ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሳዑዲ አረቢያ በተፈጸመባት የድሮን ጥቃት ወሳኝ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧዋን ዘጋች
ሳዑዲ አረቢያ በተፈጸመባት የድሮን ጥቃት ወሳኝ የሆነው የዘይት ማስተለላፊያ ቧንቧዋ ከተመታ በኋላ እንዲዘጋ አድርጋለች፤ ይህም በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ግጭት እየሰፋ መሄዱን ያሳያል እየተባለ ነው።
ይህ ጥቃት ከኢራን ድንበር አጠገብ ከሚገኝ ግዛቷ እንደተፈጸመ ኢራን አረጋግጣ፣ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ወታደራዊ አዛዥ ከኃላፊነት ተነስቶ ምርመራ እንደተጀመረ አስታውቃለች።
1,200 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ይህ የነዳጅ ማስተለላፊያ ቧንቧ፣ በዓለም ትልቋ ድፍድፍ ነዳጅ ላኪ የሆነችው ሳዑዲ አረቢያ፣ የሆርሙዝ ወሽመጥ ከተዘጋ በኋላ ምርቷን ለገበያ ለማቅረብ አማራጭ ሆኗት ነበር።
ይህ ክስተት፣ በኢራን የሚደገፉት የየመን ሁቲ አማጺያን ወሳኝ ድል በማግኘት የቀይ ባሕር ዳርቻዎችን በተቆጣጠሩበት ወቅት የተከሰተ ሲሆን፣ የአሜሪካ እና ኢራን ጦርነት ወደ ሰባተኛ ወሩ በገባበት በአሁኑ ጊዜ በዓለም የነዳጅ ዝውውርን አስተጓጉሏል።
ሳዑዲ አርብ ዕለት እንደገለጸችው፣ ከጥቃቱ በኋላ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧውን ለጥንቃቄ ሲባል ዘግታለች። ይህም በሥፍራው የተቃጠለ ቦታ እና ጭስ የሚያሳዩ የሳተላይት ምሥሎች ከወጡ በኋላ ነው።
የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥቃቱ አንዳንድ ጉዳቶች እና የንብረት ውድመት እንዳስከተለ፣ መጠኑንም ለማወቅ ግምገማ እየተደረገ መሆኑን ገልጿል።
ሮይተርስ የመርከብ ትራንስፖርት ክትትል ተቋማት እና ተንታኞችን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ይህ የቧንቧ መስመር ከዓለም አቀፍ የነዳጅ አቅርቦት ከ4 በመቶ እስከ 5 በመቶው የሚተላለፍበት ነው።
የሳዑዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳለው፣ ክስተቱን ተከትሎ ከኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በስልክ ውይይት ከተደረገ በኋላ ሳዑዲ አረቢያ የበቀል እርምጃ ላለመውሰድ ወስናለች፤ ሆኖም ጥቅሞቿን ለማስከበር "አስፈላጊ የሆኑ ሁሉንም እርምጃዎች" የመውሰድ መብት እንዳላት አስጠንቅቃለች።
በኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በተሰጠ መግለጫ፣ ከኢራን ጋር የሚዋሰነው የመይሳን ግዛት የዘመቻ አዛዥ፣ የድሮን ጥቃቱ ከዚያ ክልል መነሳቱ ከተረጋገጠ በኋላ ከሥልጣኑ መነሳቱን ገልጿል።
በዚህ ሳምንት፣ በየመን የታየው ፈጣን የሁቲ ታጣቂዎች ግስጋሴ የየመንን አብዛኛውን የባሕር ዳርቻዎች ለመቆጣጠር እንዳስቻላቸው ተገልጿል።
ሁቲዎች የቀይ ባሕር እና የሱዌዝ ካናል መግቢያ የሆነውን የባብ ኤል መንደብ ወሽመጥን መቆጣጠር እንደተቻለ እየተናገሩ ነው። በዚህም ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ግንኙነት ካላቸው መርከቦች ውጪ "የባሕር መስመሩ ለሁሉም መርከቦች ክፍት ነው" ብለዋል።
በሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ ላይ የተፈጸመው ጥቃት እና ሁቲዎች ወሳኙን የባብ ኤል መንደብ መተለላፊያን መቆጣጠራቸው በአረቢያ ልሳነ ምድር በሚገኙት ቁልፍ በሆኑት ሁለቱም አቅጣጫዎች በሚደረጉ የመርከብ ጉዞዎች ላይ ጫና መጨመሩን የሚያሳዩ ናቸው።
ከአሜሪካ ጋር እያካሄደችው ባለው ጦርነት ኢራን በዘጋችው የሆርሙዝ ወሽመጥ ምክንያት የነዳጅ ዋጋ ከሐምሌ ወር ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በበርሜል ከ100 ዶላር በላይ ሆኗል። አሁን ደግሞ በቀይ ባሕር ላይ የሚደረገው የመርከቦች ጉዞ ከተስተጓጎለ የነዳጅ ዋጋ ሊንር ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።