አገራት የአብርሃም ስምምነትን በአስቸኳይ እንዲፈርሙ በአስገዳጅነት እየጠየቅሁ ነው። ኢራን እንደ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከእኔ ጋር ስምምነቱን የምትፈርም ከሆነ፤ በዚህ ወደር የለሽ የዓለም ጥምረት አካል መሆናቸው ትልቅ ክብር ይሆናል" ብለዋል።

ትራምፕ ይህንን ያሉት ከሳዑዲ አረቢያ፣ ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ከኳታር፣ ከፓኪስታን፣ ከቱርክ፣ ከዮርዳኖስ፣ ከባህሬን እና ከግብፅ መሪዎች ጋር በስልክ ከተነጋገሩ በኋላ ነው። ከእነዚህ አገራት መካከል የተወሰኑት ቀድሞውኑም ስምምነቱ ፈርመዋል።

እስካሁን ድረስ ዕቅዱን ውድቅ በማድረግ ይፋዊ ምላሽ የሰጠችው ብቸኛ አገር ፓኪስታን ናት።

የመከላከያ ሚኒስትሩ ኻዋጃ አሲፍ ፓኪስታን "ከመሠረታዊ ርዕዮተ ዓለሞቿ" ጋር የሚጋጭ ማንኛውንም ስምምነት አትቀላቀልም ብለዋል። የእስራኤልንም ቃል "አይታመንም" ሲሉም የአገራቸውን አቋም አስታውቀዋል።

አብዛኛው ሕዝብ ሙስሊም በሆነባቸው አገራት እንዲሁም በሌላኛው ወገን በቆሙት አሜሪካ እና እስራኤል መካከል ዋነኛ የጥል ምክንያት የሆነው የፍልስጤም አገርነት እና የሁለት አገራት መፍትሔ ጉዳይ ነው። እስራኤል በጋዛ የከፈተችው ወታደራዊ ዘመቻ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን ይበልጥ ውስብስብ አድርጎታል።

የጋዛ ጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው እስራኤል በጋዛ ወታደራዊ ዘመቻዋን ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ከ72 ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

የጋዛ ጦርነት ከሦስት ዓመት ገደማ በፊት የተቀሰቀሰው በሐማስ የሚመሩ ታጣቂዎች በደቡባዊ እስራኤል በፈጸሙት ጥቃት 1,200 ሰዎች ከተገደሉ እና 251 ሰዎች ታግተው ከተወሰዱ በኋላ ነው።

'አብርሃም አኮርድስ' ምንድነው?

አሜሪካ ያመቻቸችው እና በ2020 የተፈረሙት ስምምነቶች በእስራኤል እና በአራት የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት መከካል መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመፍጠር ያለመ ነበር።

ስምምነቱ ውስጥ የተካተቱት ባህሬን፣ ሞሮኮ፣ ሱዳን እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ናቸው። እስራኤል ለረጅም ጊዜያት ከቀጣናው አገራት መገለል ገጥሟት ነበር።

የስምምነት ዕቅዱ በትራምፕ የመጀመሪያው የሥልጣን ዘመን ወቅት በኤምሬቶች እና ባህሬን ነበር የተፈረመው። የስምምነቱ መደረስ በአገራቱ መካከል ቱሪዝም፣ ንግድ እና የደኅንነት ትብብር እንዲጨምር ረድቷል።

ኋላ ላይ ደግሞ በ2020 እና በ2021 በተፈረሙ የተለያዩ ስምምነቶች አማካኝነት ሞሮኮ እና ሱዳን ተቀላቅለዋል። ባለፈው ዓመት ደግሞ ካዛኪስታን ስምምነቱን ፈርማለች።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ 2020 ላይ ከፍልስጤማውያን ጋር ለሚደረጉ ቀጣይ ድርድሮች እንደ መሠረት ሊውል የሚችል "የክፍለ ዘመኑ ዕድል" ሲሉ ስምምነቱን አወድሰውት ነበር።

የፍልስጤም ፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ ግን ዕቅዱን "የክፍለ ዘመኑ ጥፊ [ምት]" ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።

ዌስት ባንክ ሆነው በቴሌቪዥን ባስተላለፉት መልዕክት "ለትራምፕ እና ለኔታንያሁ የምናገረው፤ ኢየሩሳሌም ለሽያጭ አትቀርብም፣ መብቶቻችን በሙሉ የሚሸጡም ሆነ ለድርድር የቀሚርቡ አይደሉም። የእናንተ ስምምነት፣ ሴራ አይሳካም" ብለዋል።

የኢራን ባለሥልጣናትም ስምምነቱን አውግዘውታል።

አከራካሪዎቹ ነጥቦች ምንድናቸው?

የፍልስጤም የአገርነት ጥያቄ በአረብ አገራት እና በእስራኤል መካከል ዋነኛው የክርክር ነጥብ ሆኖ ቀጥሏል።

ይህ ስምምነት፤ የአረብ አገራት ለረጅም ጊዜ ይዘው ከቆዩት 'ከእስራኤል ጋር መበደኛ ግንኙነት መድረስ የሚያስችለው ትክክለኛ ዋጋ የፍልስጤም ነጻነት ነው' የሚል አቋም የተቃረነ ነው።

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዝዳንት ሼህ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ከፍልስጤም ሉዓላዊነት ጋር በተያያዘ ስምምነቱን ለመፈረም ያስቀመጡት ቅድመ ሁኔታ፤ እስራኤል ሰፊውን የዌስት ባንክ ግዛት ገንጥላ መውሰዷን ማቆም አለባት የሚል እንደነበር ተናግረዋል።

እስራኤል ዌስት ባንክ እና ምሥራቅ ኢየሩሳሌም በገነባቻቸው 160 ገደማ ሰፈራዎች ውስጥ 700 ሺህ የሚጠጉ እስራኤላውያን አይሁዶች ይኖራሉ። እስራኤል ባትቀበለውም፤ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት እነዚህ ሰፈራዎች ሕገ ወጥ ናቸው።

ስምምነቱ ምን ለውጥ አምጥቷል?

የእስራኤል ባለሥልጣናት ከኤምሬቶች ጋር የሚደረግ የንግድ ልውውጥ በጥቂት ዓመታት ውስጥ በዓመት አራት ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ እና ይህ እድገትም 15 ሺህ የሥራ ዕድሎችን እንደሚፈጥር በ2020 ገምተው ነበር።

2023 ላይ በእስራኤል እና በአብርሃም አኮርድ ፈራሚ አገራት መካከል የሚደረገው የንግድ ልውውጥ ከአራት ቢሊዮን ዶላር አልፏል። ይህ ቁጥር በ2022 ከነበረው ጋር ሲነጻጸር የ16 በመቶ ጭማሪ ያሳየ መሆኑን የእስራኤል የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ቢሮ መረጃ ያሳያል።

ኤምሬቶች ስምምነቱ መፈረሙ ወታደራዊ እና የንግድ ፍላጎቶቿን ይበልጥ እንድታጎለብት አስችሏታል። የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ባህሬን ከዓለም አገራት መካከል በቴክኖሎጂ ዘርፍ እጅግ ካደገችው እስራኤል ጋር በግልጽ የንግድ ልውውጥ ማድረግ ችለዋል።

ሞሮኮ በበኩሏ ከእስራኤል ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን በማሻሻሏ የተወሰነ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማግኘት ችላለች። የሱዳን ተሳትፎ በአንጻሩ ብዙም ፈቀቅ ማለት አልቻለም። ከካዛኪስታን ጋር የተደረሰው ስምምነት ደግሞ ከትዕምርታዊነት የዘለለ አይደለም።

በጥቅሉ ሲታይ ሐማስ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ የተካሄደው የጋዛ ጦርነት በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለውጦታል።

ጥቃቱ እና እርሱን የተከተለው የጋዛ ጦርነት የንግድ ትስስሮች እንዲቀዛቀዙ እንዲሁም በእስራኤል እና በቀጣናው አገራት መካከል ያለው ውጥረት እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል።