ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዓለምን ገጽታ የቀየረው የመስከረም 1 ጥቃት 25ኛ ዓመት እና የስለላው ዘርፍ ያጋጠመው ውድቅት
ለብዙ አስርተ ዓመታት የተለያዩ መሪዎች እንደተናገሩት፣ የማንኛውም መንግሥት የመጀመሪያ ግዴታ ሕዝቡን መጠበቅ ነው። በአውሮፓውያኑ 2001 መስከረም 11 ቀን ግን አሜሪካ ይህንን ግዴታ ለመወጣት ሳትችል ቀርታለች። የስለላ መረጃዎች ቢኖሩም፣ የተለያዩ ፍንጮችን በጊዜው አገናኝቶ ተግባራዊ እርምጃ የወሰደ አልነበረም።
በኋላ "9/11" ተብለው የታወቁት በአሜሪካ ላይ የተፈጸሙት ጥቃቶች እና ለእነሱ የተሰጠው ምላሽ፣ በዚህ ክፍለ ዘመን የመጀመሪያዎቹን ሁለት አስርተ ዓመታት የውጭ ጉዳይ፣ የደኅንነት እና የስለላ ፖሊሲዎችን በእጅጉ የቀረጹ ክስተቶች ሆነዋል።
በ2001 መስከረም 11፣ አጥፍቶ ለመጥፋት የተዘጋጁ የአልቃኢዳ አብራሪዎች የተጠለፏቸው አውሮፕላኖችን ዓለም ንግድ ማዕከል ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች ጋር በማጋጨት ጥቃቱን ከጀመሩ በኋላ በዚያ ቀን 2,977 ሰዎች ተገድለዋል።
እነዚህ ጥቃቶች ከየትም ተነስተው የመጡ አልነበሩም። የአሜሪካ ማዕከላዊ የስለላ ድርጅት (ሲአይኤ) ከ2001 በፊት ለብዙ ዓመታት ስለ አልቃኢዳ እና በስደት ስለሚኖረው ሳዑዲያዊ መሪው ኦሳማ ቢን ላደን መረጃ ነበረው። እንዲያውም እሱን ለመያዝ ተመድቦ የሚሠራ ልዩ ቡድን ነበረው።
ከሴፕቴምበር 11 ጥቃቶች ከዘጠኝ ቀናት በኋላ፣ የዚያን ጊዜ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ "ጦርነት በሽብር ላይ" የተሰኘው ዘመቻ መጀመሩን አወጁ።
ባለፉት 25 ዓመታት በአሜሪካ እና በአውሮፓ በስለላ ረገድ በርካታ ስኬቶች እንዲሁም ውድቀቶች ተመዝግበዋል። ከስኬቶቹ መካከል የከሸፉ የሽብር ሴራዎች፣ የተያዙ ተጠርጣሪዎች፣ ለፍርድ የቀረቡ፣ ጥፋተኛ ሆነው የተፈረደባቸው እና ወደ እስር ቤት የተላኩ ግለሰቦች ይገኙበታል።
ነገር ግን ትልቁን ምሥል ስንመለከትስ በአሜሪካ ታሪክ ከተፈጸመው እጅግ ከባድ የሽብር ጥቃት ወዲህ ባሉት 25 ዓመታት ውስጥ፣ የመረጃ ማሰባሰብ ሥርዓት፣ ሽብርተኝነትን የመከላከል ሥራ እና ስትራቴጂያዊ ዕቅድ አወጣጥ እንዴት ተለወጠ?
ታላቁ ውድቀት
9/11 እጅግ ግዙፍ የስለላ ውድቀት እንደነበር ማንም ሊከራከር አይችልም። ይበልጥ በትክክል ለመናገር ከተፈለገ፣ ይህ በአሜሪካ የስለላ ማኅበረሰብ ውስጥ የነበረ "የአመለካከት ጉድለት" ነበር። በወቅቱ ሁለቱም የአሜሪካ የስለላ ተቋማት ሲአይኤ እና ኤፍቢአይ በእጃቸው ያለውን መረጃ በአግባቡ ቢጋሩ ኖሮ፣ የተከሰተውን አደጋ መከላከል ይቻል ነበር።
ከጥቃቱ በኋላ የተዘጋጀው የ9/11 ኮሚሽን ሪፖርት፣ በአሜሪካ መንግሥት ውስጥ "የአመለካከት፣ የፖሊሲ፣ የብቃት እና የአስተዳደር ውድቀቶች" እንደነበሩ አመልክቷል። ሪፖርቱ እንደደመደመው፣ ሁለቱ ተቋማት የደረሳቸውን መረጃ በአግባቡ ለመገምገም፣ እርስ በርሳቸው ለመጋራት እና ሴራውን ለማስቆም በቂ እርምጃ መውሰድ አልቻሉም ነበር።
ከዚህ አንጻር በ2001 ከነበረው ጋር ሲነጻጸር፣ በምዕራባውያን የስለላ ተቋማት መካከል የመረጃ ልውውጥ እጅግ ተሻሽሏል። በቀድሞ ጊዜ የነበሩት ፉክክሮች እና አለመተማመኖች ለምሳሌ በብሪታንያው በኤምአይ5 እና በፖሊስ የፀረ-ሽብር ክፍሎች መካከል በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል።
ከ9/11 ወዲህ በአሜሪካም የስለላ ሥርዓቱ ሰፊ የሆነ መልሶ ማዋቀር ተካሂዷል። ከዋሽንግተን ዲሲ ውጭ የብሔራዊ ፀረ-ሽብርተኝነት ማዕከል ተቋቁሟል፣ እንዲሁም በ18ቱ የአሜሪካ የስለላ ተቋማት መካከል መረጃ በተገቢው ሁኔታ መጋራቱን የሚቆጣጠር የብሔራዊ የስለላ ዳይሬክተር ተሹሟል።
በሲአይኤ እና በብሪታኒያ አቻው ኤምአይ6 መካከል ያለው ግንኙነት ምናልባት በዓለም ላይ ከሁሉ የበለጠ ጥብቅ ነው። ይህም በአሜሪካ፣ በብሪታንያ፣ በካናዳ፣ በአውስትራሊያ እና በኒውዚላንድ መካከል የሚካሄደው "ፋይቭ አይስ" የተባለውን የስለላ ትብብር ይደገፋል።
ይሁን እንጂ መንታ ሕንፃዎቹ ከተመቱ በኋላም አስከፊ የስለላ፣ የመረጃ ግምገማ እና የስትራቴጂ ዕቅድ ውድቀቶች አጋጥመዋል። በአውሮፓውያኑ 2003 በአሜሪካ የተመራው የኢራቅ ወረራ ከመጀመሩ በፊት፣ ኤምአይ6 የስለላ መረጃው በፖለቲካ እንዲመራ ፈቅዶ ነበር። ይህም ድርጅቱ ከ1950ዎቹ እና 1960ዎቹ ለሌላም አገር በሚሰልለው ኪም ፊልቢ እና በሌሎች የሶቪየት ሰላዮች ከተፈጸመበት የመራጃ ማሹለክ ወዲህ ዝናው ላይ ከባድ ጉዳት እንዲደርስበት አድርጓል።
በዚያን ወቅት ከዋሽንግተን የሚመጣው የፖለቲካ ጫና እጅግ ከፍተኛ ነበር። ጫናውም በፕሬዝዳንት ሳዳም ሁሴን መሪነት ስር የነበረችው ኢራቅ አሁንም "የጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች" እንዳሏት የሚያሳይ ማስረጃ እንዲቀርብ ነበር። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ኤምአይ6 ለጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር መንግሥት በኋላ ላይ ጉድለት ያለበት መሆኑ የታወቀ የስለላ መረጃ አቅርቧል። ኢራቅ በእርግጥ ቀደም ሲል የጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ነበሯት፤ ሆኖም እነዚህ በ1991 ከተካሄደው የባሕረ ሰላጤው ጦርነት በኋላ ሙሉ በሙሉ ተደምስሰው ነበር።
ይህም ከ2003 የኢራቅ ወረራ በኋላ፣ ኤምአይ6 በመስክ ካሉ ወኪሎች የሚደርሰውን "ሲኤክስ" ተብሎ የሚጠራ ጥሬ የስለላ መረጃ የሚገመግምበትን ሥርዓት ሙሉ በሙሉ አሻሽሏል። በአሁኑ ጊዜ መረጃ የሚሰበስቡት መኮንኖች እና ያንን መረጃ የሚመረምሩ ሪፖርት አዘጋጆች በግልጽ ሁኔታ ተለያይተዋል።
የመጀመሪያው ቡድን ከኢራን፣ ከሰሜን ኮሪያ ወይም ከአልቃኢዳ ከመሳሰሉ የሽብር ቡድኖች ውስጥ ከሚገኙ ምንጮች መረጃ የሚያሰባስብ ሲሆን፣ ሁለተኛው ቡድን ደግሞ ያንን መረጃ ይፈትሻል፣ ትክክለኛነቱን ያጣራል፣ አስፈላጊ ሲሆንም ተጨማሪ ማረጋገጫ እንዲቀርብ በማድረግ ወደ ምንጩ ይመልሰዋል።
"የ2003 የኢራቅ ጦርነት በእጅጉ የተሳሳተ የስለላ መረጃ ላይ የተመሠረተ ነበር" ይላሉ በኢራቅ ጦርነት ወቅት የክፍለ ጦር አዛዥ ሆነው ያገለገሉት ጄኔራል ሰር ሪቻርድ ሺሬፍ። "ከዚያ ተምረናልን? አይመስለኝም፣ እኔ እንደማስበው ትምህርት ለመውሰድ ደካሞች ነን። እንደ አዛዥ ለእኔ ስትራቴጂያዊ ውድቀት እየጠበቀን መሆኑ በጣም ግልጽ ነበር።"
ከኢራቅ ወረራ በኋላ እንደገና ምርመራ ተካሂዶ በመጨረሻ ሪፖርት ወጥቶ ነበር። ይህ ሪፖርት ብሪታንያ ኢራቅን በተመለከተ ስለተነገረው የጅምላ ጨራሽ የጦር መሣሪያ ፕሮግራም ያላት የስለላ መረጃ "በጣም የተሳሳተ እና ያልተረጋገጡ ምንጮች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የተመሠረተ" እንደነበር ደምድሟል።
የብሪታንያ የአገር ውስጥ ደኅንነት አገልግሎት ኤምአይ5 ደግሞ በርካታ የሽብር ጥቃት ሴራዎችን በማክሸፍ አስደናቂ ስኬቶችን ቢያስመዘግብም፣ የራሱ የሆኑ ውድቀቶችም አጋጥመውታል።
ከአውሮፓውያኑ 2007 እስከ 2013 ድረስ ኤምአይ5ን የመሩት ሎርድ ጆናታን ኤቫንስ "ከ9/11 በኋላ፣ ለዩናይትድ ኪንግደም እጅግ አስቸኳይ የሆነው የደኅንነት ስጋት፣ ከአልቃኢዳ እና ከተያያዙ ግለሰቦች እንዲሁም ቡድኖች የሚመጣው የሽብርተኝነት አደጋ መሆኑ ተገምግሞ ነበር።"
ነገር ግን በዚያን ወቅት ከ20,000 በላይ መረጃዎች የተመዘገቡበት ቋት ስለነበረ እና በርካታ ምርመራዎች በአንድ ጊዜ እየተካሄዱ፣ ኤምአይ5 የትኛውን ፍንጭ በቅድሚያ እንደሚከታተል በየቀኑ ከባድ ፈተና ይገጥመው ነበር፤ ይህ ፈተናም እስከ ዛሬ ድረስ ቀጥሏል። ሁልጊዜም ትክክለኛውን ውሳኔ መስጠት ግን አልቻለም።
በአውሮፓውያኑ 2005 ሃምሳ ሁለት ሰዎችን የገደሉትን የአጥፍቶ ጠፊ የለንደን የቦምብ ጥቃቶችን መከላከል አልቻለም። የደኅንነት አገልግሎቱ በኋላ የጥቃቱ ዋና አቀናባሪ ሆኖ ስለተገኘው ሞሐመድ ሲዲክ ካን መረጃ ነበረው፤ ነገር ግን ሊፈጽመው ስላለው ጥቃት አላወቀም ነበር። በ2017 የተፈጸመው የማንቸስተር አሬና የቦምብ ጥቃትም በቅርብ ጊዜ የተከሰተ ሌላ የደኅንነት ክፍተት ነበር።
ዛሬም ከሽብርተኝነት የሚመጣው ስጋት አልጠፋም፤ ሆኖም ሎርድ ኤቫንስ እንደሚሉት "ሁኔታው ተለውጧል። በመንግሥታት ያልተደገፈ ሽብርተኝነት አሁንም ከባድ ስጋት ቢሆንም፣ ከመንግሥታት የሚመጡ ስጋቶች እየተባባሱ መጥተዋል፤ እነሱም ቢያንስ ከሽብርተኝነት ያልተናነሱ የብሔራዊ ደኅንነት አደጋዎች ናቸው። እነዚህ ስጋቶች በተለያዩ መልኮች ከሩሲያ፣ ከኢራን፣ ከእነሱ ወኪል ቡድኖች እና ከቻይና ይመጣሉ።"
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከእስራኤል ጋር ተባብረው በኢራን ላይ ጥቃት የፈጸሙበት ውሳኔም የስለላ ማኅበረሰቡ ጉድለት ማሳያ ነበር ተብሎ ሊነገር ይችላል። ሁሉም የአሜሪካ አጋር አገራት በባሕረ ሰላጤው አካባቢ፣ ኢራን በምላሹ የሆርሙዝን ወሽመጥን ልትዘጋ እንደምትችል ከፍተኛ ስጋት እንዳለ ያውቁ ነበር።
ማስጠንቀቂያዎቹ ሁሉ በግልጽ የሚታዩ ነበሩ፣ ሆኖም ትራምፕ ለኢራን የአጸፋ እርምጃ ተቃራኒ ስትራቴጂ የነበራቸው አይመስልም። ይህም በዓለም የነዳጅ ገበያዎች ላይ ከባድ መስተጓጎል አስከትሏል።
የተፈጸሙ በደሎች
ከ9/11 ጥቃቶች በኋላ ወዲያውኑ፣ ሁለተኛ ዙር ጥቃቶች ሊከተሉ ይችላሉ የሚል ሰፊ ስጋት ነበር። በእርግጥም አልቃኢዳ ተጨማሪ ሕንፃዎችን ለማጥቃት "በርካታ አውሮፕላኖች" እንደሚያሰማራ ተናግሮ ነበር።
ይህንን ዓይነት ጥቃት አስቀድሞ ለመከላከል በተደረገው ፍጥነት፣ በአሜሪካ እና በአጋሮቿ በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል። ተጠርጣሪዎች በአፍጋኒስታን እና በፓኪስታን በብዙ ጊዜ ካልተረጋገጡ ጥቆማዎች በመነሳት ይያዙ ነበር።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታስረው፣ ዐይናቸው ተሽፍኖ፣ እጅ እና እግራቸው ታስሮ ከዓለም አንደኛው ጫፍ ወደ ሌላው በማጓጓዝ በኩባ በሚገኘው ጓንታናሞ ቤይ የአሜሪካ የባሕር ኃይል ሰፈር ወደ ጊዜያዊ እስር ቤት ተወስደው ያለ ፍርድ ታስረው ቆይተዋል።
የሰብአዊ መብት ቡድኖች ይህንን ድርጊት በአሜሪካ የሥነ ምግባር መዝገብ ላይ የሰፈረ ጥቁር ነጥብ ሲሉ አውግዘውታል።
በኢራቅ እና በአፍጋኒስታን በአሜሪካ ቁጥጥር ሥር የነበሩ እስረኞች ላይ ስለተፈጸሙ ግፎች በርካታ ቅሌቶች ተጋልጠዋል፤ በጉዳዩ የተሳተፉ አንዳንድ ግለሰቦችም ተጠያቂ ሆነዋል። ተቺዎች ግን ከፍተኛ ኃላፊዎች ከተጠያቂነት አምልጠዋል ይላሉ።
ይሁን እንጂ አሜሪካ አሁንም በጓንታናሞ ቤይ ያለ ፍርድ ማሰርን ትተገብራለች። በ2025 ከ200 በላይ ሰዎችን ከአሜሪካ ወደ ኤል ሳልቫዶር አነጋጋሪ ወደሆነው የሽብርተኝነት እስር ማዕከል ልካለች።
ከ9/11 በኋላ የነበረው ወቅት ለብሪታንያም የሰብአዊ መብት ጥሰት ችግር የተሞላበት ነበር። በ2004 ኤምአይ6 ሊቢያዊው እስላማዊ ተቃዋሚ አብደልሐኪም በልሐጅ እና ባለቤቱ ከታይላንድ ወደ ሊቢያ በግድ እንዲወሰዱ በተደረገበት እርምጃ ተሳትፎ ነበረው።
በዚያም በኮሎኔል ሙዐመር ጋዳፊ አገዛዝ ለዓመታት ታስሮ እና ለስቃይ ተዳርጎ ነበር። ጉዳዩ በኋላ ተጋልጦ በ2018 የብሪታንያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በፓርላማ ፊት ይፋዊ ይቅርታ እንዲጠይቅ ተደርጓል። ዛሬ በስለላ ተቋማቱ ውስጥ በፍጥነት እያደገ ያለው ክፍል የሕግ አማካሪዎች ክፍል እንደሆነ ይነገራል።
የሩሲያ እና የቻይና ኃያልነት
ከ2014 እስከ 2020 ድረስ የMI6 ኃላፊ የነበሩት ሰር አሌክስ ያንገር "በዚህ ምዕተ ዓመት የመጀመሪያዎቹን 20 ዓመታት ሙሉ በሙሉ በፀረ-ሽብርተኝነት እና በፀረ-አመፅ ዘመቻዎች ላይ አተኩረን ነበር" ብለዋል።
ከኃላፊነታቸው ከለቀቁ በኋላ በአንድ ዝግጅት ላይ ሲናገሩ፣ "ቻይና እንደ ወታደራዊ ኃይል እየጠናከረች መምጣቷን እና እንደ ስትራቴጂያዊ ተግዳሮት መደቀኗን ችላ ብለነዋል" ብለዋል።
በተመሳሳይ፣ ጄኔራል ሺሬፍ በ2016 "ዋር ዊዝ ሩሲያ" የተባለ ፖለቲካዊ የልቦለድ መጽሐፍ ጽፈው ሩሲያ ዩክሬንን ሙሉ በሙሉ እንደምትወር ቀድመው ገምተው ነበር።
ከ9/11 እና ከ"ጦርነት ሽብር ላይ" ከተባለው ዘመቻ በኋላ፣ ምዕራባውያን አገራት ከታሊባን፣ ከአይሲስ ጋር በመዋጋት እና የኢራቅን ውስብስብ ወረራ ለማስተካከል ሲጠመዱ፣ ሩሲያ እና ቻይና ታላላቅ የመሣሪያ ማዘመኛ ፕሮግራሞችን ጀምረዋል። እንደ ሃይፐርሶኒክ ሚሳዔሎች ያሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ያካተቱ እነዚህ ፕሮግራሞች፣ ኔቶ የነበረውን ወታደራዊ ብልጫ በከፍተኛ ደረጃ አዳክመዋል።
የደኅንነት ትንተና ዋና ተንታኝ የሆኑት ሳም ኦልሰን "የምዕራቡ ስህተት ከ9/11 በኋላ በፀረ-ሽብር ሥራዎች መጠመዱ ብቻ አይደለም። እንዲሁም የቻይናን እድገት ባህሪ በትክክል አልተረዱትም፤ የኢኮኖሚ ለውጡ ወደ ፖለቲካውም ይሻገራል ብለው አስበው ነበር።"
ቻይና፣ ልክ እንደ ኢራን፣ ሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ፣ ለስለላ መረጃ ማሰባሰብ እጅግ አስቸጋሪ "ከባድ ዒላማ" እንደሆነች ትቆጠራለች። በ2001 የባዮሜትሪክ መረጃ ቴክኖሎጂ ገና በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ነበር፤ ከዚያ ወዲህ ግን ፊትን፣ የዐይን ብሌንን ለይቶ ማወቅ እና ሌሎች መለያ ቴክኖሎጂዎች ስለተስፋፉ፣ ዛሬ ወኪሎችን እና መሪዎቻቸውን ሳይታወቁ ድንበር አቋርጠው ማንቀሳቀስ እጅግ ፈታኝ ሆኗል።
ስለዚህ፣ የምዕራባውያን የስለላ ተቋማት ቻይናን ምን ያህል በደንብ ይረዳሉ?
ከሩሲያ ጋር በመሆን፣ ቻይና ዛሬ ለኤምአይ6 ከፍተኛ የስለላ ዒላማ ናት።
"የምዕራቡ ዓለም የስለላ ተቋማት ስለ ቻይና ብዙ ነገሮችን ያውቃሉ" ይላሉ የደኅንነት ተንታኙ ሳም ኦልሰን። "ትልቁ አደጋ ግን እያንዳንዱን ቁራጭ መረጃ በተናጠል ማየታቸው እንጂ፣ ቁርጥራጮቹ አንድ ላይ ሲደመሩ ምን ማለት እንደሆነ ሁልጊዜ አለመረዳታቸው ነው።
የቻይና ኃይል ከእንግዲህ መርከቦች፣ ሚሳዔሎች እና ወታደሮች ብቻ አይደሉም። እየጨመረ የሚገኘው ኃይሏ በሴሚኮንዳክተሮች፣ በወሳኝ ማዕድናት፣ በባትሪዎች፣ በወደቦች፣ በቴሌኮሙኒኬሽን መሠረተ ልማቶች እና በኢንዱስትሪ ምርታማነት ላይ ጭምር ነው።...ስለዚህ ችግሩ ብዙ ጊዜ የመረጃ ማሰባሰብ ውድቀት ሳይሆን የስትራቴጂያዊ ትርጓሜ ስህተት ነው።"
ከ25 ዓመታት በፊት፣ በ9/11 ጥቃቶች ቀን የአሜሪካ የስለላ ወኪሎች መረጃዎች በእጃቸው ላይ ነበሯቸው፤ ነገር ግን በጋራ እነዚህን ሁሉ ማገናኘት እና የሚመጣውን አደጋ በግልጽ ሁኔታ ማየት አልቻሉም። አገራት ታላቅ የስለላ መረጃ ቢኖራቸውም፣ ለወሳኝ አገልግሎት ጥቅም መስጠት ካልቻሉ ምንም ፋይዳ የለውም።
የተለወጠ ዓለም
ከዚያ አሜሪካንን እና ዓለምን ካናጋው የኒውዮርክ መንትያ ሕንጻዎች ጥቃት በኋላ ባለፉት 25 ዓመታት፣ የስለላና የፀረ-ሽብር ዓለም ከመታወቁም በላይ ተለውጧል። ከሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) እና ከረቂቅ ኮምፒውተሮች መምጣት ጋር፣ ይህ ለውጥ ወደፊትም ይቀጥላል፤ በአንዳንድ ዘርፎች ደግሞ በእጅጉ በፍጥነት ይፈጸማል።
ነገር ግን በተቃራኒ ትረካዎች እና ጥቅሞች በተሞላ ዓለም ውስጥ፣ የምዕራባውያን አገራት ብቻቸውን በስለላ ሥራ ውድቀት፣ በቸልተኝነት ወይም በስትራቴጂያዊ ስሌት ስህተት ከሌሎች የተለዩ አይደሉም። ሌሎች ታዋቂ ምሳሌዎችም አሉ፤ ለምሳሌ በ2022 ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችው ወረራ እና አንዳንዶች "የእስራኤል 9/11" ብለው የጠሩት፣ በ2023 ሐማስ በእስራኤል ላይ የፈጸመው ወረራ ይገኙበታል።
በመጨረሻም፣ ትላልቅ ብሔራዊ እና ስትራቴጂያዊ ውሳኔዎች አሁንም ጥያቄ የሚያስነሱ ናቸው። ብሪታንያ የፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽን የኢራቅ ወረራ መቀላቀሏ ትክክል ነበር? በአፍጋኒስታን በአሜሪካ በተመራው ዘመቻ መሳተፏ ተገቢ ነበር? ከዚያስ ከ20 ዓመታት በኋላ አገሪቱን ለታሊባን ጥለው በፍጥነት መውጣታቸውስ ትክክል ነበር?
እነዚህ እና ተመሳሳይ ሌሎች ጥያቄዎች እስከዛሬ ድረስ መልስ እየተፈለገላቸው እና ጥልቅ ውይይቶችን እያስነሱ ቀጥለዋል።