የቻይና ሰላዮች የመንግሥት ሠራተኞችን ዒላማ ለማድረግ የሥራ መፈለጊያ ድረ ገጾችን ይጠቀማሉ ሲል ኤምአይ5 አስጠነቀቀ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የቻይና ሰላዮች የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት እና መከላከያ ባልደረቦች የአገር ምስጢር እንዲያወጡ እንደ ሠራተኛ ቀጣሪ ድርጅቶች በመሆን እያጭበረበሩ ነው ሲል ኤምአይ5 አስጠነቀቀ።

የዩኬ፣ አሜሪካ፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ እና ኒውዚላንድ የስለላ ተቋማት በጥምረት ባወጡት ማስጠንቀቂያ የስለላ ተቋማት እንደ ሊንኪድን፣ ኢንዲድ እና አፕ ወርክ የመሳሰሉ ድረ ገጾችን በመጠቀም ሐሰተኛ የሥራ ማስታወቂያዎችን እንደሚያሰራጩ ተናግረዋል።

አመልካቾች "ለሕዘብ ይፋ ያልሆኑ" እና የቻይና የወታደራዊ ደኅንነት አገልግሎት ሊገለገልባቸው የሚችል መረጃዎችን ይፋ እንዲያደርጉ ይገደዳሉ።

ፋይቭ አይስ የተባለው የአምስቱ አገራት ጥምረት የቤይጂንግ ሰላዮች "ለቻይና ስልታዊ እና ታክቲካዊ ጥቅም ሊሰጥ የሚችል ልዩ ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መረጃ ለማግኘት ይፈልጋሉ" ብሏል።

በቻይና ስለላ ተቋማት ዒላማ የሚደረጉ ሠራተኞች የደኅንነት የይለፍ ፈቃድ ያላቸው፣ ምሑራን እና የቲንክ ታንክ ተቀጣሪዎች ናቸው።

የደኅንነት ሚኒስትሩ ዳን ጃርቪስ "ሁሉም የመንግሥት እና የጦሩ ሠራተኞች የብሔራዊ ደኅንነት ባለሥልጣናት ያወጣውን ማስጠንቀቂያ እንዲከተሉ እና በኦንላየን ዒላማ የሚያደርጋቸውን ነገር ነቅተው እንዲለዩ እንዲሁም ደኅንነታችንን አደጋ ላይ ከሚጥል ነገር እንዲቆጠቡ እመክራለሁ" ብለዋል።

"አገራችንን ለመከላከል ጠንካራ እርምጃ የወሰድን ሲሆን ቻይናን ጨምሮ ከተለያዩ አገራት የሚመጡ አዋኪ ተግባራትን መከላከላችንን እንቀጥላለን።በቅርብ ጊዜ የተከሰቱት በርካታ ጉዳዮች የውጭ አገርን ወክለው የሚንቀሳቀሱትን ለፍርድ ለማቅረብ ያለንን አቅም እና ጥንካሬ ያሳያሉ።"

ፋይቭ አይስ የተሰኘው ተቋም ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው የቻይና ሰላዮች ሐሰተኛ የሥራ ማስታወቂያዎችን በመለጠፍ እና የአመልካቾችን ሲቪ በመቀበል ለሚፈልጉት ዓላማ ብቁ ስለመሆናቸው ማጣራት ያካሄዳሉ።

የለይዋቸው አመልካቾች የሚፈልጉትን የመንግሥት እና ወታደራዊ ቁልፍ መረጃ ይዘው እንደሆን ለመለየት በኦንላየን ቃለ መጠይቅ ያደርጉላቸዋል ተብሏል።

አመልካቾቹ የመጨረሻ ደረጃ ላይ የሚደርሱ ከሆነ ቻይና ባላት ዓለም አቀፍ ግንኙነት ወይም መከላከያ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ሪፖርቶችን እንዲጽፉ ይጠየቃሉ።

ተመልማዮች በጻፉት ሪፖርት መጠን በሺህዎች የሚቆጠር ዶላር ክፍያ እንዲፈጸምላቸው ይደረጋል።

ጃርቪስ በኅደር ወር ኤምአይ5 ሁለት የሊንክዲን ፕሮፋይሎች በቻይና የደኅንነት ሚኒስቴር ጥቅም ላይ መዋሉ እንደተደረሰበት አስታውቀዋል።